31/03/2022
መንፈሳዊ የማንነቴ ክፍል
ይህ ክፍል በሌሎቹ አስተዋጽኦ የሚገነባ የማንነታችን ክፍል ሲሆን በጣም ጥልቅና ከፍተኛ አቅም የሚደራጅበት ነው። ለምሳሌ እሴቶቻችን የሚሰሩትም ሆነ የሚካተቱት በዚህ ክፍል ነው። እሴቶች ስንል በህይወታችን ከፍ ያለ ግምት የምንሰጣቸው እና የምር ስለራሳችን ያለንን ምስል ያሳያል። ይኸውም ሲባል በራሳችንም ሆነ በሌሎች ላይ ያለን እምነት ፣ ስለዓለምም ሆነ ስለነገሮች ያለን እይታና አመለካከት ፣ በህይወታችን ማሳካት የምንፈልገው ዓላማ ፣ ህይወታችንን የምንመራበት ፍልስፍና ፣ ወዘተርፈ አውቀነውም ይሁን ሳናውቀው የሚቀዳው ከእሴቶቻችን ነው።
በተጨማሪም ይህ የማንነታችን ክፍል ዘላለማዊና በቀላሉ የማይደረስበት ከመሆኑ የተነሳ ያለኛ በጎ ፈቃድ ሌሎች ሰዎች ሊያጠቁትም ሆነ ሊያሸንፉት የሚችሉት አይደለም። ይህ የማንነታችን ክፍል በአካላችን ውስጥ የሚካሄደውን ልዩ ልዩ ስርዓቶች ማለትም የምግብ መፈጨት ስርዓት ፣ የአተነፋፈስ ስርዓት ፣ ወዘተርፈ የሚያንቀሳቅሰው የፈጣሪ ሃይል ጋር የተቆራኘ ነው። ሆኖም ግን ይዘቶቹ የሚሰሩትና የሚዳብሩት ከአደግንበት ማህበረሰብ ባህልና ወግ እንዲሁም በተስማማ ሁኔታ ስለሆነ የሁላችንም የተለያየ እና ለራሳችን ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ነው። ስለሆነም ከሌሎች ሰዎች ጋር ሊነጻጸርም ሆነ በሌሎች መመዘኛ ሊመዘን የሚገባው አይደለም። ለምሳሌ አንድ ሰው በህይወቴ ማሳካት የምፈልገው ይህንን ነው ወይንም ያንን ነው ካለ ትክክል ነው ፤ ምንም እንኳን ያ ነገር በሌሎች ሰዎች መመዘኛ ተቀባይነት ቢኖረውም ባይኖረውም።
ሁላችንም ሁልጊዜ የተነቃቃን ነን ምንም እንኳን አነቃቂ ንግግር ነው የሚያነቃቃን የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እየጎላ ቢመጣም። የተነቃቃን ለመሆናችን ማሳያው ይህንን ወይንም ያንን ማከናዎናችን ሲሆን ጉዳዩ ግን በምንፈልገውና በሚያስፈልገን መካከል በምናደርገው ውሳኔ ላይ የሚመሰረት ነው። በሌላ በኩል ማንም ማንንም ሊያነሳሳ አይችልም የሚባለው መነቃቃታችን የሚመነጨው ከመንፈሳዊ የማንነታችን ክፍል ስለሆነ ነው። በእርግጥ ከተናጋሪዎቹ በምናገኘው እውቀትና መረጃ አማካኝነት ማሳካት የምንፈልገውን ነገር እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ስልቶችን ልናፈልቅና ትጋታችንን ልንጨምር እንችላለን። ከዚህ ውጭ ግን ምንም የሚኖርለት ዓላማ ለሌለው ሰው ንግግሮቹ ከመረጃነት አልፈው ምንም የሚለውጡት ነገር የለም።
ስኬታማ ሰኞ ይሁንልን!!!