21/10/2023
መናኙ ሃኪም !............ .......
በአዲስአበባ የፎቅ ጫካ ውስጥ እልፍኛቸውን ዋሻ ያደረጉ፣ ኃጢያት በበረታበት ከተማ በምናኔ የሚኖሩ፣ በትትልቅ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው እየሰሩ ገንዘብ፣ዝናንና ክብርን ንቀው የተቸገሩት ለመርዳት የሚሰሩ፤ ዓለምና አምሮቷን ንቀው ግርማ ሌሊቱን ጸብዓ አጋንንቱን ታግሰው በበረሃ ከሚኖሩ ባህታውያን ያላነሰ የቅድስና ሕይወት ላይ የደረሱ ስውር ባሕታውያን ብዙ ወንድምና እህቶች በየከተማው ያሉባት ሀገር ናት ኢትዮጵያ።
ጊዜው ቢረዝምም በአንድ ወቅት ለጊዜው ስማቸውን የማልጠቅሳቸው በገዳም የሚኖሩ አንድ ትልቅ አባት ያጫወቱኝን ታሪክ በአጭሩ ላውጋችሁ።
"ልጄ በአንድ ወቅት ወደ ገዳሙ የመጣ አንድ ወንድም ያጫወተኝ ታሪክ ልንገርህ....." ነገሩ ወዲህ ነው በአዲስአባ የሚኖርና በአንድ ታዋቂ ሃኪም ቤት ተቀጥሮ የሚሰራ አንድ ዶክተር ነበር። ይህ ሃኪም በሙያው አንቱ የተባለ የታፈረና የተከበረ ሃኪም ነው። ብዙ ሕመምተኞችን አምላኩን አጋዥ በማድረግ የፈወሰ ጎበዝ ሃኪም ነበር።
ቤተሰቡ ጥሩ ገቢ ያላቸው በመሆኑ የሚኖረው ከቤተሰቡ ጋር በአንድ ቤት ነበር። በሚሰራበት መስሪያ ቤት ከትሕትናው፣ከእርጋተውና ከጠንካራ ሰራተኛነቱ በተጓዳኝ በሁለት ነገር የስራ ባልደረብቹ ያስታውሱታል።
1ኛ ሁልጊዜ ሽክ ብሎ ሙሉ የሱፍ ልብ ለብሶ ወደ ስራ ገበታው በመምጣቱና።
2ኛ "ለጤናዬ የሚስማማኝን ቤት በልቼና ጠጥቼ ስለመጣሁ አልበላም" በሚለው ንግግሩ።
ከቤተሰቡ ጋር ሲኖርም ማንም የማይገባበት የራሱ ክፍል ቤት ነበረው።
ቤተሰቡም "በሕይወት እያለን አግብተህ ፣ወልደህ ከብደህ እንይህ " ሲሉትም " አምላክ ሲፈቅድ" ከማለት ውጪ አይመልስም ነበር። የሚገርመው ይህ ሰው ሳይታመም በድንገት ያርፋል። ቤተሰቡም ይደናገጣል።
እንግዲህ ጉዳዩ ከዚህ በሗላ ነው የታወቀው። ገናዦች መጥተው ገላውን ለማጠብ ልብሱን ሲያወልቁ " ቅንአተ ዮሐንስ " ታጥቆ መላ ሰውነቱን በሰንሰለት አስሮ ያገኙታል። የጆቹ መዳፎች ጠቋቁረው፣ ጉልበቱም ገርጦ፣ ሰንሰለቱም በሰውነቱ ላይ መስመር ሰርቶ ይመለከታሉ። በመገረም አዲስ ነገር ቢሆንባቸው " ምንድን ነው" ብለው ቤተሰቡን ይጠቃሉ። ቤተሰቡም "ኸረ እኛም አናውቅም ከብዙ ጊዜ በሗላ ክፍሉ ብንገባ የጥራጥሬ አይነት በፌስታል ተቋጥሮ ከበሶና ከስኳር ጋር አገኘን። ክፍሉም እንደምትመለከቱት የጸሎት ቤት ነው የሚመስለው።አምላኩን የሚፈራ ጠንካራ ክርስቲያን አንደ ሆነ ልጃችንን እናውቃለን አንዲህ አይነት ሕይወት እንዳለው ግን አናውቅም " በማለት ይመልሳሉ።
በስፍራው የተገኙ ጓደኞቹም ይህንን ሲመለከቱ " ለካ ጓደኛችን ባሕታዊ ነበር። ሙሉ ልብስ በከረባት ሁሌ ለብሶ የሚመጣው ለካ በውስጥ የደበቀውን የምናኒ ልቡሱን እዳናይና እንዳንጠረጥረው ነው። ለካ ምግብ ቤት በልቼ መጥቻለው የሚለን "የእርሱ ምግብ ቆሎና በሶ ነበር።" ብለው ተላቀሱ። በምናኔ ሕይወቱ እጅግ ተደነቁ።
ይኸውልህ ልጄ "ሁለተኛው በጣም ያስደነቀኝ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተፈጠረው ነገር ነበር። " ማን የተገኘ ይምስልዃል ?" አሉኝ በተመስጦ እያዳመጥኳቸው መሆኔን ተገንዝበው። ኸረ ምኑን አውቄ አባቴ። አልኳቸው " የተገኙትማ አይናቸው የፈረጠ፣እግራቸው የተቆረጠ፣ ዓይነ ስውራን፣ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያን ከየት መጡ ሳይባል ከቀባሪ ዘመድ አዝመድ በቁጥር በልጠው። የለቅሶ እሩምታ ያዘንቡ ጀመር። " ወይኔ አባቴ" " ከእንግዲህ ማን ያክመኛል " የማትጠየፈኝ አንተ ነበርክ " ሕይወቴን፣ ልጄን ማን ነጠቀኝ" ለማን ጥለኸን ሄድክ "የሚሉ የለቅሶ ድምጾች ተበራከቱ። ቤተሰቡም የሰፈሩ ሰዎችና ጓደኞቹም በተፈጠረው ነገር ተደነቁ። " እነ ማናቸው " በሚል..
ከመሃል አንድ ሰው ጠርተው ሲጠይቁ ያገኙት መልስ። እጅግ ልብ የሚነካ ነበር።" በትርፍ ሰዓቱ ሳይቀር እየሰራ የሚያስተዳድራቸው፣ የሚንከባከባቸው፣የሚጦራቸው፣ ፍቅር የሚሰጣቸው ሰዎች እንደሆኑ ይሰማሉ ። ይኼንን ከሃኪሙና ከእነዚህ ሰዎች በቀር ማንም አያውቅም ነበር።
የሚደንቀው በአንድ ቤት አብረውት የሚኖሩ የገዛ ወላጆቹ እንኳን ስለ እርሱ የምናኔ ሕይወት አያውቁም ነበር።
ታዲያ ከዚህ በላይ የምናኔ ሕይወት ወዴት አለ ? በመሃል ከተማ በአዲስአበባ እንዲህ ያለ የቅድስና ሕይወትን መኖር እንዴት አያስገርም አያስደንቅ ልጄ። መናኝ በበረሃና በገዳም ብቻ ሳይሆን በከተማም አለ። ታሪኩን ከሰማሁት የዘገየ ቢሆንም ሁሌ ስለሚደንቀኝ ነው ያጫወትኩህ።" በማለት የነገሩኝ ታሪክ ዛሬ በልቤ ውስጥ ይታወሰኛል።
የሰው ልጅን ክፋት፣ ተንኮል፣ጸብ፣ክርክር፣ መገፋፋትና መጠላላት ስመለከት ሁልጊዜ ይኼንን አስታውሰዋለሁ።
እኔ ኃጢያተኛውና በደለኛው ብቻ ሳይሆን ይህች ዓለም የከተማ ባሕታውያን የሚኖሩባትም ዓለም ናትና በዚህ እጸናለሁ። እጽናናለሁ።
ያለንበት ሁኔታና ቦታ፣ የሰዎችን ክፋትና ተንኮል እየዘረዘርን ከመውቀስና ከማማረር እኛ ራሳችንን በማረምና በማስተካከል ኃጢአት በበዛበት ከተማ " እንዴት ከእግዚአብሔር ጋር መኖር እንደምንችል እናስብ"
መንፈሳዊነት ረቂቅ ነው። መንፈሳዊነት ጥልቅ ነው። መንፈሳዊ ሰው እርሱ ሁሉን ይመረምራል። እርሱ ግን በማንም አይመረመርም። የክርስቶስ ልብ አለውና።
የሃኪሙ ታሪክም የሚያስረዳን ይኼንኑ ነው።
❤ልዑል አምላክ ለሁላችን ለጽድቅ የመነነ ልብ ያድለን።
✍️ ኤፍሬም ሀብተ ማርያም (መ/ር)
አዳማ -ኢትዮጵያ
❤ 👉 ለመከታተል 👇
https://t.me/joinchat/UKtl1jyrzcSQl68D
..............................