15/02/2022
#አሸባሪው ሕወሓት በፈጸመው ዳግም ወረራ ከ300 ሺ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን የአፋር ክልል አስታወቀ፣፣
ሰመራ-የካቲት 08, 2014 (አፋ.ብ.መ.ድ)
አሸባሪው ሕወሓት በፈጸመው ዳግም ወረራ ከ300 ሺ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን የአፋር ክልል አስታወቀ፣፣
አሸባሪው ሕወሓት በሰሜናዊ የአፋር ክልል ዞን ሁለት በአምስት ወረዳዎች ላይ በፈጸመው ዳግም ወረራ ከ300 ሺ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሕመድ ከሎይታ አስኑም በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አሸባሪው ሕወሓት ከዚህ ቀደም በአፋር ክልል በሁለት ዙር በፈጸመው ወረራ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን በላይ ዜጎች ለተለያዩ ጉዳቶች ተዳርገው ነበር፡፡
ቡድኑም ይህንን ሽንፈት ለማካካስ እና የአፋር ጅቡቲ መንገድን ለመዝጋት ካለው ጉጉት የተነሳ ዳግም በሰሜናዊ የአፋር አካባቢ ለሶስተኛ ጊዜ በከባድ መሳሪያ በመታገዝ ጥቃት መሰንዘሩን እና በዚህም በመጋሌ፤ አብአላ፤ በርሃሌ፣ ኩናባር እና አረርቲ ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን አቶ አህመድ ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም ይህ ተግባሩ ለጊዜው በዜጎች ላይ ጉዳት ቢያስከትልም ዓላማው የማይሳካ ቅዠት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
ይህ ቡድን እየፈፀመ ያለው ተግባር ከበረሃ አንበጣ በላይ የከፋ ነው የሚሉት አቶ አህመድ፤ “የበረሃ አንበጣ አረንጓዴና እርጥብ ነገር ይፈልጋል፤ ይህ ቡድን ግን ህይወት ያለውም ሆነ የሌለው ነገር ሁሉ ነው የሚያጠፋው፤ የዚህን ቡድን የጥፋት መጠን ለመግለፅ ከባድ ነው” ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ሁለት ጊዜ በፈፀመው ወረራ ያወደመው የመንግስት ንብረት የህብረተሰቡን ሳይጨምር ከ10 ነጥብ ሶስት ቢሊየን ብር በላይ እንደነበር እና አሁን ደግሞ በዞን ሁለት በአምስት ወረዳዎች ላይ እያደረሰ ያለው ውድመት እየተጠና እንደሆነ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
የዞን ሁለት ነዋሪዎች በአብዛኛው አርብቶ አደር መሆናቸውንና የኑሮ መሰረታቸውም ፍየል፤ ከብት፣ ግመልና መሰል የቤት አንስሳት ናቸው ያሉት አቶ አህመድ፤ አሸባሪው ቡድን ደግሞ እንስሳቱን ስለዘረፈባቸው የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
አቶ አህመድ እንደገለፁት አሁን የተወረሩት አካባቢዎች በአንድ በኩል ከትግራይ ማህበረሰብ ጋር ከፍተኛ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ያላቸው ሲሆን፤ በአብዛኛው የአካባቢው ነዋሪዎችም አርብቶ አደር በመሆናቸው አሸባሪው ቡድን ወረራ ይፈጽምበታል ተብሎ አልታሰበም፡፡ በሌላ በኩል አብዛኛው ህዝብ ትጥቅ የሌለውና ሰላማዊ ህይወት የነበረው ነው፡፡
አካባቢው ከሌላው የአፋር አካባቢ በተለየ ተራራማ በመሆኑ አሸባሪው ቡድን ከተራራ ላይ በመሆን በከባድ መሳርያ ህዝቡን ጨፍጭፏል ያሉት አቶ አህመድ፤ በዚህም በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች መጎዳታቸውንና ከዚህም አልፎ በደረሰው ጥቃት እና መፈናቀል የደረሰው የስነልቦና ቀውስ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ቀደም ሲል የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት እያደረገ በነበረበት ሁኔታ አሸባሪው ሕወሓት ሌላ ጥቃት በመሰንዘሩ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እንዲፈጠር ቢያደርግም፣ አሁንም የተፈናቀሉ ዜጎችን በአንድ ቦታ በማስፈር ድጋፍ ለማድረግና መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ እንደሆነ አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ከዚህ አልፎ ወደሌሎች ቀበሌዎች እንዳይስፋፋ የፀጥታና የሰላም ኮማንድ ፖስቱ ስራውን እየሰራ መሆኑንና ኅብረተሰቡም ራሱን ለመከላከል ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን