13/08/2024
"መንግስት በፓስፖርት ላይ ያደረገዉ ጭማሪ የሰዎችን የመዘዋወር ነፃነት መብት የሚጥስ ከመሆኑ በላይ ማሻሻያው የተጋነነ መሆኑ ተገለፀ"
የኢትዮጵያ ኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በዚህ ሳምንት ይፋ ያደረገዉ የአገልግሎት ክፍያ ማሻሻያዎች ወቅቱን ያልጠበቀና የሰዎችን አቅም ያላገናዘበ ከመሆኑ በላይ በነፃነት የመዘዋወር መብትን የሚጥስ እንደሆነ ተገለፀ።
በህገመንግስቱ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ እና በአንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ ኢትዮጵያ ያጸደቀችዉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሀገሪቷ የራሷ ህግ አካል መሆናቸውን እንዲሁም እነዚህ አለምአቀፍ ሰነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ እንደሚተረጎም ያስቀምጧል።
ይህን የህግ ድንጋጌ በመያዝ የኢትዮጵያ ህገመንግስት በአለምአቀፍ ሰነዶችና መርሆዎች መሰረት ሰብዓዊ መብቶች እንደሚተረጎም በማስቀመጡ ምክንያት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ይገለጻል ።
የህግ ባለሙያ እና የኢትዮ-አሊያንስ አድቮኬትስ ኤልኤልፒ የህግ ተቋም አጋር የሆኑት አቶ ከተማ አዳነ ለካፒታል እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን እነዚህ አለምአቀፍ ስምምነቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ የፓስፖርት ክፍያ በነፃነት የመዘዋወር መብት ላይ እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ፓስፖርት እንዳያገኙ እና መብታቸውን እንዳይጠቀሙ ያደርጋል ብሎ ያስቀምጣል ።
ከፍ ያለ የፓስፖርት ክፍያ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በማብራራት በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ግለሰቦች ተጠቃሚ የማያደርግ ነዉ ። ይህም በህብረተሰቡ ዉስጥ ሙሉ በሙሉ የመሳተፍ የመስራት ወይም የዉጪ ትምህርት እድሎችን የመከታተል ጨምሮ የዜግነት መብቶች ላይ ገደብ ሊጥል እንደሚችል አቶ ከተማ አስረድተዋል ።
ከሶስት ወራት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የፀደቀው እና ከነሐሴ 1ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ የጀመረዉ ይህ ማሻሻያዉ ሲጠበቅ የነበረ መሆኑ ተነግሯል ። ከፍተኛ ጭማሪ የተደረገበት የፓስፖርት ዋጋ ብዙዎች አስደንጋጭ እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሀሳባቸውን ሲሰነዝሩ ተስተውሏል ።
የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጎሳ ደምሴ ማሻሻያውን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ የምትጠቀምባቸው ፓስፖርቶች እንዲሁም ተያያዥ ግብዓቶች ወደ ሀገር ዉስጥ የሚገቡት በዉጪ ምንዛሪ በመሆኑ አሁን ባለዉ ንባራዊ ሁኔታ ግን ምንዛሪው በሶስት እጥፍ ስለጨመረ የፓስፖርት ክፍያዉ ላይ ጭማሪ ለማድረግ አስገዳጅ ሆኖ መገኘቱን ገልፀዋል ።
"ሀገሪቷ አሁን የምትጠቀምበትን ፓስፖርት ወደ ኤሌክትሮኒክስ ( E-passport) ለመቀየ አስገዳጅ ሁኔታ ላይ ነዉ ያለነዉ ። ይህ ሲሆን ደግሞ ፓስፖርቱን ለማዘጋጀት የሚያፈልጉ ግብዓቶች በ 3 እጥፍ የዉጪ ምንዛሪ እንዲጨምር ሆኗል" ሲሉም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል ።
የፓስፖርት ክፍያዎች ብዙ ጊዜ በአስተዳደር ወጪዎች ላይ ተመስርተው መጨመራቸው በመሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች አጠቃቀም ላይ በተለይም የመንቀሳቀስ፣ የእኩልነት እና የዜግነት ተጠቃሚነትን በተመለከተ ከፍተኛ እንቅፋት እንደሚኖረው የተገለፀ ሲሆን ክፍያዎችን ሲያዘጋጁ ወይም ሲጨምሩ መንግስታት እነዚህን አንድምታዎች ማጤን አስፈላጊ መሆኑንና አፅንኦት እንዲሰጠዉ ተጠይቋል።
(Capital)