26/03/2021
ሁለተኛው ታሪኬ ስለማፍቀርና ማጣት ነው፡፡ ዕድለኛ ነኝ፡፡ ማድረግ የምፈልገውን ያገኘሁት ገና በለጋ ዕድሜዬ ነበር፡፡ ጓደኛዬ ዎዝ እና እኔ አፕልን በቤተሰቦቼ ጋራዥ ውስጥ ስንጀምር ገና የ20 ዓመት ወጣት ነበርኩ፡፡ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል ፈግተን፣ በ10 ዓመት ውስጥ፣ አፕል በሁለታችን ጋራዥ ውስጥ ከተቋቋመ ኩባንያነት ተነስቶ 4,000 ተቀጣሪዎች ወዳሉት የባለ 2 ቢሊዮን ዶላር ግዙፍ ኩባንያነት ተመነደገ፡፡ የመጨረሻው ድንቁ ፈጠራችንን፣ ማኪንቶሽ (ኮምፒዩተር)ን ከአንድ ዓመት በፊት ለዓለም አበርክተናል። እናም እኔ 30ኛ ዓመቴን እንደያዝኩ ተባረርኩ! ...እንዴት ነው ራሳችሁ ካቋቋማችሁት ኩባንያ የምትባረሩት?
ነገሩ እንዲህ ነው። አፕል እያደገ ሲመጣ በጣም ክህሎት አለው ብዬ ያመንኩበት ሰው አብሮኝ ኩባንያውን እንዲመራ ቀጠርነው፡፡ በመጀመሪያ ዓመት አካባቢ ነገሮች በጥሩ ሁኔታ ላይ ነበሩ። ቀስ በቀስ ግን የድርጅቱን መፃኢ ዕድል በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ራዕያችን እየተራራቀ መጣና በስተመጨረሻ ጭርሱኑ ተለያየን፡፡ ስንለያይ፣ የዳይሬክተሮቹ ቦርድም ለእሱ ወገኑና፣ በ30 ዓመቴ ተባረርኩ። ሀገር ባወቀው አሳፋሪ ሽንፈት፤ ተባረርኩ! ህይወቴን የሰጠሁለት ነገር በአንዴ ከእጄ በንኖ ጠፋ፡፡ ይጎዳል፤ ተጎዳሁ፡፡ ለጥቂት ወራት ያህል ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንኳን አላወቅኩም ነበር፡፡
የቀድሞውን ትውልድ ስራ ፈጣሪዎች ራዕይ ያበላሸሁ፤ ለእኔ የተላለፈልኝን ሰንደቅ እንደጣልኩ ተሰማኝ፡፡ ዴቪድ ፓካርድና ቦብ ኖይስን አግኝቼ ለከፋው ሽንፈቴ ይቅርታ ልጠይቅ ተፍጨረጨርኩ፡፡ በህዝብ ፊት ነበራ የተዋረድኩት። ከኮምፒዩተር ዓለሙ ማማ፤ ከሲልከን ቫሊውም ሹልክ ብዬ ልጠፋ አሰብኩ፡፡ ግና…ቀስ በቀስ አንዳች እውነት ይገለፅልኝ ጀመር፡፡ ምንም ይሁን ምን፤ እስከዛሬ የሰራሁትን እወደዋለሁ፡፡ አፕል ውስጥ ከተከሰቱት ሁነቶች አንዳችም የተለወጠ ነገር የለም፤ አሁንም እንደተባረርኩ ነው፡፡ ቢሆንም ግን፣ አሁንም ድረስ፣ የምሰራውን እወደዋለሁ። እናም፣ እንደገና፣ እንደ አዲስ ለመጀመር ወሰንኩ፡፡
ያኔ ባይታየኝም ከአፕል መባረሬ ለእኔ በህይወቴ ሊያጋጥሙኝ ከሚችሉት ታላላቅ ክስተቶች አንዱ ሆነ፡፡ የስኬታማነት ሸክም በውድቀት ሳቢያ በሚከሰት የእንደገና ጀማሪነት ቅለት ተተካ፤ ስለ ሁሉም ነገር ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ የማይኮንበት ጅማሮ፡፡ የህይወቴ እጅጉን በፈጠራ የተንበሸበሸው ወቅት ይፈነጥቅ ዘንድ መንፈሴ ነፃ ወጣች፡፡
በቀጣይ አምስት ዓመታት ኔክስት እና ፒክሳር የተሰኙ ኩባንያዎችን አቋቋምኩ፡፡ አሁን ላይ ሚስቴ ከሆነችው አስደናቂ ሴት ጋር በፍቅር ወደቅኩ፡፡ ፒክሳር የዓለማችን የመጀመሪያው የሆነውን የኮምፒዩተር አኒሜሽን ፊቸር ፊልም፣ ቶይ ስቶሪን፣ ለመስራት በቃ። እናም የዓለማችን እጅጉን ስኬታማው የአኒሜሽን ሲቱዲዮ ለመሆን ቻለ፡፡
አስደናቂ በሆነ የክስተቶች መገጣጠም ሳቢያ፣ አፕል ኔክስትን ሲገዛ ደግሞ፣ እኔም በዛው አፕልን ዳግም ተቀላቀልኩ፡፡ ኔክስት ውስጥ ያጎለበትናቸው ፈጣራዎችም የአፕል የወቅቱ ህዳሴ ስረ መሰረት ሆኑ፡፡ ሎረን እና እኔ አሁን ላይ አስደሳች ቤተሰብ መስርተናል፡፡
ከአፕል ባልባረር ኖሮ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ላገኝ እንደማልችል እርግጠኛ ነኝ፡፡ በዕርግጥ በጣም መራር መድኃኒት ነበር። ግን እንደምገምተው ለበሽተኛው የግድ አስፈላጊ ነበረ፡፡ አንዳንዴ ህይወት አናታችሁን ትቀውራችኋለች፡፡ እምነት ግን አትጡ፡፡ በሽንፈቴ ውስጥ ሁሉ እንዳላቆም ፣ እንድቀጥል የረዳኝ የምሰራውን መውደዴ ለመሆኑ ጨርሶ ጥርጥር የለኝም፡፡ የምታፈቅሩትን ልታገኙ ይገባል፤ ይህ ደግሞ ለስራችሁም ሆነ ለፍቅራችሁ ወሳኝ ነው፡፡
መልካም ቀን!