09/08/2026
የቅዳሁድ ወግ - በሀይቅ በኩል
በተስፋዬ ይመር ( ወርጣዬ)
ከሎጎ ሀይቅ ሪዞርት ጉብኝት በኃላ የተፃፈ
………………. ..,,,,
"ሀይቅ" ስል ከደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች ጋር አጣምሬ ነው፣ ከአምባሰል፣ ተሁለደሬና ወረባቦ ወረዳዎች እንዲሁም በቆላው በኩል ሀብሩ ወረዳ ነጥዬ አይቼ አይደለም - እስከአፋርና ወደብ የሚዘረጋ መገናኛ አድርጌ ነው የማያት፣ ቀጠናውን የምትወክል መሰባሰቢያ / Melting pot / አድርጌ ነው የማስባት። የምስራቅ አፍሪካ ዋና ከተማ እያልኩ አሽኮረምማታለሁ።
ኢኢለዚህ አንዱ ምክንያቴ ታሪክና ስልጣኔ ነው። ሁለተኛው ኃይማኖት፣ ሶስተኛው ባህላዊ መገለጫዎችና አራተኛው የተፈጥሮ ፀጋ ነው።
የአክሱም ስልጣኔ ያከተመው፣ የአክሱም የመጨረሻው ንጉስ ድልን ነዓድ በዚሁ አካባቢ ደማሞ በተባለ ተራራ ላይ ነው። 32x40 የሆነ የንጉሱ ቤተመንግስት፣ መቃብሮችና በወቅቱ ከቤተመንግስቱ ጎን አሰርቶት የነበረው ቤተክርስቲያምም ዛሬም እየተቀደሰበት ነው።
ቤተመንግስቱ የህንፃ ቅሪት ብቻ አይደለም የተወልን። ሞሰበወርቅ የተባለችው የንጉስ ድልነዓድ ልጅን የንጉሱ ባለሟል የነበረው መራ ተክለኃይማኖት ከንጉሱ ፊልም በሚወጣው መልኩ ለትዳር ይሁንታን አግኝቶ ወደላስታ የወሰዳት በኋላም እነዣንስዩምን ወልደው፣ ቅዱስ ላሊበላም Sileshi Girma ተወልዶ ዛጉዬም ስርወመንግስትም የፀናው መነሻው ከሀይቅ ነው። በዚህም የአክሱምና የዛጉዬ ስርዓቶች ሽግግር ያደረጉባት ደሴት ያደርጋታል።
ቤተክርስቲያኑና ቤተመንግስቱ ብቻ ሳይሆን በሀይቁና በአካባቢው እስከ ግሸን ደብረከርቤ የሚዘረጉ ታሪካዊና ሀይማኖታዊ አሻራዎች አሉ።
በዚሁ አካባቢ የእስልምና ሀይማኖት አሻራዎች ያሉባቸው ታላላቅ የእምነት ቦታዎችም በመኖራቸው አማኞች ለፀሎትና ጉብኝት ዛሬም ድረስ ይጎበኟቸዋል።
በቅርቡ የባቡር ፕሮጀክት ስራ ለማከናወን በነበረ ቁፋሮ የአንድ ትልቅ የእስልምና ኃይማኖ አባት መቃብር የነካ ዶዘር ምን እንደገጠመው ብዙዎች ያወሳሉ። በዘመናዊ አእምሮ የማንደፈራቸው በርካታ ተአምራትም አሉ።
በክርስትና ኃይማኖትም የመጀመርያው ኃይማኖታዊ ዩንቨርስቲ የሚባለው የሐይቅ እስጢፋኖስ አቡነ እየሱስ ሞዓ ገዳም ይገኛል። በዚህ ቦታ ከደብረ ዳሞ እስከ ደብረ ቢዘን( ኤርትራ) ከሳይንት እስከ አባጊዮርጊስ ዘጋስጫ የሚዘረጉ ታሪኮች አሉ። ቅዱሳንና ልዕለ ስብዕናዎች ፈርተውበታል።
በባህላዊ መገለጫነት ከሚጠቀሱት ውስጥ አጊያጌጥ( costume )፣ ፌስቲቫሎችና የጭፈራ አይነቶች ተጠቃሽ ናቸው። ለምሳሌ "የሚሌው አውሬ" የሚባለው የጭፈራ አይነት አጨዋወት ልዩ መገለጫ ያለው ሲሆን በጭፈራዎቹ ውስጥ ጀግንነትን፣ ውበትና አካባቢን የሚገልፁበት አሰነኛኘት አስደናቂ ነው።
የሀይቅ ልጅና የጣት ወርቅ አንድ ነው
ካመለጠ ወዲያ ፈላጊው ብዙ ነው።
ሌላው በዚህ አካባቢ ተለይቶ የሚታወቀው አሆላሎ ፌስቲቫል በውስጡ በርካታ ባህላዊ መገለጫዎችን የያዘ ነው። ፌስቲቫሉ ያለሀይማኖት ልዩነት የልጃገረዶችና ጎረምሶች ልዩ ክብረ በዓል ነው። የአደስ፣ አርቲ፣ ኩል፣ የተፈጥሮ ማጌጫዎችን የሚጠቀም በተለይ ጥር ወር ከጥምቀት ጋር እንዲሁም የአረፋ ሰሞንና የአስተርዮ ማርያም ባህላዊ ክዋኔ ነው። የዳኝነትና ልዩ ልዩ ስነስርዓቶች ያሉት ነው።
ሀይቅና አካባቢው በሁሉም አቅጣጫ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ኃይማኖታዊ መገለጫዎች ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ፀጋ የታደሉ ናቸው። ወይናደጋ የአየር ንብረት ስላላት ከሀይቅ ውሃው በተጨማሪ በ15 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የአርዲቦ ሀይቅና ጎልቦ ሀይቅ፣ የሚሌ ፍልውሃና የፈውስ ቦታዎች መገኛም ናት። በርካታ አይነት አዝዕርቶች የሚበቅሉባትም ነች።
እንዲህ ያሉ ታሪካዊ፣ ኃይማኖታዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች ላይ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ተጨምረውላታል። ከነዚህም ውስጥ
- የጭፍራ - ሀይቅ አስፋልት መንገድ
- የአዋሽ - ኮምቦልቻ- ወልድያ ባቡር መንገድ
- የሎጎ ሀይቅ ሪዞርት ይገኙበታል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች በተለይ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ልዩ ገፅታን አላብሷታል።
ሎጎ ሀይቅ ሪዞርትን እንደዕድል
ሪዞርቱ ሀይቅ እስጢፋኖስ ጋር ትይዩ ሆኖ ሆኖም በሀይቁ በኩል 1 ኪሜ ያክል ርቆ የተሰራ ከባቡርና ከጭፍራው መንገድ እንዲሁም ወደኮምቦልቻ ለመሄድ ሌላ አማራጭ መንገድ በሚኖርበት አመች ቦታ ላይ 14 ሄክታር ቦታ ላይ ያረፈ ነው።
ሪዞርቱን ድንቅ የሚያሰኘው ቀድመው የነበሩ ዛፎችንና የመሬት አቀማመጦችን ባሉበት ሁኔታ ተጠቅሞ በመርከብ ቅርፅ የተሰራ መሆኑ ነው። ጥበበኛ እጆች የሰረት ነው Nigat Zd ሊመሰገን የሚገባው ጥበበኛ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ቀደም ሲል ከሰለሞን ክብረት በፊት "ከበደ አሊ መናፈሻ" ( ፊሾ) ይባል የነበረው ቦታ ላይ ቀድሞ የነበረውን ሎጅ የሚያስታውስ ዲዛይን አለበት። ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ገፅታዎችን ጠብቆ ማልማት መቻላቸው በአጠቃላይ የፕሮጀክቱን መሪዎች በሙሉ የሚያስመሰግን ነው።
ሪዞርቱ የእርሻ፣ የመዝናኛ፣ የአገልግሎት ክፍሎች ያሉት ነው። ይህን ሪዞርት የቱሪዝም አገልግሎት መስጫ ብቻ አድርጎ ማዬት አይቻልም።
በሶስት ምክንያት
1. በታሪካዊና ተፈጥሯዊ ዳራው
2. በተሰራበት ጥራት፣ እይታና ሁኔታ
3. ተስፋው
ሪዞርቱ ራሱን የቻለ ከተማ የሚሆን ነው።
የሚጎድለው አንድ ትልቅ የፌስቲቫል/ ኹነት ማከናወኛ መሰረተ ልማት ነው። ይህ ቦታ ልዩ ልዩ የአደባባይ ዝግጅቶች ለማከናወን የሚያስችል ይሆናል። ተከታታይ ሰፋፊ ስብሰባ ማከናወኛ ማዕከልም መሆን ይችላል። ልዩ ልዩ ሁሉን አቀፍ ውድድሮችም ማከናወኛ ይሆናል። ቦታው ከተፈጥሮና ባህላዊ ፀጋው ጋር ተያይዞ ተመራጭ መዳረሻም የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው።
ቦታው በተለይ ለአሆላሎ ፌስቲቫል ማከናወኛ ሆኖ ቢሰናዳና በሪዞርቱ አስተዳዳሪነት የሀይቅ ውሃው እይታ ባለበት ቦታ ላይ ተጠርጎ ቢዘጋጅ ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ ፌስቲቫሎች ሊዘጋጁበት ይችላሉ። የወሎ ፈረሰኞች በተለይ ድሮ ቀጤ ሜዳ ላይ ይከናወን የነበረውን ፈረስ ግሊቢያ ማከናወኛም የመሆን እድል አለው።
ሌላው ሪዞርቱ የመግቢያ ክፍያ ያለው በመሆኑና ገና ስላልተዋወቀ ብዘ ሰው እየጎበኘው አይደለም። በርግጥ ብዙ ሰው ቢያጥለቀልቀው ሊበላሹ የሚችሉ ጉዳዮች ይኖራሉ።
ሆኖም የአካባቢው ሰው ልማቱን ትርጉም እንዲሰጠው የሚያችል ግብዣዎችና ዝግጅቶች በማሰናዳት ማነቃቂያም አድርጎ ማሰብ ይፈልጋል። ባለቤትነትም ተሰምቶት አብሮ እንዲሰራ ለማድረግ ልዩ ልዩ ስልቶችን መጠቀም ያስፈልጋል። ይህ እስከ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ አፋር፣ ወልድያ ድረስ የሚያካት ቢሆን።
ልማትና ዕድገት ይምሩን!
ተስፋዬ ይመር ( ወርጣዬ)
ሀምሌ 20-24 ስለጎበኘኋት ሀይቅ
ነሀሴ 3/2018