26/08/2026
የኢትዮጵያ የብቃትና ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት የ2018 አፈጻጸም ግምገማ፣የ3ዓመት ስትራተጂ እና የ2019 እቅድ
ውይይት በአዳማ ተካሄደ
የኢትዮጵያ የብቃትና ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ከነሐሴ 17 ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ሁለት ቀናት የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ፣ የሪፎርምና የፕሮጀክት አፈጻጸም ደረጃ፣ የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እንዲሁም የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድን አስመልክቶ ከሥራ መሪዎችና ከሠራተኞች ጋር ሰፊ ውይይት አደረገ።
በውይይቱ ወቅት ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን፣ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም እጅግ የላቀ በመሆኑ ለ2019 በጀት ዓመት ጠንካራ መንደርደሪያ መሆኑ በሰፊው ተነስቷል።
በግምገማው የተነሱ ዋና ዋና የትኩረት ነጥቦች
የሪፎርም ሥራዎችም ዘግይተው ተጀምረው ከቀድሞዎቹ በዌቭ አንድ ውስጥ ካሉ ተቋማት ጋር እኩል መራመዳቸው በሪፎርም ሥራው ላይ የበላይ አመራሩን ቁርጠኝነት ያሳየ ከመሆኑም በተጨማሪ በኢንስቲትዩቱ ላይ ያለውን የመፈጸም አቅም በግልጽ እንደሚያሳይ ተሳታፊዎችና አመራሩ ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከሪፎርም ሥራዎች በተጨማሪ በ 2018 በጀት ዓመት በዕቅድ የተያዙ ሥራዎችን በላቀ አፈጻጸም ማከናወኑ ወደፊት ለሚጠበቅበት ተጨማሪ ተልዕኮ በተሻለ ሁኔታ ለመፈጸም ጥሩ መነሳሳት የሚፈጥር እና እንደ መንደርደሪያ የሚሆን ነው፡፡
በሦስት ዓመት ስትራቴጂውና በ2019 ዕቅድ ላይ ሥራዎች በመነቃቃት መጀመራቸው በመላው ሠራተኛ ዘንድ ደስታን የፈጠረና ተነሳሽነትን የጨመረ መሆኑ ታይቷል፡፡
የለአዲሱ በጀት ዓመት ስኬታማ መነሻ የሚሆኑ በርካታ ተግባራት ከወዲሁ መጀመራቸው ተገልጿል። ከእነዚህም መካከል በምሥራቅ ሐረርጌ የመዋለ ሕጻናት ትምህርት ቤት ግንባታ፣ በቢሾፍቱና በአዲስ አበባ ለአካባቢው 200 ወጣቶች የተደረገ የነፃ የሥራ ፈጠራ ሥልጠና ይጠቀሳሉ።
የኢንስቲትዩቱን አዲስ ሎጎ በ200 ቲሸርቶች ላይ በማሳተም የማስተዋወቅ ሥራ መከናወኑ፣ እንዲሁም የችግኝ ተከላ እና የደም ልገሳ መርሐ ግብሮች መካሄዳቸው ተመላክቷል።
የዋና ዳይሬክተር ማጠቃለያና የቀጣይ አቅጣጫዎች
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳሬክተር አቶ ደሳለኝ ጣሰው በሰጡት ማጠቃለያ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች አንስተዋል፦
ሠራተኛውንና አመራሩን በአግባቡ በማንቀሳቀስ ለተመዘገበው ውጤት መብቃት መቻሉን ገልጸው፣ አሁን ካለው አቅም አንጻር ይበልጥ ወደፊት ተስፈንጥሮ መሥራት እንደሚቻል ያላቸውን ጽኑ እምነት አጋርተዋል።
ኢንስቲትዩቱ በአዲስ ስያሜና በአዲስ ሎጎ ቀጣዮቹን ዓመታት ራሱን በማስተዋወቅ፣ በአገሪቱ ውስጥ የብቃት ምዘናና የቅጥር ሥራዎችን በዋናነት በማከናወን የተሰጠውን ብሔራዊ ተልዕኮ በአርአያነት እንደሚወጣ ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በቀጣይ አጭር ጊዜ ውስጥ የሪፎርም ሥራዎችን በማጠናቀቅ እና የሠራተኞች ምደባ በማካሄድ ሙሉ በሙሉ በውጤት ላይ የተመሰረተ ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመው፤ መጪው ዓመት የሥራና የውጤት ዓመት እንደሚሆን በመተማመን ስብሰባው ተጠናቋል።