Free law consultancy services

Free law consultancy  services Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from Free law consultancy services, Consulting Agency, Addis Ababa.

13/03/2020

ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ የሚሰማበት ሥነ-ሥርዓት /Trial in absentia/
*******

መግቢያ
ክስ በሚሰማበት ሂደት ውስጥ ተከሳሽ የመኖር መብት እንዳለው ተግባራዊ መሆን የጀመረው በጥንታዊው የአንግሎሳክሶን ሕግ ነበር፡፡ በጥነታዊው የአንግሎሳክሶን ሀወግ የትኛውም ፍርድቤት ተከሳሽ በሌለበት ውሳኔ ሊሰጥ አይችልም ነበር፡፡ (ST. JOHN'S LAW REVIEW volum 53 pp.722)
ስለሆነም የተከሳሽ የመሰማት መብት በጥንታዊው የሕግ ሥርዓትም ተግባራዊ ነበር ማልት ይቻላል፡፡ ባሁኑ የሕግ ሥርዓትም በመርህ ደረጃ ከክስ ጀምሮ እሰክ ቅጣት ውሳኔ ድረስ ያሉት ሂደቶች ተከሳሰሁ ባለበት መከናወን አለባቸው፡፡ ተከሳሽ ችሎት በመቅረብ የቀረበበትን ክስ የመረዳትና የመከላከል መብት አለው፡፡ ሥለሆነም ተከሳሽ ችሎት መገኘቱ ክሱን በበቂ ሁኔታ ለመከላከል እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ሀገራችን ኢትዮጵያም ሆነ ሌሎች ሀገራት ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ የሚታይበትን ሥርዓት በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ህጋቸው አካተውት ይገኛሉ፡፡
ተከሳሽ በሌለበት ክስ የሚሰማበት ሥርዓት በኢትዮጵያ
በወንጀል ተጠርጥሮ የተከሰሰ ሰው ፍርድ ቤት ቀርቦ ክሱ ደርሶትና ተረድቶት የመሰማት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንሥግሥት አንቀጽ 20 ደንግጓል፡፡ የሕገመንግስቱ አንቀፅ 9(4) በደነገገው መሰረት ሌሎች ኢትዪጲያ ያፀደቀቻቸው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እነዚህ ውስጥ የሚካተቱ እና እንደ ኢትዬጲያ ሕግ እንደሚቆጠሩ ይደነግጋል፡፡
ልክ እነደ ሌሎች ሀገሮች ሁሉ በኛ ሀገርም በመርህ ደረጃ ክስ መሠማት ያለበት ተከሳሽ ባለበት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የወንጀል ክስ ሁሉ ተከሳሽ ፍርድ ቤት ካልቀረበ ታይቶ አይወሰንም ማለት አይደለም፡፡
በሕግ ተለይተው በተመለከቱ ወንጀሎች ላይ ተከሳሽ በሌለበትም ክሱን መርምሮ መወሰን ይቻላል፡፡ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ ቁጥር 160/2/ ሥር ነገሩ ሊሰማ በተቀጠረበት ቀን ተከሳሽ ካልቀረበ ወይም ለመቅረቱ በቂ ምክንያት የሚሰጥለት እንደራሴ ካልቀረበ እንዲያዝ ትዕዛዝ ፍ/ቤት እንደሚሰጥ ይደነግጋል፡፡ በዚህ ትዕዛዝ መሠረት መፈፀም ካልተቻለ ተከሳሹ በሌለበት ነገሩን ለመስማት ፍ/ቤቱ እንደሚያስብበት የዚሁ ቁጥር 160/3/ ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ ይዘት መረዳት የሚቻለው ተከሳሹ መጥርያ ደረሰውም አልደረሰውም ክሱ እነዲሰማ በተቀጠረበት እለት ካልቀረበ ክሱ በሌለበት ሊሰማ እነደሚችል ነው፡፡
በተገቢው ሁኔታ የፍርድ ቤቱ መጥርያ ለተከሳሽ መድረስ አለመድረሱ ሳይረጋገጥ ጉዳዩን በሌለበት ለመስማት መዎሰን የተከሳሽን ክሱን የመከላከል መብት አያጠብም? በሕገመንግሰቱ አንቀጽ 20 ላይ የተዘረዘሩት ማስረጃ የማቅረብ፣ ምስክሮችን የመጠየቅ፣ የሀግ አማካሪ የማግኘት የመሳሰሉት መብቶች ተከሳሽ ከቀረበ ብቻ የሚያገኛቸው አይደሉም?
የኢፌደሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 20/2 ተከሳሽ ክስ የቀረበበት መሆኑን እና የክሱን ዝርዝር ሁኔታም የመረዳት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ይህ ደግሞ ክሱ ከመሰማቱ በፊት ለከሳሽ መጥርያ ሊደርሰው እንደሚገባ መንግስት ላይ ግዴታ የሚጥል ነው፡፡ አሁን አሁን እየተለመደ የመጣውና በልምድ የዳበረው ጉዳይ ፖሊስ ለተከሳሽ መጥርያ አለማድረሱን መጥርያ ያላደረሰበት ምክንያትም ተከሳሽ ባካባቢው የሌለ መሆኑን ከገለጸ ጉዳዩ በሌለበት እነደሚታይ ይወሰናል፡፡ ፖሊስ መጥርያ ስላላደረስሰ ወይም መጥርያ ማድረስ ስላልቻለ ጉዳዩ በሌለበት ይቀጥል ማለት ለተከሳሽ ከተሰጠ የመብት ጥበቃ ጋር አንጻር እንዴት ይታያል?
ከዚህ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ጉዳይ ተከሳሽ መጥርያ ደርሶት በመጀመርያው ቀጠሮ ፍርድቤት ከቀረበ በኋላ ቀጣይ ባሉት ቀጠሮዎች ሳይቀርብ ቢቀር ምን አይነት ሥነ-ሥርዓት ልንከተል ይገባል የሚለው ነው፡፡ ተከሳሽ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ለመስማት በተቀጠረበት ቀን ወይም የዐቃቤ ሕግ ምስክር ተሰምቶ ለብይን በተቀጠረበት ቀን ወይም ተከላከል ተብሎ መከላከያ ማስረጃ ለመስማት በተቀጠረበት ቀን ባይቀርብ ልንከተለው የሚገባው ሥነ-ሥርዓት ምን ሊሆን ይችላል? ተከሳሽ ተከላከል ተብሎ የመከላከያ ማስረጃ ለመስማት በተቀጠረበት መቅረብ ካልቻለ የ ወንጀል ሥነስርኣት ህጉ ድንጋጌዎች 160 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች ተግባራዊ እንደማይሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚችሎት በአመልካች የአብክመ ፍትሕ ቢሮ እና በተጠሪ አቶ አንዷለም ገናነው መካከል የሰበር መዝገብ ቁጥር 127313 አስገዳጅነት ያለው የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ የጠቅላይ ፍርድቤቱ ሰበር ሰሚችሎት ቡውሳኔው ላይ የሚከተለውን ተታ ሰጥቷል፡፡
…………… ተጠሪ ክሱ በሚሰማበትና የከሳሽ ዓ/ሕግ ምስክሮች በሚሰሙበት ጊዜ ችሎት ቀርቦ የተከራከረ በመሆኑ እና በተከሰሰበት የሕግ ድንጋጌ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ አውቆ መከላከያ ማስረጃ ለመስማት ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ በያዘበት ቀን ሳይገኝ መቅረቱ ጉዳዩ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ (4) በወንጀል የተከሰሰሰው የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ ሲሰማ በመገኘት የዓቃቤ ሕግን ምስክሮች የመጠየቅና የመመርመር መብቱን በአግባቡ ከተጠቀመና የመከላከያ ምስክሮችንና ማስረጃ እንዲያቀርብ የተሰጠውን መብት በራሱ ፍላጎት ካልተጠቀመ እና የመከላከል መብቱን ካልተጠቀመ ዳኞች የቀረበውን ክርክርና ማስረጃ በመመዘን ፍርድ ከመስጠት የሚገድባቸው ባለመሆኑ በህጉ ለተከሳሽ ከተሰጠው የመደመጥ መብት አንፃር ተከሳሹ መብቱ በራሱ ፍላጎት ባለመጠቀሙ ጉዳዩ ተከሳሹ በሌለበት እንደሚታይ ጉዳይ ሊታይ የሚችል ባለመሆኑ ፍርድ ቤቶች የቀረበውን ጉዳይ መርምረውና መዝነው ውሳኔ ከመስጠት የሚገድባቸው ጉዳይ አይሆንም፡፡ (የሰበር መዝገብ ቁጥር 127313 ቅጽ22)
ከዚህ ውሳኔ ለመረዳት የሚቻለው ተከሳሽ የዐቃቤሕግ ማስረጃዎችን ከሞገተ በኋላ ባይቀርብ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ህጉ ድንጋጌዎች 160 እና ተከታዮቹ/provisions governing default proceeding /ተግባራዊ መሆን እንደሌለባቸው ነው፡፡
ሆኖም ግን ተከሳሽ በመጀመርያው ቀጠሮ ቀን ቀርቦ በዋሰ ከወጣ በኋላ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ለመስማት ቀጠሮ በተያዘበት ቀን ባይቀርብ ምን ሥነ-ሥርዓት እንከተላለን? የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን የመመርመርና የመጠየቅ መብቱን ስላልተጠቀመ ጉዳዩ በሌለበት የሚታይ አይደለም እንላለን?መብቱን በራሱ ግዜ ትቶታል በማለት በሌለበት ቀጥታ ጉዳዩን እናስቀጥላለን? ወይሰ የሥነስርት በህጉን 160 እና ተከታዮችን ድንጋጌዎች ተግባራዊ ዕናደርጋለን?
ተከሳሽ መጥርያ ደርሶት ፍርድቤት ካልቀረበ መብቱን በራሱ ፈቃድ እንደተዎው በመቁጠር ተከሳሽ ሳይኖር ጉዳዩ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ነገር ግን በኛ ሀገር የሕግ ስርአት ተከሳሽ መጥርያ ደርሶት በራሱ ፈቃድ ፍርደቤት ሳይቀርብ ብቻ ሳይሆን መጥርያ ሳይደርሰውም ቢቀር ጉዳዩ በሌለበት የሚታይበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡
በኛ ሀገር ሁሉም ወንጀሎች ተከሳሽ በሌለበት ይታያሉ ማለት አይደለም፡፡ አንድን የወንጀል ክስ ተከሳሽ በሌለበት መስማትና መወሰን የሚቻለው በወንጀል ሥነስርአት ሕግ ቁጥር 161/2/ መሠረት ከ12 ዓመት በማያንስ ጽኑ እሥራት የሚያሳስር ወንጀል የሠራ ወይም በቀድሞ ወ/መ/ሕግ ቁ. 354-365 በአዲሱ የወንጀል ሕግ ቁ. 343 እስከ 354 ድረስ ያሉ ወንጀሎች ፈጽሞ ጽኑ እሥራት ወይም ከ5ዐዐዐ ብር በላይ በሚያስቀጣ ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን እንዲሁም በውጭ ሀገር ጥገኛ ሆኖ ጥገኛ ያደረገው ሀገር አሳልፎ ያልሰጠው እንደሆነ ነው፡፡
ከ12 አመት በማያንስ ጽኑ እስራት ማለት ምን ማለት ነው? በወንጀል ህጉ ልዩ ክፍል የተደነገገው ወይም ተከሳሽ የተከሰሰበት ወንጀል ፍቅድ ስልጣን ውስጥ መነሻው 12 አመት መሆን አለበት? ወይስ የ12 አመት ቅጣቱ በፍቅድ ስልጣኑ ዝቅተኛውና ከፍተኛው ጣርያ መካከል መገኘት ለበት?
እነዚህ ጥያቄዎች በሕግ በለሙያዎች ዘንድ አከራካሪነታቸው እነደቀጠለ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ሁሉም የሕግ ባለሙያዎች የየራሳቸውን አቋም ሲያንጸባርቁ ማየት የተለመደ ነው፡፡
የወንጀል ሕግ ሲተረጎም ማለትም ህጉ ግልጽነት የጎደለው እንደሆነና መተርጎሙ የግድ አስፈላጊ ከሆነ ተከሳሽን በሚጠቅም መልኩ መተርጎም አለበት፡፡ ይህ ደግሞ አለማቀፋዊ ተቀባይነት ያለው የሕግ አተረጓጎም መርህ ነው፡፡ ስለሆነም የወንጀል ሥነስረአት ሕግ ቁጥር 162/2 ሲተረጎም ተከሳሹን ሊጠቅም በሚችል መልኩ መሆን አለበት፡፡ ይህ ሲበል ተከሳሽ ፍርደቤት ቀርቦ ክሱን የመከላከል መብት እንዳለው በሕገመንግሰቱና በሰብዘዊ መብቶች ሰነዶች ላይ ጥበቃ ሰጥቶታል፡፡ ስለሆነም ይህ ሕግም ሲተረጎም ተከሳሽ መብቱን መጠቀም በሚያስችል መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ የሚታይበት ስርአት ልዩ ሕግ (exception) እንጅ መርህ አይደለም፡፡ የ12 አመት እስራት ቅጣት በከፍተኛው አና በዝቅተኛው ቅጣት መካከል ከተገኘ በሌለበት ለማለት በቂ ነው የሚባል ከሆነ እጅግ በርካታ ወንጀሎች ከደንብ መተላለፍ እና ቀላል ወንጀሎች በስተቀር ተከሳሽ በሌለበት የሚታዩ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ተከሳሽ በሌለበት መስማትን ልዩ ሕግ መሆኑ ቀርቶ መርህ የሚያደርግ ነው፡፡ ልዩ ሕግ ደግሞ መተርጎም ያለበት በጠባቡ ነው፡፡
ሌላው ሕግ ሲተረጎም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የሚተረጎመው ሕግ አላማ /purpose of the law/ነው፡፡ ሕግ ሲተረጎም ህጉየቆመለትን አላማ ከግብ ለመምታት መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም በወንጀል ሥነስረአታችን ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ ሊታይ የሚችልበት ሥነስርአት ለምን የህጋቸን አካል እንደሆነ ማጤኑ ተገቢ ነው፡፡ የወንጀል ሥነስርአት ህጉን አንቀጽ 160 እና ተከታዮቹን ድንጋጌቸ ስንመለከት ተከሳሽ በሌለበት ክሱ የሚታየው ለከባድ ወንጀሎችና ተከሳሽም ሊጣልበት የሚችለውን ከባድ ቅጣት በመፍራት ከሕግ ለመሸሽ የሚደበቁ ተጠርጣሪዎችን የክስ ሂደት ከግብ ለማድረስና ተከሳሾችንም ተጠያቂ ለማድረግ የተቀመጠ ነው፡፡ ይህም ማለት በባህርያቸው ከባድ የሆኑ ወንጀሎች ላብነትም በከባድ ሁኔታ ሰው መግደል(የወንጀል ሕግ ቁጥር 539/1)፣ ህጻናት ላይ የግብረስጋ በደል መፈጸም( አንቀጽ627/1 )ተከሳሽ፣ ከ13 አመት በታች የሆኑ ህጻናት ላይ የሚፈጸም ግብረሰዶማዊነት( ወ/ህ/ቁ 631/1/ለ)፣ ጅምላ ጭፍጨፋ (የወ/ህ/ቁ 269) በሌለበት የሚታዩ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
ከዚህ በተቃራኒ 12 ዝቅተኛው የቅጣት መጠን መሆኑ አስገዳጅ አይደለም፤ የ12 አመት እስራት ቅጣት በዝቅተኛውና በከፍተኛው ቅጣት መካከል የሚገን ከሆነ ተከሣሽ በሌለበት ጉዳዩን ማየት ይቻላል የሚሉ ባለሙያዎች አሉ፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች የሚያቀርቡት የመከራከርያ ሃሳብ ተከሳሽወንጀል ፈጽም ከፍትሕ መሸሽና ማምለጥ የለበትም፤የህጉ አላማም ወንጀል ፈጽመው የሚደበቁ ግለሰቦች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኑ ማድረግ ኑው የሚል ነው፡፡
ከዚ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ክርክር ሙስና ወንጀል ዋስትና ክርክርን በተመለከተ አዋጅ ቁጥር 437/97 አንቀጽ 4/1ን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚችሎት በሰበር መዝገብ ቁጠር 63344 የሰጠው የሕግ ትርጉም ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 437/97 አንቀጽ 4/1 የሚደነግገው ከ 10 አመትና በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሰው ዋስትና የማግኘት መብት የሌለው መሆኑን ነው፡፡ ይህንን የአዋጁን ድንጋጌ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት በሰጠው የሕግ ትርጉም ላይ ተከሳሽ የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል ክስ ጣርያው ከ 10 አመት በላይ የሚያስቀጣ ከሆነ በዋስትና ወረቀት ሊለቀቅ እንደማይችል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ (በሰበር መዝገብ ቁጠር 63344 ቅጽ12)
ስለሆነም ተከሳሽበሌለበት ሊታዩ የሚገባቸውን ጉዳዮችም በዚህ ውሳኔ መሰረት የ12 አመት ጣርያ መታየት አለበት? የሰበር ውሳኔ የሕግ ትርጉም አስገዳጅነት ለተመሳሳይ የሕግና የፍሬ ነገር ጉዳዮች ብቻ መሆነ የለበትም?
የሰበር ሰሚ ችሎቱ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች አስገዳጅ የሚሆኑት በተመሳሳይ የፍሬ ነገርና የሕግ ጉዳዮችነው፡፡ የሰበር ሰሚችሎቱ በሙስና ጉዳይ ላይ ለተነሳ የዋስትና ክርክር ላይ ለደረሰበት ድምዳሜ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስን ለማየት እንደ ምክንያት ሊወሰድ አይችልም፡፡
ሌላው መነሳት የሚገባው ነጥብ በሕገመንግስታችን አንቀጽ 20 ስር በዝርዝር እንደተመለከተው ማንኛውም የተከሰሰ ሰው የቀረበበትን ክስ የመከላከል መብት አለው፡፡ ይህ መብት በሕገመንግሰቱ ገደብ የተጣለበት አይደለም፡፡ ሌሎች የሕገመንግሰቱን ድንጋጌዎች ስንመለከት የራሳቸው የሆነ ገደብ/limitation clauses/ ያላቸው ሲሆን ስለተከሰሱ ሰዎች የሚደነግገው ድንጋጌ ግን ገደብ አልባ እንደሆነ ከድንጋጌው ለመረዳት ይቻላል፡፡
በሕገመንግስቱ ገደብ ያልተጣለበትን መብት በሥነስርኣት ህጉ መገደብ ይቻላልን? በሕግ ገደብ ሊጣልበት እንደሚችል ሕገመንግሰቱ ላይ ሊደነገግ አይገባም ነበር? በተራ አዋጅ ተፈጥሮአዊ እና ሕገመንግስታዊ የሆነውን መብት መገደብ ሕገመንግስታዊ ነውን? ምናልባትም ሕገመንግስቱ የጸደቀው ከወንጀል ሥነስረዓት ህጉ በኋላ ስለሆነ ነው ለማለት ይቻላልን?
በረቂቅ ደረጃ ያለው የወንጀል ሥነስረዓት ሕግ ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሊሰጥ በሚችል መልኩ የተረቀቀ ከሆነ ተፈጥሮዓዊ የሆነውን መብት ማስከበር ይቻል ይሆናል፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክሱን ማየት በሕግ የተከለከለ ባይሆንም ጉዳዩ እንዲቀጥል ፍርድቤቶች የሚወስኑ ከሆነ የተከሳሹን መብት በማያጣብብ መልኩ መሆን አለበት፡፡ ተከሳሽ ስለመከሰሱ በማያውቅበት ሁኔታ ክሱን ማስቀጠል ተገቢ አይመስለኝም፡፡ በተለይም በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ሰፊ ያልተማረ ህዝባ ባለበትና ጋዜጣ ማንበብ ባህሉም በሌለበት እንዲሁም ሰፊ የጋዜጣ ስርጭት ሳይኖር የጋዜጣ ጥሪ በማድረግ ብቻ ተከሳሽ ካልቀረበ ጉዳዩ በሌለበት እንዲቀጥል መወሰን ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ አንጻር የፍትሕ ተቋማት የተከሳሽ መብት በክርክሩ ሂደት መከበሩን ግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው፡፡

14/02/2020

ዜግነትን መልሶ ስለማግኘት - የኢትዮጵያ ዜግነትን ያለባለሥልጣኑ (ኤጀንሲው) ውሳኔ መልሶ ማግኘት የማይቻል ስለመሆኑ
****
ሰሞኑን የአቶ ጀዋር መሐመድን ኢትዮጵያዊ ዜግነት መልሶ የማግኘት ጉዳይ በኦፌኮ እና በምርጫ ቦርድ መካከል ክርክሮችን ማስነሳቱን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየሰማን እንገኛለን፡፡ በመሆኑም የዜግነት ህጉ ኢትዮጵያዊ ዜግነት መልሶ ስለማግኘት ስላሰቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች እና ዜግነት መልሶ ማግኘት ስለሚረጋገጥበት መንገድ ያለኝን መረዳት ለማካፈል ወደድኩኝ፡፡

አቶ ጀዋር መሐመድ አስቀድመው የኢትዮጵያ ዜጋ የነበሩ በመሆናቸው ነገር ግን በሕግ ዜግነታቸውን ከቀየሩ በኋላ መልሰው ዜግነታቸው እየጠየቁ በመሆኑ ለዚህ ጉዳይ ተገቢነት ያለው ድንጋጌ ስለዜግነት የሚደነግገው የአዋጅ ቁጥር 378/96 አንቀፅ 22 እና 23/2/ሐ ነው፡፡ በዚህ መሰረትም ኢትዮጵያዊ የነበረ ነገር ግን በሕግ የሌላ ሀገር ዜግነት ያገኘ ሰው የሚከተሉትን መሰረታዊ ጉዳዮች ከተሟሉ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን መልሶ ያገኛል፤

1. አስቀድሞ ኢትዮጵያዊ የነበረ መሆኑ፤
2. ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በመምጣት መደበኛ መኖሪያውን በኢትዮጵያ ውስጥ ከመሰረተ፤
3. ይዞት የነበረውን የሌላ ሀገር ዜግነት ከተወ፤
4. ዜግነቱ እንዲመለስለት ለኢሚግሬሽን እና ስደተኞች ባለስልጣን ካመለከተ፤
5. ጥያቄው ለዜግነት ጉዳይ ኮሚቴ ቀርቦ በባለስልጣኑ ተቀባይነት ካገኘ፡፡
ከፍ ሲል በዝርዝር የተመለከቱ ጉዳዮች አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን መልሶ ለማግኘት ቅድመ ሁኔታዎች በመሆናቸው እና እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች የተሟሉ መሆን አለመሆናቸውን የማረጋገጥ እና የውሳኔ ሐሳብ የመሰጠት ስልጣን ደግሞ የዜግነት ጉዳይ ኮሚቴ በመሆኑ በአዋጁ አንቀፅ 23/3 መሰረት የዜግነት ይመለስልኝ ጥያቄው በማለስልጣኑ አማካኝነት ለኮሚቴው ቀርቦ ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ ለባልስልጣኑ አቅርቦ መወሰን ይገባዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ከፍ ሊል የተገለፁ ዝርዝር ጉዳዮች ራሳቸውን ችለው በርካታ የሕግ እና የማስረጃ ጥያቄ ሰለሚያስነሱ በአጭሩ ማብራራት አስፈላጊ ነው፡፡

አስቀድሞ ኢትዮጵያዊ መሆን

የኢትዮጵያ ዜግነት የሚገኘው በሁለት መሰረታዊ መንገዶች ሲሆን አንደኛው ከኢትዮጵያውያን ወላጆች በመወለድ የሚገኝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሕግ የሚገኝ ነው፡፡ በህጉ በግልፅ በሕግ ዜግነት ስለማግኘት በተደነገገው የህጉ ክፍል ባይካተትም አንደ ሰው ኢትዮጵያዊ ዜግነቱ ካጣ በኋላ መልሶ ጠይቆ ሲያገኝም ራሱን የቻለ ዜግነት የማግኛ መንገድ በመሆኑ አንደ ሶስተኛ ዜግነት ማግኛ መንገድ ሊቆጠር ይችላል ብሎ መከራከር ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንደ ሶስተኛ መንገድ መቆጠር አለመቆጠሩ በውጤት ደረጃ የሚያሰከትለው ህጋዊ ውጤት ስላለ እንዲሁ እንደተፈለገ የሚበየን ጉዳይ ባለመሆኑ በዚህ የፅሁፉ ክፍል አቋም ከመያዝ እቆጠባለሁ፡፡ የመጀመሪያውን መንገድ በተመለከተ አንድ ሰው ከኢትዮጵያውያን ወላጆች መወለዱን በማረጋገጥ ብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያገኛል፡፡ (እዚህ ጋር ህጉ በኢትዮጵያ ውስጥ በመወለድ ብቻ ኢትዮጵያዊነት እንደሚገኘ በስራ ላይ ያለው ሕግም ሆነ የቀደመው ሕግ ስለማይደነግግ ወላጆቹ ራሳቸው ኢትዮጵያውያን መሆናቸው በምን ይረጋገጣል የሚል ጥያቄ ቢቀርብ አጥጋቢ መልስ በህጉ ላይ አናገኝም፡፡ ምክንያቱም በህጉ መሰረት ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሚገኘው ከኢትዮጵያዊያን በመወለድ ከሆነ ወላጆቹ ኢትዮጵያውያዊነታቸውን እንዴት አገኙ የሚል የማያልቅ እና ለመመለስ አስቸጋሪ የሆነ ጥያቄ ስለሚያሰነሳ ነው) ስለዚህ ጉዳዮ የነበረን ዜግነት መልሶ የማግኘት ጉዳይ በመሆኑ አስቀድሞ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ማረጋገጥ የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ሁለተኛው እና በሕግ ዜግነትን የማግኘት ጉዳይ ዝርዝር እና በርካታ ጉዳዮች የያዘ በመሆኑ እና ለዚህኛው ፅሁፍ አላማ ጠቃሚ ባለመሆኑ አልፌዋለሁ፡፡

መደበኛ ኑሮን ኢትዮጵያ ውስጥ መመሥረት

ሌላኛ ቅድመ ሁኔታ መደበኛ ኑሮውን ኢትዮጵያ ውስጥ መመስረት ሲሆን መደበኛ ኑሮን በኢትዮጵያ ውስጥ መመስረት ማለት ደግሞ በፍትሐ-ብሄር ሕግ ቁጥር 183 ላይ በተገለፀው አግባብ ጠያቂው በኗሪነት አይነት ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖር ሐሳብ የጉዳዮቹ እና የጥቅሞቹ ዋና ስፍራ ኢትየጵያ ውስጥ ማድረግ እና ይህኑ ማረጋገጥ ነው፡፡ በኗሪነት በመኖር ሃሳብ እና ዋና ጥቅምን በኢትዮጵያ ውስጥ ማድረግ የሚለው የሕግ አነጋገር አካራካሪ እና በቀላሉ ለመወሰንም አስቸጋሪ ነው፡፡ የቃላቶቹ ጥቅልነት ህጉ ለቃላቶቹ ግልፅ የሕግ ትርጉም አለመስጠቱ ደግሞ በዚህ ዙሪያ ብቻ በርካታ የሕግ እና የማስረጃ ክርክሮች ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ጉዳዮች የፍሬ ነገር እና የሕግ ጉዳዮች በመሆናቸው ከፍ ሲል በተገለፀው አግባብ አመልካቹ መደበኛ ኗሪነቱን ለኮሚቴው በማስረጃ ማረጋገጥ ይኖርበታል በዚህ ጊዜ ታዲያ በርግጥ በመኖር ሃሳብ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣው? ዋና ጥቅሞቹስ ኢትዮጵያ ውስጥ ናቸው? ዋና ጥቅሞች የሚባሉት ምን ምን ናቸው? የሚሉት ጉዳዮች በኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ የሚሹ ጉዳዮች ናቸው፡፡

የሌላ ሐገር ዜግነትን መተው

ዜግነትን መልሶ ለማግኘት ሌለኛው ቅድመ ሁኔታ አስቀድሞ የያዘውን ዜግነት መተው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ጥምር ዜግነትን የማትፈቅድ ሀገር እንደመሆኗ የኢትዮጵያን ዜግነት መልሶ ለማግኘት የቀደመውን ዜግነቱን መተውን የሚጠይቅ በመሆኑ ዜጋ ነበር የተባለበት ሀገርን ዜግነት የተው ስለመሆኑ በቃል ከመግለፅ ባለፈ በተጨባጭ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ አስቀድሞ ዜጋ የሆነባት ሀገር ዜግነትን ለመተው ቅድመ ሁኔታ ያሰቀመጠች ከሆነ ይህው ቅድመ ሁኔታ መሟላቱ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ምን አይነት ቅድመ ሁኔታ ካላስቀመጠች ደግሞ የቀደመ ዜግነቱን መተውን ብቻ ለባለስልጣኑ በማሳወቁ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ትቷል ለማለት ዜግነቱን መተውን ባለስልጣኑ ባስቀመጠው ወይም ባዘጋጀው ቅፅ መሰረት ለባለስልጣኑ ማሳወቅን ይጠይቃል፡፡ በተለይ ደግሞ በሕግ የተጣለበት ብሄራዊ ግዴታዎች ካሉበት እነሱን ካልተወጣ ወይም በወንጀል ተከሶ ወይም ተቀጥቶ ከሆነ ከክሱ ነፃ ካልሆነ ወይም ቅጣቱን ካልፈፀመ በስተቀር መልቀቂያ አይሰጠውም በሚል የአዋጁ አንቀፅ 19/4 ይደነግጋል፡፡ ሌሎች ሀገሮችም የየራሳቸው ቅድመ ሁኔታ ያላቸው እንደ መሆኑ አንድ ሰው የቀደመ ዜግነቱን ትቷል ለማለት የጠያቂውን የቀደመ ዜግነት ሕግ ፈትሾ በዚሁ አግባብ ዜግነቱን መተውን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ የማስረጃ እና የሕግ ጉዳዮችን ስለሚያስነሳ የዜግነት ኮሚቴው መርምሮ የውሳኔ ሃሳብ የሚሰጥት ነጥብ ይሆናል፡፡

ዜግነቱ እንዲመለስለት ለባለስልጣኑ ማመልከት

ይህኛው ቅድመ ሁኔታ የጠያቂውን ለባለስልጣኑ ማመልከትን የሚጠይቅ ብቻ በመሆኑ እና ባለስልጣኑም እንዲህ አይት ጥያቄ ሲቀርብለት ጉዳዩን ለዜግንት ጉዳይ ኮሚቴ የመምራት ግዴታ ያለበት በመሆኑ ጠያቂው ማመልከቻውን ለባለስልጣኑ በማቅረቡ ብቻ የሚረጋገጥ ፍሬ ነገር በመሆኑ የሚያስነሳው የተለየ አከራካሪ ጉዳይ ላይኖር ይችላል፡፡

ባለለስልጣኑ (ኤጀንሲው) ጥያቄውን ስለመቀበሉ

የመጨረሻው ዜግነት መልሶ የማግኘት ቅድመ ሁኔታ የቀረበው ማመልካች በዜግነት ጉዳዮች ኮሚቴ ማመልከቻው ተመርምሮ ከፍ ሲል የተገለፁ ጉዳዮች በሕግ እና በማስረጃ ረገድ መሟላታቸው ሲረጋገጥ ኮሚቴው በአብላጫ ድምፅ ወይም እኩል ድምፅ ከሆነ ሰብሳቢው ድምፅ የሰጠበት አመልካቹ ዜግነቱን መልሶ ለማግኘት የሚጠበቅበትን ያሟላ ስለመሆኑ የውሳኔ ሃሳብ ለባለስልጣኑ መስጠት ይኖርበታል፡፡

ባለስልጣኑ (ኤጀንሲው) የውሳኔ ሃሳብ ሲቀርብለት ስለሚያደርገው ነገር በህጉ ያልተገለፀ በመሆኑ ጉዳዩ አካራካሪ መሆኑ የሚጠበቅ ቢሆንም ጉዳዩ በሕግ ያልተደነገገ ክፍተት በመሆኑ ወይም በመመሪያ መሸፈን ሲገባው መመሪያ ባለመውጣቱ (መመሪያውን በስንፍናየ ወይም በሚመለከተው አካል ድክመት መኖሩን ባለማወቄ የለም ብየ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ) የተፈጠረ ክፍተት ስለሚሆን ኮሚቴውም ሆነ ባለስልጣኑ የአመልካቹን መብት ወይም ህጉ ሊከላከከለው የፈለገውን አላማ ሳይጎዳ አንድ ነገር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በዚህ ፀሃፊ እምነት ኮሚቴው የሚያቀርበው የውሳኔ ሃሳብ ብቻ እንጅ ውሳኔ ባለመሆኑ በመጨረሻ የኮሚቴውን የውሳኔ ሃሳብ መነሻ በማድረግ ውሳኔ የሚሰጠው ባለስልጣኑ መሆኑን ከህጉ መንፈስ መረዳት ይቻላል፡፡ ኮሚቴው የተዋቀረው ከፍትህ ሚንስቴር በአሁኑ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ፤ በውጭ ጉዳይ፤ በፌደራል ፖሊስ እና በራሱ በባለስልጣኑ(ኤጀንሲው) በመሆኑ የኮሚቴውን የውሳኔ ሃሳብ በግልፅ ከሕግ ጋራ የሚቃረን ካልሆነ በቀር የመቀበል ግዴታ አለበት ብሎ ያምናል፡፡ የውሳኔውን ሃሳብ ከተቀበለ ደግሞ ለአመልካቹ ማመልከቻውን በመቀበል ኢትዮጵያው ዜጋ መሆኑን የሚያሳይ ማስርጃ ሊሰጠው ይገባል፡፡

ስርተፍኬት መስጠት አለመስጠትን በተመለከተ ብሎም የኮሚቴውን የውሳኔ ሃሳብ መቀበል አለመቀበልን በተመለከተ ህጉ የሚለው ነገር ባለመኖሩ በመመሪያ ክፍተቱ መሙላት እንደተጠበቀ ሆኖ መመሪያ ባይወጣም በህጉ መንፈስ እና አላማ ላይ በመመስረት ባለስልጣኑ ውሳኔ የመስጥት ግዴታ ይኖርበታል፡፡ ከፍ ሲል እንደተብራራው ኢትዮጵያዊ ዜግነትን መልሶ ማግኘት እንደተጠየቀ ወይም ቸአመነልካቹ በራሱ የሚጠበቅብኝ አሟልቻለሁ ብሎ በማሰቡ ወዲያውኑ የሚገኝ ሳይሆን ሟላቱን የማረጋገጥ ስልጣን የተሰጠው ኮሚጠየ የሚመረምረው በመሆኑ ከምርመራው በኃለሰ ማመልከቻው ተቀባይነት ያገኘ ወይም ያላገኘ መሆኑን በተመለከተ ማስረጃ መስጠጥ ደግሞ የሚጠበቅ ነው፡፡ ስለዚህ ባለስልጣኑ ጥያቄውን ከተቀበለ መቀበሉን እና ካልተቀበለም አለመቀበሉን በፅኁፍ አረጋግጦ ማሰረጃ ለአመልካቹ ወይም ማሰረጃውን ለሚፈልግ አካል የመስጠት ግዴታ ይኖርበታል፡፡ እንዲህ አይነቱ ተግባር ደግሞ ወደፊት በጉዳዩ ላይ የሚነሱ ክርከሮችን አስቀድሞ እልባት ስለሚሰጥ በተለይ ደግሞ አመልካቹ በውሳኔው ቅር ከተሰኘ መብቱን በሌላ የሕግ አግባብ እንዲያስከብር ከምርመራው በኃላ የማመልከቻውን ውጤት የሚገልፅ ማስረጃ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ ማስረጃ መስጠት አለመስጡ አካራካሪ ነው ቢባል እንኳ በማመልከቻው ላይ ውሳኔ የመሰጠት የማይታለፍ ስልጣን ግን የባለስልጣኑ እና የዜግነት ጉዳይ ኮሚቴው መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡

በመሆኑም ምርጫ ቦርድ ለባለስልጣኑ (ለኤጀንሲው) በፃፈው ደብዳቤ ምንም እንኳ ጉዳዩን መርምሬ ከአዋጁ አኳያ ውሳኔ ማሳረፍ ብችልም በማለት የገለፀው ሐረግም ሆነ ኦፌኮ በአዋጁ መሰረት አመልካቹ የሚጠበቅባቸውን ስላሟሉ ኢትዮጵያዊ ሆነዋል በማለት በደብዳቤቸው ላይ የገለፁት አነጋገር በሕግ በግለፅ ለዜግነት ኮሚቴ እና ለኤጀንሲው የተሰጠን ስልጣን መጋፋት በመሆኑ ተገቢነት የለውም።
#አቢሲኒያ ሎው

15/10/2019

አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 እና አንዳንድ ጉዳዮች
************
ከዚህ ቀደም በሀገራችን ኢትዮጵያ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይን የሚገዙ ሕጎች እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በ1955 ዓ.ም የወጣው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 210/1955፣ በ1968 ዓ.ም የወጣው የሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 64/1968፣ የሠራተኛ ጉዳይ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 85/1968፣ ስለአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ የወጣው አዋጅ ቁጥር 42/1985 እና አዋጅ ቁጥር 377/1996 የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከየካቲት 18 ቀን 1996 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ በግሉ ዘርፍ ያለውን የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትና መስተጋብር እንደ ዋነኛ ምሰሶ በመሆን ሲያስተዳድር የነበረው ሕግ አዋጅ ቁጥር 377/1996 እና የዚህ አዋጅ ማሻሻያ ሕጎቹ አዋጅ ቁጥር 466/1997 እና አዋጅ ቁጥር 494/1998 ነበሩ፡፡ እነዚህ ሕጎች ከ14 አመታት በላይ በሥራ ላይ የዋሉ በመሆናቸው አሁን ካለው የማህበረሰብ እድገት ጋር የተጣጣሙ ባለመሆናቸው የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀን ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው 4ኛ አመት የሥራ ዘመን 48ኛ መደበኛ ስብሰባው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ረቅቅ አዋጅን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ይህም ሕግ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ዓ.ም ሆኖ ነሐሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በሥራ ላይ ውሏል፡፡ ይህ አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ምን ምን ሀሳቦችን አካቶ ነው የተሻሻለው? ለሠራተኛው ምን ዓይነት ሕጋዊ ጥቅምና መብቶችን አካቷል? እንዲሁም የአሠሪ ግዴታና መብት ምን ይመስላል? የሚሉትን ጉዳዮች እና አዲሱን አዋጅ ከተሻረው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 በማነፃፀር በወፍ በረር (Bird’s Eye View) እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡
አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ከዚህ ቀደም የነበረውን አዋጅ ከነ ማሻሻያዎቹ በመሻር እና የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጄንሲ አዋጅ ቁጥር 632/2001ን በአዲሱ አዋጅ ውስጥ በማካተት ነው በሥራ ላይ የዋለው፡፡
ይህ አዲሱ አዋጅ የተለያዩ አዳዲስ ሀሳቦችን አካቶ ብቅ ብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው በተሻረው ሕግ መሠረት በቅጥር ምልመላ ሂደት (Recruitment Process) ላይ አዋጁ ተፈጻሚ እንዲሆን አልተደረገም ነበር፡፡ በአዲሱ አዋጅ የአዋጁን የተፈጻሚነት ወሰን በአሠሪና ሠራተኛ በቅጥር ላይ በተመሰረተ ግንኙነትና በቅጥር ምልመላ ሂደት ላይ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህም ማለት በአዲሱ አዋጅ አንድ ቅጥርን የሚፈጽም አካል (አሠሪ) ምልመላ ሂደቱ ግልጽና ተጠያቂነት ባለው መንገድ እንዲያካሂድና ከማንኛውም ዓይነት አድሎ (Discrimination) በፀዳ መልኩ እንዲያከናውን የሚያስገደድ ነው፡፡ ቅጥሩን የሚፈፅመው አካል ይህንን የቅጥር ሂደት ግልጽ ባልሆነና አድሎን በሚፈጥር መልኩ ምልመላውን ካከናወነና ሠራተኛው ላይ ቅሬታን ከፈጠረ ሠራተኛው (የወደፊት ተቀጣሪው) ቅሬታውን የሥራ ክርክር ጉዳይን አይቶ ለመወሰን ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት አቤቱታውን እንዲያቀርብና መፍትሄ እንዲያገኝ የሚፈቅድ ድንጋጌ ነው፡፡ ይህ የአዋጁ የተፈፃሚነት ወሰን ድንጋጌ ለአሠሪው ግዴታን የሚጥል ለሠራተኛው ደግሞ መብትን የሚያጎናፅፍ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ በአግባቡ ከተተገበረ አሁን በአገራችን ኢትዮጵያ ላይ እየታየ ላላው የሠራተኛ ቅጥር ሂደት ቅጥ ያጣ ነፃነትን ወደ ስርአት የሚያስገባ እና ለዜጎች እኩል ሥራ የመወዳደር እና የመቀጠር ዕድል መብትን (The Right of equal opportunity of jobs) የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡
አዋጁ ለአሠሪውም ሆነ ለሠራተኛው እንዳያደርጉ የከለከላቸው ህገ-ወጥ ተግባራትን ዝርዝሯል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የተከለከሉ
ድርጊት በሚለው በአንቀፅ 14 ስር ለህብረት ድርድር አስፈላጊ የሆነ መረጃ ባለማቅረብ የድርድር ጊዜ እንዲራዘም ማድረግ ወይም ሌሎች ከቅን ልቦና ውጭ የሆኑ ተግባራትን መፈፀም፣ በሥራ ቦታ ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥፋት መፈፀም፣ በሥራ ቦታ አካላዊ ጥቃት መፈፀም እና ሠራተኛን በሀይል አስገድዶ ማንኛውንም ሥራ እንዲሰራ ወይም ግዴታን እንዲያሟላ ማድረግ በአሠሪ ወይም በሥራ መሪ ከተፈፀሙ የአሠሪ ህገ-ወጥ ተግባራት ተደርገው ተቆጥረዋል፡፡ በተመሳሳይ አንቀፅ ስር በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል ወይም ለመገልገል መሞከር፣ በህብረት ስምምነት ከተፈቀደው ውጭ ወይም አሠሪው ሳይፈቅድ በሥራ ሰዓት ስብሰባ ማካሄድ፣ በሥራ ቦታ ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት መፈፀም እና በሥራ ቦታ አካላዊ ጥቃት መፈፀም ለሠራተኛው የተከለከሉ ድርጊቶች ናቸው በሚል እንደ አዲስ የተካተቱ ሀሳቦች ናቸው፡፡
የሥራ ስንብት ክፍያን በተመለከተ የተሻረው አዋጅና ማሻሻያ ድንጋጌዎቹ ላይ የሰፈሩት ምክንያቶች ሲሟሉ ክፍያ የሚፈፀም የነበረ ሲሆን በአዲሱ አዋጅ አንቀፅ 39 (1) (መ) ስር አዲስ ሀሳብ አካቷል፡፡ ይህም ሀሳብ በአሠሪ ወይም በሥራ መሪ ወሲባዊ ጥቃት ወይም ትንኮሳ የተፈፀመበት እንደሆነ ወይም ድርጊቱ በሌላ ሠራተኛ እንደተፈፀመ ሪፖርት ተደርጎለት አሠሪው ተገቢውን እርምጃ ባለመውሰዱ ሠራተኛው የሥራ ውሉን ያቋረጠ እንደሆነ ከአሠሪው የሥራ ስንብት ክፍያ የማግኘት መብት እንዳለው የሚደነግግ ነው፡፡ የሥራ ስንብት ክፍያ ዋነኛው ዓላማ አንድ ሠራተኛ ከሥራ ሲሠናበት ችግር ላይ እንዳይወድቅ ራሱን እንዲያቋቁም ለመርዳት ወይም በሥራ ላይ የቆየ ሠራተኛ አዲስ ሥራ ፍለጋ ላይ እያለ ሊደርስበት የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቀነስ ነው፡፡ ይህ የክፍያ ዓይነት በተለምዶ የሥራ ማፈላለጊያ በመባል ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ወሲባዊ ጥቃት ወይም ትንኮሳ የደረሰበት ሠራተኛ በሥራ ላይ የሚደርስበትን አካላዊም ሆነ ሞራላዊ በደል ችሎ የሚሰራበት ጊዜ እንዲያበቃ የሕግ ከለላ በሀገሪቱ እንዳለ ማሳያ ድንጋጌ ነው፡፡
ሌላኛው የዚህ አዋጅ ማሻሻያ የሙከራ ጊዜ ቅጥርን የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ የሙከራ ጊዜ ቅጥር ማለት አንድ ሰው በሥራ ውሉ መሠረት ሊመደብበት ለታቀደው ቦታ ተስማሚ መሆኑን ለመመዘን በተዋዋዮቹ ወገኖች (በአሠሪው እና በሠራተኛው) ስምምነት በፅሁፍ የሚደረግ የቅጥር ዓይነት ሲሆን ይህ የሙከራ ጊዜ በተሻረው አዋጅ ከአርባ አምስት (45) ተከታታይ ቀናት ለማይበልጥ ጊዜ የሚደረግ የነበረ ቢሆንም በዚህ በአዲሱ አዋጅ ግን የሙከራ ጊዜው ሠራተኛው ሥራ ከጀመረበት ቀን አንስቶ ከ60 (ስልሳ) የሥራ ቀናት (ከሁለት ወራት) ሊበልጥ አይችልም በማለት የሙከራ ጊዜ ቀናቱ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ ይህ የህጉ ድንጋጌ ለአሠሪው ሰፋ ያለ መብት የሰጠና አሠሪው ሠራተኛውን ሊመድብበት ላቀደበት የሥራ መደብ ብቁ መሆኑን በቂ ጊዜ በመስጠት እንዲመዝነው የሚረዳው ነው፡፡ በሌላ በኩል ሠራተኛው ቋሚ ከመሆን እና የሥራ ዋስትናን ቶሎ ከማረጋገጥ ጉጉት አንጻር ሲታይ ይህ ድንጋጌ ሠራተኛው ላይ ቅሬታ ያስነሳል የሚል እምነት አለኝ ፡፡ ይህ ቢሆንም ሠራተኛው ለተጠቀሰው ጊዜ ቋሚ አለመሆኑን አውቆ ሥራውን አክብሮ በትጋት እንዲሰራ እና የሥራ ባህሉን (Work Habit) እንዲያዳብር ይረዳል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡
አንድ ሠራተኛ የሥራ ውል ስምምነት ከፈፀመና ሥራውን መሥራት ከጀመረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የተለያዩ ፈቃዶችን የማግኘት ህገ መንግስታዊ መብት አለው፡፡ ይህም መብቱ በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 ተረጋግጧል፡፡ ከእነዚህ የፍቃድ አይነቶች ውስጥ ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ሁለቱን ብቻ እናያለን፡፡ አንደኛው የአመት ፈቃድን የሚመለከት ሲሆን ለመጀመሪው የአንድ አመት አገልግሎት የሚሰጠው የፈቃድ መጠን አሥራ ስድስት (16) የሥራ ቀናት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህም በተሻረው የአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ ላይ ከነበረው ለተመሳሳይ አንድ አመት አገልግሎት ይሰጥ ከነበረው የአሥራ አራት (14) የሥራ ቀናት የዓመት እረፍት የሁለት (2) ተጨማሪ የሥራ ቀናት ዕድገት እንዲያሳይ ተደርጓል፡፡ ከአንድ አመት በላይ ለሆነ አገልግሎት በአሥራ ስድስት ቀናት ላይ ለእያንዳንዱ ተጨማሪ ሁለት የአገልግሎት ዓመት አንድ የሥራ ቀን እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በጠቅላላው ሲታይ ለሠራተኛው የሚሰጥ አመት ፈቃድ መጠን አንፃራዊ መሻሻል አሳይቷል ለማለት ይቻላል፡፡
ሁለተኛው የፈቃድ ዓይነት ልዩ ፍቃድ ሆኖ ለቤተሰብ ጉዳይ የሚሰጥ ፈቃድ ሲሆን ከዚህ ቀደም ያልነበረው በዚህ በአዲሱ አዋጅ የተካተተው ባል የሆነ ሠራተኛ (Married Employee) የትዳር ጓደኛ ስትወልድ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ከክፍያ ጋር ፈቃድ እንዲያገኝ ሆኗል፡፡ ይህም ድንጋጌ የባል ሰራተኞችን ጥያቄ የመለሰ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ይህ (Paternity Leave) በሌላው አለም በበለፀጉትና በተለይ በስካንዲኒቪያን (Scandinivian) ሀገሮች የተለመደ አሰራር ሲሆን በሀገራችንም ይህ የፈቃድ ዓይነት ማህበራዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛ ለቅድመ ወሊድ የአንድ ወር እንዲሁም ለድህረ ወሊድ የሶስት ወር በጠቅላላው የአራት ወር የወሊድ ፈቃድ ዕረፍት የማግኘት መብትን አረጋግጦላታል፡፡ በዚህ አግባብ ከተሻረው አዋጅ ጋር ሲነፃፀር የአንድ ወር የወሊድ ፈቃድ ዕረፍት ጭማሪ እንዲኖረው ተደርጓ ተሻሽሏል፡፡ ይህም ድንጋጌ የሴት ሰራተኞችን ጤና ለመጠበቅ ከፍተኛ የሆነ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
በአሠሪና ሠራተኛ የሥራ ውል ግንኙነት ላይ አለመግባባት የሚፈጥረው ዋናው ጉዳይ አሠሪው የሠራተኛውን የሥራ ውል ያለማስጠንቀቂያ የሚያቋርጥበት ጉዳይ ነው፡፡ መደበኛ ፍ/ቤቶችም በአብዛኛው የሥራ ክርክር ጉዳዩችን በሥራ ክርክር ችሎቶች ሲያዩ እንደጭብጥነት የሚይዙት ጉዳይ አሠሪው የሠራተኛውን ውል ያቋረጠው በሕጋዊ መንገድ ነው ወይስ አይደለም የሚል ነው ፡፡ ለዚህ ጭብጥ ደግሞ መፍትሄ ለመስጠት ፍ/ቤቶች የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ይሰማሉ፡፡
አሠሪው የሠራተኛውን የሥራ ውል ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ በአዋጅ ቁጥር 377/76 አንቀፅ 27(1) ላይ በተመለከቱት ምክንያቶች እና በህብረት ስምምነት ላይ በተገለፁት የሥራ ውል ለማቋረጥ ያስችላሉ ተብለው የተወሰኑ ጥፋቶችን ሠራተኛው ፈፅሞ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ ከነዚህም ጥፋቶች ውስጥ በአንቀፅ 27 (1) (ሀ) እና (ለ) የተጠቀሱት፡- ሀ) ያለበቂ ምክንያት እና ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው (warning) በመደጋገም የሥራ ሰዓት አለመክበር፣ እና ለ) በመደዳው ለአምስት የሥራ ቀናት ወይም በአንድ ወር ውስጥ በጠቅላላው ለ10 የሥራ ቀናት ወይም በአንድ አመት ውስጥ በጠቅላላው ለ30 የሥራ ቀናት ያለ በቂ ምክንያት ከሥራ መቅረት የሚሉት ይገኙበታል፤ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ጥፋቶች በአዲሱ አሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ እንደሚከተለው ተሻሽለዋል፡፡
አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ አንቀፅ 27 (1) (ሀ) ላይ የተመለከተው አንደኛው ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል ማቋረጫ መንገድ ሠራተኛው የሥራ ሰዓት ለማክበር የማይችልባቸው ሁኔታዎች ተብለው በህብረት ስምምት፣ በሥራ ደንብ ወይም በሥራ ውሉ ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ውጭ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው በስድስት ወር ውስጥ በጠቅላላው ለስምንት ጊዜ የሥራ ሰዓት አለማክበር ነው፡፡ ይህ የሕግ ድንጋጌ ከአዋጅ 377/96 አንፃር ሲታይ ሠራተኛው የሥራ ሰዓት ባለማክበሩ የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ በፅሁፍ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን በመደጋገም የሥራ ሰዓት አለማክበር የሚለው ደግሞ በስድስት ወር ውስጥ
ለስምንት ጊዜ የሥራ ሰዓት አለማክበር በሚል ግልፅ በሆነ መልኩ የጊዜ ገደብ እንዲበጅለት ተደርጓል፡፡
ይህ ድንጋጌ ለአሠሪው በህብረት ስምምነት፣ በሥራ ደንብ ወይም በሥራ ውሉ ከሚዘረዘሩት ወይም ከተዘረዘሩት የሥራ ሰዓት አለማክበር ምክንያቶች ውጭ ሠራተኛው ወደ ሥራ ገበታው አርፍዶ ቢገባ ወይም ከተቀመጠው የሥራ ሰዓት ቀድሞ ቢወጣ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ለስምንት ጊዜ የሥራ ሰዓቱን ካላከበረ አሠሪው የሥራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ እንዲያቋርጥ ይፈቅድለታል፡፡ ድንጋጌው አሠሪዎች አሁን በሀገራችን ያለውን የትራንስፖርት ችግር ከግምት ውስጥ አስገብተው በሀላፊነት መንፈስ ሠራተኛውን ካላስተዳደሩና ካልመሩ በሠራተኛው በኩል እንደ የሥራ ሰዓት አለማክበሪያ ምክንያት ተደጋግሞ ሊጠቀስ የሚችል የትራንስፖርት ችግር በመሆኑ የጊዜ ገደብ መቀመጡ በሠራተኛው ላይ የሥራ ዋስትና (Job Security) አደጋ ውስጥ የሚጥል ነው፡፡
በአንቀፅ 27 (1) (ለ) ስር የተደነገገው ሌላኛው ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውልን ማቋረጫ ምክንያት በዚህ አዋጅ ከተመለከቱት እረፍቶች እና ልዩ ልዩ ፈቃዶች ውጭ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው በስድስት ወር ውስጥ ለአምስት ቀናት ከሥራ መቅረት
ነው፡፡ ይህ አንቀፅ ከበፊቱ አዋጅ አንፃር ሲቃኝ አሠሪው በቀላሉ የሠራተኛን የሥራ ውል እንዲያቋርጥ የሚያስችል ነው፡፡ መሰረታዊው ጥያቄ “ከሥራ መቅረት” ማለት ምን ማለት ነው የሚለው ጥያቄ ሲሆን ይህም ማለት አንድ ሠራተኛ ሊሰራ በተስማማውና በአሠሪው በተመደበበት የሥራ ቦታ ላይ በተቀመጠው መደበኛ የሥራ ሰዓት እና ጊዜ አለመገኘት ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ አሠሪዎች (ድርጅቶች) የሥራ ሰዓቱን ያላከበረ ( ያረፈደ ወይም ቀድሞ የወጣን) ሠራተኛን ከሥራ እንደቀረ (Absent) እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩና የሚተገብሩ በመሆናቸው አንድ ሠራተኛ ከሥራ ለቀረባቸው ጊዜያት ደሞዙን ከመቁረጥ አልያም ሌላ ቀላል አስተዳደራዊ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የመጨረሻውንና ከባድ የሚባለውን አስተዳደራዊ እርምጃ ማለትም የሥራ ውልን እንዲያቋርጡ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሠራተኛውን የሥራ ዋስትና (Job Security) አደጋ ላይ የሚጥልና በአሠሪና ሠራተኛ መካከል የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማምጣት አዳጋች የሚያደርግና በዚህ ድንጋጌ ምክንያት ሊፈጠር በሚችለው አለመግባባት ፍ/ቤቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ጫና ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በሌላ በኩል ሥራው ላይ የሚያለምጥ፣ የሚለግም ወይም የሚያሾፍ በጠቅላላው ሥራውን የማያከብር ሠራተኛን አሠሪው የመሸከም ግዴታ እንደሌለበት የሚያሳይ ድንጋጌ ነው፡፡
በአጠቃላይ አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ለሠራተኛው አንዳንድ መብቶችን ያስከበረ፣ ለአሠሪው ደግሞ የሥራ ውልን ለማቋረጥ ሰፊ መብትን ያጎናፀፈ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ መካከልም የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማስፈን ታስቦ የወጣ አዋጅ ስለመሆኑ ከአዋጁ መግቢያ (Preamble) ላይ በግልፅ መረዳት ይቻላል፡፡ አዋጁን በማስፈፀም ሂደት ላይ ወደፊት ለሚፈጠሩ ችግሮች በሶስትዬሽ መድረክ ማለትም በሠራተኛው፣ በአሠሪውና በመንግስት በኩል በሚደረግ ቅርብ ውይይት ይፈታሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተጨማሪም ይህንን ሕግ ለመተርጎም ህገ-መንግስታዊ ስልጣን የተሰጣቸው ፍ/ቤቶችም ህጉ የወጣበትን ዓላማና ሊደርስበት ላሰበው ግብ ህጉን በአግባቡ በመተርጎም ለሠራተኛው ቅሬታ አፋጣኝ መፍትሄ በመስጠት ለእውነትና ለፍትህ ይቆማሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ መልካም የሥራ ዘመን ይሁንልን!!!
ምንጭ ፦አቢሲኒያ ሎው

26/05/2019

አጭር ስነስርአት (summary Procedures)
==============================
ከፍትሓብሔር ሥነ-ሥርዓት ህጋችን ላይ አቤቱታ ለማቅረብ የሚንጠቀሚባቸው ሶስት መንገዶች አሉ፡፡ እናዚህም 1ኛ/ በደበኛ ሥነ-ሥርዓት 2ኛ/ አጭር ሥነ-ሥርዓት 3ኛ/ የተፋጠነ ሥነ-ሥርዓት ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ 2ኛውን የክስ አቀራረብ እንመለከታለን፡፡
1. ከፍ/ብ/ስ/ስ/ቁ/ 284 እስከ 292 በተደነገገው መሠረት ይፈፀማል፡፡
2. በዚህ ሥርዓት መሠረት ክስ ልቀርብ የሚችለው በቁ. 284 ሥር በተዘረዘሩ ጉዲዮች ብቻ ነው፡፡ ምንጩ ግልፅ ውል፣ የሃዋላ ሰነድ፣ ቼክ፣ የተስፋ ሰነድ ወይም ቀላል ውል የሆነ ልኩ የታወቀ ገንዘብን የሚመለከት ክስ በሆነ ግዜ፤
3. ማመልከቻው በመኃላ ቃል ተደግፎ መቅረብ አለበት (284(ለ))፡፡ የመኃላ ቃለ ተከሳሹ ለነገሩ ምንም ዓይነት መከላከያ እንደሌለው ከሳሽ የሚያምን መሆኑን መግለፅ አለበት፡፡
4. ፍ/ቤቱ ማመልከቻውን ከተቀበለ በኃላ ለተከሳሹ መጥሪያ እንድደርሰው ያዛል (ቁ. 285(1)) ፡፡
5. ተከሳሹ ቀርቦ ለመከላከል እንድፈቀድለት ፍ/ቤቱን ጠይቆ ካላስፈቀደ በቀር መከላከያ ልያቀርብ አይችልም (ቁ. 285(1))፡፡
6. ተከሳሹ ቀርቦ ለመከላከል እንድፈቀድለት ለፍ/ቤቱ ካላመለከተ ወዲያው ፍርድ ይሰጣል(ቁ. 285(2))፡፡
7. ለመከላከል ፈቃድ እንድሰጥ የሚቀርበው ማመልከቻ በቁ. 286 መሠረት በመኃላ ቃል ተደግፎ መቅረብ አለበት፡፡
8. ተከሳሹ ለመከላከል እንድፈቀድለት ያቀረበው ማመልከቻ ተቀባይነት ካጣ ወዲያው ለከሳሹ ይፈረዳል (ቁ. 287)፡፡
9.ማመልከቻው ተቀባይነት ካገኘ ግን ተከሳሹ መከላከያ እንድያቀርብ ይፈቀድለታል፡፡ ክርክሩም የሚመራው ፍ/ቤቱ በሚሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ወይም እንደመደበኛው ክስ በቀጥታ ልሆን ይችላል(ቁ. 290 እና 291)፡፡
10. ፍርድ ከተሰጠ በኃላ ለተከሳሹ የተላከው መጥሪያ በአግባቡ ያልደረሰው ከሆነ ፍ/ቤቱ ፍርድ ከመፈፀም እንድቆይ በማድረግ ተከሳሹ ቀርቦ እንድከላከልና ስለ ጉዳዩም አፈፃፀም ተገቢ መስሎ የታየውን ትዕዛዝ ለመስጠት ይችላል(ቁ.292)፡፡

25/04/2019

ተጠርጣሪን ፍርድ ቤት በ48 ሰዓት አለማቅረብ ወንጀል መሆኑን ያውቃሉ?

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ እስካሁን ድረስ በራሱ አነሳሽነት ክስ ለመመስረት ጥረት ሲያደርግ ግን አይታይም።

ህጉ ምን ይላል ?
________________________________

ሰላም እንዴት ናችሁ ውድ የገጻችን ተከታታዮች ወንጀል በሚፈጸምበት ጊዜ አንድን ተጠርጣሪ በህግ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ፍርድቤት በ48 ሰዓት ቀርቦ በቁጥጥር የዋለበትን ምክኒያት የማወቅ መብቱ እንደሚጠበቅ በአገራችን የህግ ማእቀፍ ላይ ተካቷል፡፡

ለዛሬ ስለጉዳዩ ከህግ ማብራሪያዎች ጋር እያጣቀስን ማብራሪያ እንሰጥዎታለን በጥሞና ያንብቡ።

በወንጀል ድርጊት በመፈፀም ተጠርጥረው በፖሊስ ወይም በህግ አስከባሪ አካላት የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ በአቅርቢያ በሚገኝ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብታቸው በሚጣስበት ጊዜ በህግ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብታቸውን ማስከበር የሚችሉበት ስርዓት አለ፡፡ እንዲሁም ይህንን በፈፀመው ህግ አስከባሪ ወይም ፖሊስ ላይ የሚያስከትለው ተጠያቂነትም አለ፡፡

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት በአንቀጽ 19 (4) በግልፅ እንደተደነገገው ተጠርጣሪዎችን የያዛቸው የፖሊስ መኮንን ወይም የህግ አስከባሪ በጊዜ ገደቡ ፍርድ ቤት አቅርቦ የተያዙበትን ምክንያት ካላስረዳ የተያዙ ሰዎች ለፍርድ ቤት የአካል ነፃነታቸውን እንዲያስከብርላቸው የመጠየቅ ሊጣስ የማይችል መብት አላቸው፡፡

ይህ የተያዙ ሰዎች በጊዜ ገደብ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ሲቀር የሚኖረው መብት የአካል ነፃነትን ማስከበር /Habeas Corpus/ የሚመለከት ሲሆን የሚቀርብበት ስርዓትም በፍትሐብሔር ስነ-ስርዓት ህግ በክፍል 7 ተገድዶ የመያዝን ህጋዊነት ለማጣራት ስለሚፈፀም ስነ ሰርዓት ርእስ ስር ከአንቀፅ 177 – 179 በተመለከተው መሰረት ነው፡፡

በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህጉ አንቀጽ 177 ላይ በወንጀል ህግ የተደነገገውን መሰረት በማድረግ ሳይወሰንበት ወይም ሳይፈርድበትና ማናቸውንም ሌላ ትዕዛዝ ሳይሰጥ የተያዘ ወይም የታሰረ ሰው ፍርድ ቤት እንዲቀርብ በማመልከቻ የተገደደው ሰው እራሱ ወይም ማናቸውም ሌላ ሰዉ በቃላ መሃላ ማመልከቻ ማቅረብ ይችላል፡፡

የአካል ነፃ ለመውጣት የሚቀርብ አቤቱታን የመመልከት ስልጣን የፌደራል ፍርድ ቤቶች በአዋጅ ቁጥር 25/1988 በአንቀጽ 5(10)የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ለክልሎች በህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/2/ በተሰጣቸዉ የዉክልና ስልጣን መሰረት ጉዳዩ የሚመለከተው በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይሆናል፡፡

ማመልከቻው የቀረበለት ፍርድ ቤት የአቤቱታውን እውነተኛነት ለማጣራት በቁጥጥር ስር የዋለው ፖሊስ ወይም የህግ አስከባሪ ተጠርጣሪውን በአካል ፍርድ ቤት ይዞት እንዲቀርብ እና እንዲያስረዳ በማድረግ ጉዳዩን ይመረምራል (ፍ/ስ/ስ/ህ ቁጥር 178)፡፡

በፍትሐብሄር ስነ ስርዓት ህጉ አንቀጽ 179 (2) መሰረት የተያዘው ሰው በህገ ወጥ መሆኑን ካረጋገጠ ወዲያዉኑ ከእስር እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ይህ ትዕዛዝም ያለቅድመ ሁኔታ መፈፀም እንዳለበት በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ መጨረሻ በፓራግራፍ ላይ ተገልፆል፡፡

ነገሩ ባጠራጠረ ጊዜ የተያዘ ሰው በተፈለገ ጊዜ እንዲቀርብ የሚያስችል ዋስ ጠርቶ እንዲለቀቅ ይህም የገንዘብ ወይም የሰዉ ዋስ እንዲጠራ ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህግ ከአንቀጽ 179 (2) ተደንግጓል፡፡

ሆኖም ግን አንድ ፖሊስ ወይም የህግ አስከባሪ ከአርባ ስምንት ሠዓት በላይ ተጠርጣሪውን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማስሩ ምክንያት በግለሰብ መብት እንዲሁም በህዝብና በመንግስት ሰላም፣ ደህንነትና ጥቅም ላይ ከባድ ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ የተያዘው ተጠርጣሪ በሥነ ሥርዓት ግድፈት ምክንያት ቢለቀቅ የሚደርሰውን ጉዳት ማመዛዘን የሚገባ በመሆኑ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 19 (4) ላይ ፍትሕ እንዳያጓድል ሁኔታው የሚጠይቅ ከሆነ ፍርድ ቤቱ የተያዘው ሰው በጥበቃ ሥር እንዲቆይ ለማዘዝ ወይም ምርመራ በማካሄድ ተጨማሪ ጊዜ ሲጠየቅ አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ ሊፈቅድ እንደሚችል ተቀምጦል፡፡

ይህንን ሲወስንም ፖሊስ ምርመራ ወይም የህግ አስከባሪ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ምርመራውን አጣርተው የተያዘው ሰው በተቻለ ፍጥነት መደበኛ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ያለውን መብት የሚያስከብር መሆን እንዳለበት በዚሁ አንቀጽ ላይ ተደንግጓል፡፡

የወንጀል ተጠያቂነትበተመለከተ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 423 እንተደነገገው ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ በህግ ከተመለከተው ውጭ ወይም ህጋዊ ስርዓትና ጥንቃቄ ሳይከተል ሌላውን ሰው በመያዝ ወይም በማሰር ነፃነቱን ያሳጣው እንደሆነ ከአስር ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና መቀጮ ይቀጣል፡፡

ሰለዚህ ፖሊስ ወይም የህግ አስከባሪ በቁጥጥር ስር የዋለውን ተጠርጣሪ በህግ በተወሰነው 48 ሰዓት ውስጥ በአቅራቢያ የሚገኝ ፍርድ ቤት ያለውን ስልጣን በመጠቀም ባያቀርበው የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል ነው፡፡

ውድ አንባቢያን ለዛሬ ያዘጋጀንላችሁን ጥንቅር በዚሁ አበቃን በቀጣይ በሌላ አርዕስት እስክንገናኝ መልካም ጊዜን ተመኘን ሰላም፡፡

13/03/2019

በፍርድ የማይዳኙ ጉዳዮችን (justiciability)
====================================
በፍርድ የማይዳኙ ጉዳዮችን (justiciability) በተመለከተ በፍርድ ቤቶች ዘንድ ያለው አረዳድ የፅንሰ ሀሳቡን ትክክለኛ ይዘት አያንጸባርቅም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 51790 ቅጽ 12 [1] በሰፈረው የሚከተለው ማብራሪያ መሰረት በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ ማለት ከፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ውጪ የሆነ ጉዳይ ማለት ነው፡፡ ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት ያለው ስለመሆኑ የኢ.ፌ.ዲ. ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 37/1/ ድንጋጌ በግልጽ የሚያሳየው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚሁ የሕገ መንግስት ድንጋጌ መገንዘብ የሚቻለው ደግሞ ፍርድ ቤቶች አንድን ጉዳይ (አቤቱታ) ተቀብለው ውሳኔ መስጠት የሚችለት ዳኝነት የተጠየቀበት ጉዳይ በሕግ ለሌላ አካል ያልተሰጠ ጉዳይ በሚሆንበት ጊዜ እንደሆነ መሆኑን ነው፡፡ በሕግ ተለይተው በአስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲቋጩ በተባሉ ጉዳዮች ላይ መደበኛ ፍርድ ቤት የመዳኘት የስረ ነገር ስልጣን ስለሌለው በሕጉ መሰረት ለአንድ አስተዳደር አካል ቀርቦ አስተዳደራዊ ውሳኔ የተሰጠበትን ጉዳይ ወይም ለአስተዳደር መቅረብ የሚገባውን ጉዳይ ፍርድ ቤት ሊያስተናግደውም ሆነ አከራክሮ ውሳኔ ሊሰጥበት አይችልም፡፡ ይኸው አቋም ጉዳዩ በፍርድ እንደሚዳኝ ድምዳሜ ላይ በተደረሰባቸው ውሳኔዎች ላይም ተፈጻሚ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ በሰ/መ/ቁ. 80202 ቅጽ 15 [2] በተሰጠ የህግ ትርጉም መሰረት ግንባታ በጊዜው አለመጠናቀቁን ወይም የገንዘብ አቅም ማነስን አሊያም በሌላ ምክንያት አስተዳደሩ በሚወስዳቸው የኪራይ (lease) ይዞታ ማቋረጥ እርምጃዎች ላይ ባለይዞታው ቅሬታ ሲያድርበት ጉዳዩን ለማየት በሕግ በግልጽ የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው ሌላ አካል እስከሌለ ድረስ ጉዳዩ በፍርድ ሊወሰን ይገባዋል፡፡ በእርግጥ በአረዳድ ረገድ የሚታየው ብዥታ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራትም ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ በአውስትራሊያ የአስተዳደር ህግ በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይን አስመልክቶ ያለው ግንዛቤ በሚከተሉት ሀሳቦች ዙሪያ ይዋልላል፡፡ ጉዳዩ ከፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን ውጪ ነው፡፡ ጉዳዩ በፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን ክልል ውስጥ ቢወድቅም ሕዝባዊ የስልጣን መገልገልን አይመለከትም፡፡ ፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን አለው ነገር፡፡ ግን ጉዳዩን ለመፍታት ተቋማዊ ብቃት የለውም፡፡ ፍርድ ቤቱ ስልጣንም ብቃትም አለው፡፡ ሆኖም ጉዳዩን በዳኝነት ለመጨረስ ህገ መንግስታዊ ተገቢነት የለውም፡፡ ጉዳዩ ገና ያልበሰለ ነው፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤት ጣልቃ አይገባበትም፡፡ ፍርድ ቤቱ ህጋዊነትን ከማጣራት አልፎ የጉዳዩን ይዘት (merit) ሳይፈትሽ በአጣሪ ዳኝነት ሊመረምር የሚችልበት በቂ ምክንያት (grounds of judicial review) የለም፡፡ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለመወሰን የሚያስችል ቅቡልነት ያለው ማስረጃ ማግኘት ወይም ማስቀረብ አልቻለም፡፡ [3] ከዝርዝሮቹ መካከል በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ በሚገባ የተገለጸው በ3ኛ እና 4ኛ ላይ ነው፡፡ የዳኝነት ስልጣን ጉዳዩን ለመዳኘት ካለመቻል የሚመነጭ ባህርይ ሳይሆን በፍርድ ቤቶች ስልጣን ላይ በህግ የተቀመጠ ገደብ ነው፡፡ አንድን ጉዳይ እንዲያይ ጥያቄ የቀረበለት ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ወይም የይግባኝ ስልጣኑ ለሌላ አካል ከተሰጠ የስረ-ነገር የዳኝነት ስልጣን ያጣል፡፡ በህግ ጉዳይ ላይ ብቻ በከፊል ስልጣን አግኝቶ ከሆነም በፍሬ ነገር ረገድ የሚደርስበት ድምዳሜ የስልጣኑን ልክ ያልፋል፡፡ ወጣም ወረደ ግን የዳኝነት ስልጣን አለመኖር ራሱን ችሎ የቆመ ሀሳብ በመሆኑ ከጉዳዩ ለመዳኘት አለመቻል ጋር ሊቀላቀል አይገባውም፡፡ በዝርዝሩ 2ኛ ላይ የተጠቀሰው ‘ህዝባዊ ስልጣን’ ጉዳዩ የአስተዳደር ህግ ጥያቁ እንደማያስነሳ ያመለክታል፡፡ ሁለት የተለያየ የአስተዳር ህግ እና የፍትሐ ብሔር ስርዓት ላለቸው አገራት ይህ ነጥብ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ አቤቱታ የቀረበበት ጉዳይ መነሻው መንግስት እንደ ግለሰብ ያሉትን መብቶች ተጠቅሞ የፈጸመው ድርጊት ከሆነ በአጣሪ ዳኝነት አይስተናገድም፡፡ ከውል ውጪ ኃላፊነት ወይም ከውል በሚመነጭ ግዴታ መንግስት ተጠያቂነት ካለበት ጉዳዩ ከመነሻው የአጣሪ ዳኝነት ጥያቄ አያስነሳም፡፡ የጉዳዩ አለመብሰል እና የይዘት ጥያቄ የአስተዳደር ህግ ወሰንን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች አስተዳደሩ ገና ውሳኔ ላይ ያልደሰበትን ጉዳይ የማያዩት ህጋዊነቱን የሚመዝኑበት በቂ ምክንያት ስለማያገኙ ነው፡፡ የውሳኔው ይዘት ማለትም ትክክለኛነቱ እንዲሁ ከህግ አንጻር የሚጣራበት መሰረት የለም፡፡ በመጨረሻም ማስረጃ ሊገኝ አለመቻሉ ወይም እንዲቀርብ የታዘዘው ማስረጃ ሚስጥራዊ ተብሎ በመፈረጁ የተነሳ ፍርድ ቤቱ እልባት ለመስጠት አለመቻሉ ጉዳዩ ከመነሻው በፍርድ እንደማይዳኝ አያመለከትም፡፡ በዝርዝሮቹ 3ኛ እና 4ኛ ላይ የሰፈረውን ሀሳብ በከፊል በሚያቅፍ መልኩ በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ ማለት ምን እንደሆነ ትክክለኛ ትርጓሜ የተሰጠው በሰ/መ/ቁ. 42150 ቅጽ 12 [4] ከአብላጫው ድምጽ በተለየው ሀሳብ ላይ ነው፡፡ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡ አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ነው የሚባለው የክርክሩ መሠረታዊ ባህሪ በፍርድ ለመጨረስ አመች የሆነ ሲሆንና ተከራካሪዎቹ የሚከራከሩበት ጉዳይ ንድፈ ሃሳባዊ ወይም ምናባዊ የፈጠራ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ሣይሆን በነባራዊ ዕውነታና ተጨባጭ በሆነ ችግር ወይም ክስተት መሠረት ያደረገ የመብት ወይም የሃላፊነት ጥያቄ ሲሆን እንደሆነ ነው፡፡ በአብላጫው ድምጽ ላይ ግን ፅንሰ ሀሳቡ ከክስ ምክንያት ጋር ተምታቷል፡፡ በአብላጫው አስተያየት አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ነው ሊባል የሚችለው፤ …የክርክሩ መሠረት በሕግ ጥበቃ ያገኘ መብት ወይም ግዴታ ሲሆን ወይም ለመብቱ ወይም ግዴታው መሠረት የሚሆን ውል መኖሩ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ‘ያለመዳኘት’ ከጉዳዩ ባህርይ እንጂ ከተከራካሪ ወገኖች መብት አይመነጭም፡፡ ከባህርያቱ አንጻር ሲቃኝ አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊዳኝ አይችልም የሚባለው አንድም ከፍርድ ቤቱ ተቋማዊ ብቃት አንጻር በፍርድ ለማለቅ አመቺ ባለመሆኑ አሊያም ከህግ መንግስታዊው የስልጣን ክፍፍል አንጻር ዳኝነት መስጠት ተገቢ ስለማይሆን ነው፡፡ ከተቋማዊ ብቃት አንጻር አንዳንድ ጉዳዮች የብዙ ወገኖች ተጻራሪና ተነጻጻሪ ጥቅም ያዘሉ (polycentric) በመሆናቸው በባህርያቸው በፍርድ ቤት ሙግት ለማለቅ አያመቹም ወይም አይመቹም፡፡ እንደ ፒተር ኬን ገለጻ፤ A polycentric issue is one which involves a large number of interlocking and interacting interests and considerations. [5] የፍርድ ቤት የሙግት ስርዓት ተጻራሪ የጥቅም ግጭት ያለባቸውን ጉዳዮች በወጉ ለመፍታት አያመችም፡፡ ፍርድ ቤቶች የሚከተሉት ጥብቅ የሙግት ስነ ስርዓት ብሎም የሚመደብላቸው ውስን የገንዘብና የሰው ኃይል ቴክኒካልና ሳይንሳዊ መረጃና ማስረጃ ለማሰባሰብ ሆነ ተጻራሪ ጥቅሞችን በማቻቻል ዘላቂ መፍትሔ ለመቀየስ አያስችልም፡፡ በአጭር አነጋገር እነዚህን ጉዳዮች ለመዳኘት ተቋማዊ ብቃታቸው አይፈቅድላቸውም፡፡ በፍርድ ለመዳኘት ህገ መንግታዊ ተገቢነት የሌላቸው ጉዳዮች በፈራጆች ውሳኔ ሳይሆን በተመራጮችና ፖለቲከኞች ጥበብና ብልሀት ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጣቸው የፖሊሲ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ዳኞች ተሿሚዎች እንጂ ተመራጮች አይደሉም፡፡ ለመራጩ ህዝብም ቀጥተኛ ተጠያቂነት የለባቸውም፡፡ ስለሆነም አገራዊ ፋይዳ ባላቸው የፖሊሲ ጥያቄዎች ላይ ዳኝነት ለመስጠት የሚያስችል ህገ መንግስታዊ ስልጣን የላቸውም፡፡ ለምሳሌ የውጭ ጉዳይ፣ መከላከያ እንዲሁም የብሔራዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ዳኝነት መስጠት ከፍርድ ቤቶች ህገ መንግስታዊ ሚና አንጻር ተገቢነት የለውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዓለም ዓቀፍ ስምምነት መዋዋል፣ የሚኒስትሮች ሹመትና ሽረት፣ ፓርላማ የመበተን ስልጣን፣ ለህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረግ፣ መንግስት በአንድ አካባቢ መሰረት ልማት ለመዘርጋት የሚደርስበት ውሳኔ በአጠቃላይ የመንግስት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ውሳኔ ፖለቲካዊ ተገቢነት መዝኖ ፍርድ ማሳረፍ የዳኝነት አካሉ ሚና አይደለም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በዳኝነት ማየት የስልጣን ክፍፍል መርህን ይጥሳል፡፡ በውሳኔ ሰጪው ፈቃደ ስልጣን የሚወሰኑ ጉዳዮች እንዲሁ በፍርድ ለማለቅ አመቺ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ የስራ ፈቃድ ወይም የግንባታ ቦታ ጥያቄዎች ተገቢነት በፍርድ ቤት ጭብጥ ተይዞበት የሚወሰን አይደለም፡፡ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶችና ሁኔታዎች አንድ ጉዳይ በፍርድ የማይዳኘው የክሱ ምክንያት በይዘቱ ዳኝነት ለመስጠት አመቺ ሳይሆን እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ተገቢነት ሳይኖረው ሲቀር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለክርክሩ መነሻ የሆነው አስተዳደራዊ ውሳኔ ወይም ድርጊት ‘የጀርባ ምክንያት’ ፖለቲካዊ ነክ መሆኑ ፍርድ ቤቶች አከራክረው ውሳኔ ከመስጠት አያግዳቸውም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 48217 [6] አመልካች በህጋዊ መንገድ ተመርተው የሰሩት ቤት በ1ኛ ተጠሪ ተነጥቀው ለ2ኛ ተጠሪ እንደተሰጠባቸው በመግለጽ እንዲመለስላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የቤቱ አሰጣጥ መነሻ አመልካች በጦርነት ምክንያት ቤትና ንብረት ስለወደመባቸው ለተፈናቃዮች ምትክ ቦታና ገንዘብ እንዲሰጥ መንግስት ባስተላለፈው ውሳኔ ነው፡፡ አመልካች በዚሁ መሰረት የራሳቸውን ገንዘብ ጨምረው ቤቱን ሰርተው ከጨረሱ በኋላ ‘ኤርትራዊ ነሽ’ በሚል ምክንያት 1ኛ ተጠሪ ቤታቸውን ነጥቆ ለ2ኛ ተጠሪ ሰጥቷል፡፡ ክሱ በቀረበበት ፍርድ ቤት 1ኛ ተጠሪ የቤቱ አሰጣጥ ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን በመጥቀስ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዳይዳኝ የመጀሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያነሳ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ሆኖም ክርክሩን በይግባኝና በሰበር ያዩት ፍርድ ቤቶች ጉዳዩ በአስተዳደር እንጂ በፍርድ እንደማያልቅ አቋም በመያዛቸው የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሸሯል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰ/ሰ/ ችሎት በበኩሉ በድርጊቱ ይዘት ላይ በማተኮር የአመልካች የክስ ‘አለአግባብ ቤቴን ተነጠቅኩኝ’ በሚል የቀረበ እንደሆነ በመጠቆም ጉዳዩ በፍርድ ሊያልቅ እንደሚችል ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ የአገራችን ፍርድ ቤቶች በፍርድ አይዳኙም በሚል በራቸውን የሚዘጉባቸው ጉዳዮች አብዛኞቹ የተቋማዊ ብቃት ሆነ የፖሊሲ ጥያቄ አያስነሱም፡፡ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሞባቸው በሰበር ችሎት ከታረሙ አንዳንድ ውሳኔዎች ለመረዳት እንደሚቻለው በግለሰብና በመንግስት መካከል የሚነሱ አስተዳደራዊ ክርክሮችን ‘በፍርድ የማይዳኙት’ ውስጥ የመፈረጅ አዝማሚያ በፍርድ ቤቶቻችን ዘንድ ሰፍኖ ይታያል፡፡ በሰ/መ/ቁ. 75414 ቅጽ 14[7] የባለቤትነት ምስክር ወረቀት እንዲሰረዝ የቀረበ አቤቱታ ‘በፍርድ አይዳኝም’ በሚል በስር ፍርድ ቤቶች ውድቅ የተደረገ ቢሆንም የሰበር ችሎት የሚከተለውን ሐተታ በማስፈር ሽሮታል፡፡ የንብረት ባለሀብትነት መብት ከአንዱ ወገን ወደ ሌላው እንዴት መተላለፍ እንዳለበት በህጉ የተመለከተውን ደንብና ሥርዓት ሳይከተል ስለሆነ የንብረቱ ባለሀብት ስለመሆኑ የህግ ግምት መውሰጃ የሆነው የባለቤትነት ምስክር ወረቀት ቀሪ ነው፤ ሊሰረዝ ይገባል በማለት የሚቀርብ ጥያቄ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1195፣ 1196 እና በፍ/ብ/ ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33/2/ እና 231/1/ሀ/ በተመለከቱት ድንጋጌዎች መሠረት በፍ/ቤት ሊረጋገጥ የሚችል የዳኝነት ጥያቄ እንጂ ጉዳዩ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ጉዳይ አይደለም ለማለት የሚያበቃ አይደለም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 97948 ቅጽ 17[8] የቀበሌ ቤት የተከራይነት መብት ተከራይ ሲሞት ለወራሾቹ ወይም ለቤተሰቦቹ የሚተላለፍ መሆን ያለመሆኑ በፍ/ብ/ሕጉ ስለማይንቀሳቀስ ንብረት የኪራይ ውል የተመለከቱትን ድንጋጌዎች፣ የቀበሌ ቤትን የኪራይ መብትና ግዴታ ለመግዛት በሚመለከተው አካል በወጡት ደንብና መመሪያዎች አንጻር ታይቶ በፍርድ ቤት ዳኝነት የሚሰጥበት እንጂ የቤቱ አስተዳዳሪ የሆነ ቀበሌ ለፈለገው ሰው የሚያከራየው ነው ተብሎ በፍርድ እንዳያልቅ የሚደረግ ጉዳይ እንዳልሆነ የህግ ትርጉም ተሰጥቶበታል፡፡
Source:- Abyssinia Law

Address

Addis Ababa
A

Telephone

+251911029885

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Free law consultancy services posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share