05/05/2024
ፈቲወ ፈተውክዎ ለዝንቱ ፋሲካ እብላዕ ምስሌክሙ።
ሉቃስ ፳፪÷፲፭
ፋሲካን ስናስታውስ ሁልጊዜ በብዙዎቻችን አዕምሮ የሚመጡ ብዙ መልካም ነገሮች ቢኖሩም በዋናነት ግን ለትንሳኤው ግብአት የሆኑ፣
ፍርደ ገምድል ገዥዎች፣
በግፍ ያለፍትሕ የተቀጣ ተበዳይ፣
በወዳጃቸው ብዙ በደል እና ግፍ ተስፋ የቆረጡ ወዳጆች፣
የሚሆነውን በርቀት እያዩ የተሻለውን ለመከተል የሚፈልጉ ወላዋዮች፣
ፍትሐዊነቱን ሳያመዛዝኑ የታዘዙትን እንደወረደ የሚተገብሩ ፈርጣማ ወታደሮች፣
ለፍትሕ እና ርትዕ ግድ የማይሰጣቸው ከግፉአን በሚሰበሰብ ግብር የደለቡ መርህአልባ የቄሳር ባለሟሎች፣
ለእውነት ዋጋ የሚሰጡ ባለጉዳዮች፣ እና
ሕይወታቸውን በሰቆቃ የሚመሩ የመርህ ሰዎች ጎልትው ይታያሉ።
ይህንንም ልማጠየቅ ወንጌላዊው ሉቃስ የመጨረሻዎችን ሳምንታት( ህማማቱን) የተረከበት መንገድ ልብን የሚሰብር ነው። በምዕራፍ ፳፪ ላይ የተገለጹ ሁነቶች የሚያሳዩትም
አንድን ንጹሕ ሰው ለመግደል ሰብብ ፍለጋ፣
ለዚህ ምችሁ ሁኔታን የመፈጥር በገንዘብ የሚገዛ ከሀዲ የራስ ወገን፣
ፋሲካን ለመደገስ እንግዳ ማረፊያ ያለው መልካም ሰው ፍለጋ፣
በስጋ ወደሙ ላይ መሰረት ያደረገ የሐዲስ ኪዳን ምስረታ፣
አንዱ አንዱን አለማመን እና እርስ በርስ እኔ እሻል ፉክክር፣
ወዳጅነትን ባረከሰ መልኩ አሳልፎ መስጠት፣
ሦስት ጊዜ ክህደት፣
በችግር ወቅት ተግቶ ከመጸለይ ይልቅ አዚም ውስጥ መውደቅ፣
በሌላ ወገን ደግሞ የደም ነጠብጣብ ከግንባር እስኪወርድ ድረስ የጭንቅ ጸሎት ማቅረብ፣
የአባትን ፈቃድ ለመፈጸም የሚደረግ ቁርጥ ውሳኔ፣
የመላእክት ማበረታቻ፣
እንደ ወንበዴ መቆጠር፣
የተገዙ ሰይፎች ተግባራት ሲገለጽ፣
የተቆረጠ አካል ደህና ሲሆን፣
ዶሮው ሲጮህ፣
ዓይኑን ሸፍነው የመታውን እንዲገምት ሲጠየቅ፣
"ክርስቶስ አንተ ነህ?
የእግዚአብሔር ልጅ ነህ? ለሚሉ ሁለት ግዙፍ ጥያቄዎች መልስ ሲሰጥ፣
ለሚደረገው ግፍ ሁሉ ምስክር እንደማያስፈልግ ሲነገር ነው።
እንደኔ መረዳት ለክርስቶስ ተሸፍኖ ከመመታት እና ማን እንደመታው ከመጠየቅ በላይ ህመሙ ጽኑዕ የሚሆነው በይሁዳ ታቅፎ የውሸት መሳሙ ይመስለኛል።
ለውትሮው በግርምት ይሚተረከው የይሁዳ ታሪክ ዛሬ ዛሬ የውሸት የሚያቅፍ፣ በሀሰት የሚደግፍ በመብዛቱ ምክንያት የትኛው ትክክለኛ ወዳጅ፣ የትኞቹ ደግሞ ከእውነት ጎን የቆሙ ደጋፊዎች መሆናአቸውን ለመለየት እነኳ የምንቸገርበት ጊዜ ላይ ደርሰን ይሁዳን የሚያስንቁ፣ በዋጋ ሳይሆን በብላሽ የሚሸጡ ወዳጆች አፍርተናል።
እርስ በእርስ ከመደጋገፍ ይልቅ ጊዜያችንን በምነቃቀፍ የምናጠፋ የብኩን ትውልድ ምሳሌዎች ሆነን ዘመን እንደምቃብር ድንጋይ ክብዶብናል።
ምንም እንኳ በበደል ውስጥ ብንሆንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም ከኛ ጋር ፋሲካውን ማድረግ ይፈልጋል።
መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ያንን ግዙፍ የመቃብር ድንጋይ ፈንቅሎ የተነሳው ክርስቶስ በደላችንን እና መከራችንን ከላያችን ላይ ገፎ የሰላም ብስራት ከትንሳኤው ጋር ያሰማን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ይቆየን!!!
መ/ር በቃሉ ቢምረው