08/02/2024
ወንበር ላይ ያለ ሰው ማመን ያቆምኩበት አጋጣሚ!
ከዓመታት በፊት አንድ ወዳጃችን ታሞ አማኑኤል ይዘነው ሄድን ! በስርዓት እንግዳ መቀበያው ውስጥ ተቀምጠን እሱም በስርዓት ህመሙ በፈቀደለት መጠን የማይያያዙ ነገሮች እያወራ ነበር። ድንገት ግን ወንበር እያነሳ መወርወር ጀመረ! በተለይ እኔን ካልገደልኩ አለ!
ዘልየ ወንበር ላይ ቆምኩ (ደመነፍስ መሰለኝ) ከውጭ ሰዎች ሲንጫጩ እሱም ከእኔ ፊት ለፊት ያለ ወንበር ላይ ወጥቶ ቆመ! ታማሚም ወንበር ላይ አስታማሚም ወንበር ላይ ! ነርሶችና ሁለት ሰዎች ተሯሩጠው ገቡ! አንዱ የተቀባበለ ስሪንጅ ነገር ይዟል ....ወደኔ በቀስታ እየተጠጋ " ማንም አይነካህም አይዞህ ውረድ ወንድሜ " እያለ እንደህፃን ያባብለኛል! ሊወጋኝ!
"እንዴ እኔ አይደለሁም እሱ ነው...ይዘነው መጥተን ...ከዛ ድንገት እቃ ሲያነሳ ...ከዛ ወንበር ሲያነሳ ...ከዛ " አልኩ በፍርሃት በተረበሸና በተኮላተፈ ድምፅ! ደግሞ ስናገር በጣም ነበር የምጮኸው! ወደሱ ሲዞሩ ከእኔ በጣም በተረጋጋና ለስለስ ባለ ድምፅ ወደእኔ እየጠቆመ "እሱ ነው ዶክተርየ፤ እባካችሁ እርዱት " አለ። ሁሉም አምነውት ነበር ....ሌላ ጓደኛችን መሃል ገብቶ ባያተርፈኝ .... ከዛ ቀን በኋላ ነው በድምፅም በምስልም ከመድረክ የጠፋሁት! እና ወንበር ላይ ያሉ ሰዎችንም አላምንም! Alex abrham