30/07/2025
በአላህ ቤቶች ላይ የሚፈፀሙ ተከታታይና የማያባሩ ጥቃቶች በአስቸኳይ ይቁም!
ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች የጋራ ፎረም የተሰጠ መግለጫ
ሐምሌ 21 ቀን 2017: አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የጋራ ፎረም በተለያዩ ጊዜያትና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በአላህ ቤቶች በሆኑት መስጂዶች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ተደጋጋሚና ስልታዊ ጥቃት እጅግ እያሳሰበው ይገኛል። መስጂድ ሙስሊሞች ግንባራቸውን ለአላህ የሚያስጠጉበት፣ የመንፈስ እርጋታን የሚያገኙበትና የማህበረሰብ አንድነታቸውን የሚያፀኑበት የተቀደሰ ስፍራ ሆኖ ሳለ በመንግስት ዉስጥ የተሸሸጉ አንዳንድ አካላት ድርጊት እጅግ አሳሳቢና የሀገርን ሰላም የሚያናጋ አደገኛ አካሄድ ነው። የዚህ ስልታዊ ጥቃት ሰለባ የሆነው በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ መልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ ውስጥ ህጋዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት የነበረው አቡዘር መስጂድ ሐምሌ 19 ቀን 2017 በሌሊት ጨለማ ተገን ተደርጎ በህገ-ወጥ መንገድ መፍረሱ ነው።
ይህ መስጂድ ለአካባቢው ማህበረሰብ ብቸኛ የመስገጃ ስፍራ ከመሆኑም በላይ፣ ከ260 በላይ ህፃናት የዲን ትምህርት እየቀሰሙበት ትውልድ የሚታነፅበት የመድረሳ ማዕከል ነበር። ከዚህም በላይ ይህ የጥፋት ድርጊት የተፈፀመው ማህበረሰቡ ለመጅሊስ አመራሮች ምርጫ በሚንቀሳቀስበትና በመስጂዱም የምርጫ ሂደት እየተከናወነ በነበረበት ወሳኝ ወቅት መሆኑ፣ የድርጊቱን ክብደትና ዓላማ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል። ይህ ድርጊት ከዚህ ቀደም በዚሁ ከተማ ብቻ ከ31 በላይ መስጂዶች ከፈረሱበት አሳዛኝ ታሪክ የማይነጣጠል የማህበረሰባችንን ትዕግስት የሚፈታተን ነው።
በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር የተቀደሰ የአላህ ቤት ሲደፈር ይህ የመጀመሪያው አይደለም፤ ዛሬም ይህን የማፍረስ ፍላጎት ባለመግታት በክልሉ ሸገር ከተማ የሚገኙ በወቅፍ የተሰጡ መስጂዶችን የማፍረስ ዝግጅት መኖሩ በልዩ ልዩ መልኩ እየተገለፀ ይገኛል። ይህ ተግባር በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በመስጂዶች ላይ እየተፈፀመ ያለ የስልታዊ ዘመቻ አካል መሆኑን እንገነዘባለን። በአዲስ አበባ ከተማ በተባረክ መስጂድ ላይ በሌሊት የተፈፀመው ተመሳሳይ የፈረሳ ድርጊትና መስጂዱን የማፍረስ ዛሬም ያለው ፍላጎት፣ በአፍንጮ በር አቅሳ መስጂድ ላይ የተሞከረው ህገ ወጥ ተግባር፣ በካዛንቺስ ባንቢስ ከፍ ብሎ የሚገኘው አሊፍ መስጂድን የማፍረስ ዕቅድ እንዲሁም ሌሎች በርካታ መስጂዶችን ለማፍረስ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች ጥቃቱ በአጋጣሚ ሳይሆን ታቅዶ የሚፈፀም፣ ሙስሊሙን ዒላማ ያደረገ ዘመቻ አካል መሆኑን በግልፅ ያመላክታሉ።
ህዝበ ሙስሊሙ አደራ የሰጣቸው የኦሮሚያ ክልል መጅሊስና የሸገር ከተማ መጅሊስ አመራሮች ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸውና በዝምታ ማለፋቸው፣ ዝምታቸው ከወንጀሉ ተባባሪነት የማይተናነስ ታሪካዊ ስህተት መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል።
ህዝበ ሙስሊሙ በሀገር ደረጃ እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎች ላይ በሰፊው እየተሳተፈና ለውጤታማነቱ ትብብር እያደረገ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ የመንግስት አካላት ለሃይማኖት ተቋማቱ ጥበቃና ምቹ ሁኔታን መፍጠር ሲገባቸው፣ የማፍረስ እርምጃ ውስጥ መገኘታቸው የህዝቡን ቀናኢነት ወደኋላ የሚጎትት ነው። በተለይ የሸገር ከተማ ከንቲባ አቶ ተሾመ አዱኛ በሚመሩት አስተዳደር ውስጥ ከዚህ ቀደም "ከአሁን በኋላ መስጂዶች አይፈርሱም" ተብሎ የተሰጠው ህዝባዊ ቃል ተቀልብሶ ጨለማ ተገን በማድረግ ህጋዊ መስጂድን ማፍረስ ህዝብን ከመንግስት ጋር በቀጥታ የሚያጋጭና በቀጣይ በሚኖሩ ግንኙነቶች እምነትን የሚሸረሽር አደገኛ ተግባር ነው። ይህ ድርጊት ከዚህ በኋላ በማህበረሰቡና በአስተዳደሩ መካከል በሚደረጉ ስምምነቶች ላይ ከባድ የጥርጣሬ ጥላ የሚያጠላና ተዓማኒነትን የሚያሳጣ ይሆናል። የመስጂድ ፈረሳን እንደ ቀላል የአስተዳደር እርምጃ መመልከት አይቻልም፤ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ድርጊት የሰው ህይወት እንደጠፋ፣ በርካታ ሙስሊሞች ፈረሳውን በመቃወም ሂደት ውስጥ የአካል ጉዳተኛ እንደሆኑ መዘንጋት የለበትም።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የጋራ ፎረም ይህንን አጥፊ ድርጊት በፅኑ እያወገዘ የሚመለከተው የመጅሊስ መዋቅር እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት ይህንን በመስጂዶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያስቆሙና ወንጀለኞችን ለህግ እንዲያቀርቡ አጥብቆ ይጠይቃል። የክልሉ መጅሊስ አመራሮችም የህዝቡን አደራ እንዲወጡና ግልፅና ጠንካራ አቋም እንዲይዙ እናሳስባለን። በመጨረሻም መላው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች፣ በተለይም የመስጂድ አስተዳደሮች የአላህን ቤቶች ከጥቃት ለመጠበቅ ከምንጊዜውም በላይ በላቀ ንቃትና ጥንቃቄ ቀን ከሌሊት እንድትጠብቁ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የአላህን ቤቶች መጠበቅ የሁላችንም ሃላፊነት ነው!
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የጋራ ፎረም
ሐምሌ 21 ቀን 2017
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ