ኢቅራዕ TUBE

ኢቅራዕ TUBE all of standard almunium technics call know

እዚህ ምስል ላይ የምትመለከቱት የጋላክሲዎች ህብረ-ስብስብ (a group of galaxy clusters) ሲሆን የኛው ፍኖተ ሀሊብም (milky way)  የሚገኝበት Laniakea superclu...
14/08/2023

እዚህ ምስል ላይ የምትመለከቱት የጋላክሲዎች ህብረ-ስብስብ (a group of galaxy clusters) ሲሆን የኛው ፍኖተ ሀሊብም (milky way) የሚገኝበት Laniakea superclusters እዚሁ ስብስብ ውስጥ ይገኛል።

የኛውን ፍኖተ ሀሊብ እና ሌሎች ከ100,000 በላይ ጋላክሲዎችን አጠቃልሎ የያዘው ህብረ-ስብስብ/Laniakea superclusters በዚህ ምስል ላይ በቀይ ተቀልሞ ይገኛል። አንድ ጋላክሲ ስርዐተ-ፀሀይን ጨምሮ በቢልየኖች የሚቆጠሩ ፍኖቶችን በውስጡ እንደሚይዝ በአንድ ፅሁፍ ላይ ተመልክተናል።

ይህ በንዲህ እንዳለ የሰው ልጅ ይህን መሰል ከ 10 ሚልየን በላይ superclusters አፅናፈ ሰማዩ ላይ መመልከት እንደቻለ በጥናቶች ተረጋግጧል።

ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ሊመለከተው የተሳነው ሌላ በቢልየን የሚቆጠር እና ህልቆ መሳፍርት ህብረ-ስብስብ superclusters እንደሚኖር ይገመታል።

የአላህ ባሮች ሆይ! ከዚህ ሁሉ ውስብስብ ስፍራዎች መካከል ለእይታ በማትገባዋ በትንሿ ምድር ውስጥ ትኖራላችሁ፣ ተጋብታችሁ ትዋለዳላችሁ፣ ‹‹ያለ እኔ ማን አለ!›› ትላላችሁ፣ እርስ በርስ ትጎዳዳላችሁ፣ ጦርነት ታካሂዳላችሁ፣ ተሿሿማላችሁ፣ ታሴራላችሁ። ግና በአላህ እይታ ቅንጣቶች ናችሁ።

Sefwan Sheik Ahmedin

ጋዜጠኛ :- ያንተ አርአያ ማነው??ሳዲዩ: - የኔ አርአያ የተከበሩት ነብዩ ﷺ ናቸው ♥♥♥
14/08/2023

ጋዜጠኛ :- ያንተ አርአያ ማነው??
ሳዲዩ: - የኔ አርአያ የተከበሩት ነብዩ ﷺ ናቸው ♥♥♥

ረሱል ሰዐወ ከባልደረቦቻቸው ጋር መዲና ከከተሙ 6ኛ አመታቸውን ይዘዋል። የትውልድ ቀዬአቸው የናፈቃቸው ሰሀባዎች ያለ መታከት ለ6 አመታት መዲና ላይ አሳልፈዋል።ድንገት ወደ መካ ለዑምራ እንጓ...
01/12/2022

ረሱል ሰዐወ ከባልደረቦቻቸው ጋር መዲና ከከተሙ 6ኛ አመታቸውን ይዘዋል። የትውልድ ቀዬአቸው የናፈቃቸው ሰሀባዎች ያለ መታከት ለ6 አመታት መዲና ላይ አሳልፈዋል።

ድንገት ወደ መካ ለዑምራ እንጓዝ የሚል ትዕዛዝ ከወደ ነብያቸው የመጣላቸው 1500 ሰሀባዎች ያለ አንዳች ትጥቅ የጉዞ ጥሪውን ተቀብለው ጉዞ ጀመሩ።

የሙስሊሞቹን ጉዞ መጀመር የሰሙ የመጋ አጋርያንም ባለ በሌለ አቅማቸው ተጠቅመው የመካን ምድር በዚህ አመት ሙስሊሞች እንዳይረግጧት ለመከልከል ከውሳኔ ደረሱ።

ረሱል ሰዐወ ሰሀባዎቻቸውን ይዘው ጋራ ተራራውን አቆራርጠው ልክ ሁደይቢያ የተባለብ ስፍራ ላይ ሲደርሱ የእረፍት ድንኳናቸውን እዝያው ተከሉ።

የመካ መሳፍንቶችም የድርድር መልዕክተኞቻቸውን እያፈራረቁ ወደ ረሱል ሰዐወ ይልኩ ጀመር። በመጨረሻም የድርድሩን መቋጫ ይዞ ሱሓይል የተሠኘ ግለሰብ ከረሱል ሰዐወ ፊት ብቅ አለ።

የስምምነት ወረቀቱ ተዘጋጅቷል።
‹‹በዚህኛ አመት መካን ሳትገቧት ወደ መዲና በዚህ ትመለሳላችሁ። ለዚህኛው አመት የነየታችሁትን ዑምራም ለቀጣይ አመት ታሸጋግራላችሁ።

ለቀጣይ አመት ዑምራ ስትመጡ ምንም አይነት ጦር ሳትታጠቁ የምትመጡ ሲሆን መካን በገባችሁ በ3ኛው ቀን ለቃችሁ የምትወጡ ይሆናል።

ከመካ እስልምናን ተቀብሎ ወደ መዲና የሚሰደድ ወገናችንን የምትመልሱ ሲሆን ከመዲና ወደ ወደኛ የሚመለሱ ሙስሊሞችን ግን እኛ የማንመልስ ይሆናል።››

የስምምነት ፊርማው በረሱል ሰዐወ ስምምነት ፀደቀ። ያን ሁሉ በረሀ አቆራርጠው የመጡ ሰሀባዎች መካን ሳይገቡ በመመለሳቸው ንዴት ውስጣቸውን ያበግነው ጀመር።

ዑመር፦‹‹አባ በክር ሆይ!››
አቡ በክር፦‹‹አቤት››
ዑመር፦‹‹ሙሀመድ የአላህ መልዕክተኛ አይደሉምን?››
አቡ በክር፦‹‹ናቸው››
ዑመር፦‹‹እኛስ ሙስሊሞች አይደለንምን?››
አቡ በክር፦‹‹ነን››
ዑመር፦‹‹ታድያ በሀይማኖታችን ለምንድነው ምናጎበድድላቸው?››

አቡ በክር፦‹‹ዑመር ሆይ! የነቢን ትዕዛዝ ዝም ብለህ ተቀበል፤ እሳቸው የአላህ መልዕክተኛ ናቸው።››
ዑመር፦‹‹እኔም መልዕክተኝነታቸውን እመሰክራለሁ።››

ዑመር በሙሽሪኮቹ ኢ ፍትሀዊ የስምምነት ሰነድ ንዴቱን መቆጣጠር ተስኖት አቡ በክርን ትቶ ወደ ረሱል ሰዐወ ሄደ።

ዑመር፦‹‹አንቱ ነብይ ሆይ! እርሶ የአላህ መልዕክተኛ ነዎት አይደል?››
ረሱል ሰዐወ፦‹‹አዎን ነኝ››
ዑመር፦‹‹እኛስ ሙስሊሞች ነን አይደል?››
ረሱል ሰዐወ፦‹‹አዎን ናችሁ››
ዑመር፦‹‹የመካ ሰዎችስ አጋርያን አይደሉምን?››
ረሱል ሰዐወ፦‹‹ናቸው።››
ዑመር፦‹‹ታድያ በሀይማኖታችን ለምንድነው ምናጎበድድላቸው?››

ረሱል፦ዑመር፦‹‹እኔ የአላህ ባርያው እና መልዕክተኛው ስሆን ከትዕዛዙም መውጣት አይቻለኝም፤ እሱም አሳልፎ አይሰጠኝም።››

ዑመር ተፀፀት። በዝያች ቀን ከነቢ ሰዐወ ስላደረጋት የቃላት ልውውጥ ማካካሻ ይሆን ዘንድ ምፅዋት እያወጣ አላህን መማፀን ጀመረ።

ነቢም ሰዐወ ባልደረቦቻቸውን ይዘው ወደ መጡበት መዲና ተመለሱ።

ብዙም ሳይቆይ ነበር የስምምነቱን መስፈር የሚያፈርስ አንድ ክስተት ድንገት የተከሰተው። አንድ ወጣት ከመካ ሸሽቶ ወደ መዲና ብቅ አለ፤ ክስተቱን ለባለ ታሪኩ እተወዋለሁ።

"መካ ላይ ምንም አይነት ወገንም ሆነ ረዳት የሌለኝ ስሆን እስልምናን በመቀበሌም የመካ አጋርያን ያላወረዱብኝ የቅጣት አይነት አልነበረም።

ያኔ ሰሀባዎች ወደ መዲና ስደት ሲጀምሩ እኔን የመካ ሰዎች በማን አለብኝነት ከቀዬአቸው አገዱኝ። ከቅጣት በየአይነቱንም ይግቱኝ ነበር።

ከሙሀመድ ጋር ጦርነት ገጥመው ሽንፈት ባጋጠማቸው ቁጥር መካ ሲመለሱ እኔን እና መሰል ጓደኞቼን በማሰቃየት የብቀላ አርጬሜአቸውን ያወርዱብን ነበር።

ከእለታት አንድ ቀን ከመካ ለመውጣት ምቹ ሁኔታ አገኘሁ። ምንም እንኳን የስምምነት ድርድራቸውን የማላውቅ ብሆንም አጋጣሚዋንም ያለ ምንም ማቅማማት ተጠቅሜያት ጉዞ ወደ መዲና አቀናሁ።

ከ6 አመታት በፊት ያየሁት የነቢ ፊት እየናፈቀኝ፣ የሙስሊሞቹን ጀመአ መቀላቀል ስሜቱ እያጣደፈኝ ፤ የአረብያ አሸዋማ ምድርን በፍጥነት አቆራርጥ ጀመር።

መዲና ገባሁ።
ነቢን አይቼ አይኖቼ ሳይጠግቧቸው፣ ከባልደረቦቻቸውም ተቀላቅዬ ናፍቆቴን ሳልወጣ ሁለት ሰዎች ከወደ መካ ብቅ አሉ።

‹‹ሙሀመድ ሆይ! ስምምነታችንን በሚፃረር መልኩ ይህ ግለሰብ ከኛ ሸሽቶ ወዳንተ መጥቷል ና በስምምነቱ መሰረት አሳልፈህ ስጠን›› ብለው ረሱልን ጠየቁ ።

ረሱል ሰዐወ ዳግም ለስቃይ እና ለእንግልት ወደሚዳርጉኝ ሰዎች አሳልፈው ይሰጡኛል ብዬ በፍፁም ባልጠበኩበት ሁኔታ ወደ መካ እንድመለስ አዘዙኝ።

‹‹ያ ረሱለላህ! እነዚህ ሰዎች ነፍሴን እና ሀይማኖቴን እንዲፈታተኑት አሳልፈው ይሰጡኛልን?›› ስል በአሳዛኝ ንግግር ተማፀንኳቸው።

‹‹አባ በሲር ሆይ! እሺ በለኝ፤ ሂድ አላህ ላንተ እና ለመሰሎችህ መውጫ ቀዳዳን ያበጅላችኋል።›› ብለው አዘዙኝ።

በሁለቱ ሰዎች ከኋላ እና ከፊት ተከብቤ መዲናን ለቅቄ ወጣሁ። ብዙ ተጓዝን፣ የመዲናን ድንበር በብዙ ርቀን ነጎድን።

ማንም ውል ማይልበት እልም ያለ በረሀ ላይ ስንደርሥም እረፍት ለማድረግ ከአንድ ስፍራ ሶስታችንም ተቀምጠን ማውጋት ጀመርን።

ከነዚህ ሰዎች የማመልጥበትን መውጫ ቀዳዳ በብዙ ሞከርኩ፤ በፍፁም አልተቻለኝም። ርዕስ ፈለግኩ ና የአንደኛውን ሰው ሰይፉን አይቼ ማደናነቅ ጀመርኩ።

ሰውዬውም በዝያች ሰይፍ የፈፀማቸውን ጀብዶች ይተርክልኝ ጀመር። እኔም የይምሰል መገረምን ለሱ እገረምለት ያዝኩ።

ብዙም አልቆየንም፦‹‹ሰይፉን ይዘህ ተመልከት ከፈለግህ›› አለኝ። ምንም ሳላቅማማ ሰይፉን ብድግ አድርጌ እያገላበጥኩ ማየት ጀመርኩ።

ከነፍሴ ጋር ማውጋት ጀመርኩ፦‹‹እነዚህ ካፊሮች ወደ ካፊሮች ሀገር ወስደው የመከራ ፅዋ ሊያጠጡኝ አይደለምን? ወላሂ በነሱማ እንደ ከብት እየተነዳሁ አልሄድላቸውም። ደግሞም ነቢ የሚጠበቅባቸውን አድርገዋል የስምምነቱ አፍራሽ የሚሆኑበት ምንም ምክንያት የለም›› ብዬ ራሴን ለመታደግ ወሰንኩ።

ሰይፉን ከማንገቸው በፍጥነት መዘዝኩት ና የአንደኛውን ጭንቅላት ከገላው ለየሁለት። ወደ ሁለተኛው ዞር ስል ሽሽት ጀምሯል፤ እሱን መግደል አላማዬ ስላልነበር ትቶ ከሸሸ እኔም ትቼው ወደ መዲና ተመለስኩ።

ልክ መዲና ገብቼ ወደ መስጅዱ ብቅ ስል የሟቹ ጓደኛ እየተንቀጠቀጠ ሁኔታውን ለነቢ ሲያስረዳ ሰይፌን እንደታጠቅኩ ተገጣጠምን።

‹‹ወላሂ ቃልኪዳንዎትን አላፈረስኩም፤ እርስዎም ቃልዎትን ሞልተዋል›› ብዬ ነቢን ሰዐወ በንግግር ቀደምኳቸው።

‹‹እንዴት?›› አሉኝ በግርምት።

‹‹ቃል ኪዳንዎትን አክብረው ለመካ ሰዎች አሳልፈው ሰጥተውኛል፤ እኔም ለትዕዛዝዎ ተገዢ ሆኜ ሄጅያለሁ። በመጨረሻም ነፍሴን ነፃ ማወጣበት መንገድ ሳገኝ ነፃ አውጥቻለሁ›› አልኳቸው።

እሳቸውም፦‹‹አይ! እሄ ጀግና ረዳት ወንዶችን ቢያገኝ›› አሉ። ደስታዬ ጨመረ፤ ግና ወደ መካ ብመለስ ለብቀላ ይገድሉኛል መዲና ብቀር ነቢን ስለ ቃልኪዳን ይወቅሷቸዋል ብዬ መዲናን ለቅቄ ወጣሁ።

ከአንድ ባህር ዳርቻ ሄጄ ጫካው ውስጥ ለመሸፈት ወሰንኩ። ጫካውም የመካ ሰዎች ንግድ መመላለሻ መሆኑን ስረዳ ይልቅ ውስጤ በደስታ ተሞላ።

የስምምነቱን ጉዳይ ሰግተው መካ ላይ ይሰቃዩ የነበሩ ሙስሊሞችም የኔን ጫካ መግባት ሰምተው ወደ ከተምኩበት ጫካ እየተንጠባጠቡ ከመካ ወደኔ መምጣት ጀመሩ።

እንዲህ እንዲህ እያልን 70 ሰዎች እዝያ ጫካ ውስጥ ተሰበሰብን። የመካ የንግድ ግመሎች ሸቀጦቻቸውን ይዘው ሲያልፉ ሸቀጡን እየነጠቅናቸው ከመካ ምንም አይነት እቃ ለንግድ ሲወጣ እኛ እየወረስን ወደ መካም ምንም አይነት ሸቀጥ ሲጋባ ሙሉ በሙሉ እየወረስን ቀጠናውን ተቆጣጠርነው።

ያኔ ያሰቃዩን የመካ ሰዎች የመኖር ህልውናቸው በጃችን እስኪወድቅ ድረስ ጎሮሮአቸው በእኛ እጅ ተዘጋ። ሚበሉትን አጡም።

‹‹ሙሀመድ ሆይ! ያኔ ከተፈራረምንበት ስምምነት አንዱን ውድቅ አድርገናል ና የፈለገ ሰው ወዳንተ መሰደድ ይችላል፤ ግና በዝምድናችን ይሁንብህ እነዚህን ወጣቶች ከጫካ አስወጥተህ መዲና ውሰዳቸው›› የሚል የተማፅኖ ደብዳቤ የመካ ሰዎች ላኩ።

ትረካውን አንዱ ወጣት እንዲህ ሲል ይቋጨዋል፦

እኛም በመካ ሰዎች ሸቀጥ ተንደላቅቀን በጫካ እየኖርን ባለንበት ሁኔታ ወደ መዲና ተመልሰን እንድንገባ ረሱል ሰዐወ ደብዳቤ ላኩልን።

ይህ የረሱል ሰዐወ ደብዳቤ ከእጃችን ሲገባ የጫካው መስራች አቡ በሲር ሞት አፋፍ ላይ ነበር።

የረሱልን ደብዳቤ ስሰጠው በስስት እያሸተተው ይስመው ጀመር። በናፍቆት አይኖቹ ነቢን አይቶ ሳይጠግብ ይህ ወጣት ደብዳቤአቸውን እየሳመ በለቅሶ፦‹‹ነቢን ሰላም በሉልኝ›› እያሉ ነፍሱ እዝያው ወጣች።

እኛም ጓደኛችንን በዝያ ጫካ ለብቻው ቀብረነው ጥሪ ወዳደረጉልን መልዕክተኛ ጉዞአችንን ቀጠልን።

የቅጣትን አርጬሜ እየተቀለበ፤ በጫካ ህይወቱ ያለፈው አቡ በሲር አላህ መልካም ስራዎቹን ይውደድለት።

Sefwan Sheikh Ahmedin

----------------------------------------------------------
ምንጭ፦
صور من حياة الصحابة

30/11/2022

Subhanallah

ከእለታት አንድ ቀንም ለዝሙት እራሷን አዘጋጅታ ክፍሏ አስጠራችው'ና በሩን ዘጋጋች። ከዚያም፦ "ተዘጋጅቼልሀለሁ ናልኝ" ስትለው፤ ዩሱፍም፦" በአላህ እጠበቃለሁ እርሱ (የገዛኝ) ጌታዬ ኑሮዬን ...
30/10/2022

ከእለታት አንድ ቀንም ለዝሙት እራሷን አዘጋጅታ ክፍሏ አስጠራችው'ና በሩን ዘጋጋች። ከዚያም፦ "ተዘጋጅቼልሀለሁ ናልኝ" ስትለው፤ ዩሱፍም፦" በአላህ እጠበቃለሁ እርሱ (የገዛኝ) ጌታዬ ኑሮዬን ያሳመረልኝ ነውና፤ (አልከዳውም)፡፡ እነሆ! በደለኞች አይድኑም" አላት።

በዚህ አጋጣሚ ዩሱፍ በሩን ከፍቶ ሲወጣ የሴትየዋ ባል፣የከተማይቷ አስተዳዳሪ፣ የራሱ አለቃ በር ላይ ተገጣጠሙ። ሚስቱ ዩሱፍን ዐሰ ተከትላም ስትወጣ ባሏን በር ላይ አገኘችው።

ለትንሽ ሰዐት በሶስቱም መሀከል ዝምታ ሰፈነ። በመቀጠልም ምን እየተከሰተ እንደነበር አስተዳዳሪው ሲጠይቃቸው ሚስትየው ቀደም ብላ፦" በባለቤትህ መጥፎን ያሰበ ሰው ቅጣቱ መታሰር ወይም አሳማሚ ስቃይ እንጂ ሌላ አይደለም" አለች።

ዩሱፍም ንግግሯ ውሸት እንደሆነ አስተባበለ በዚህ መሀልም አንድ በወራት ቤት ያለ የዙለይካ የዘመዷ ህፃን ልጅ ሊዳኛቸው አላህ በመሀል አስገባው።

ህፀኑም፦" ቀሚሱ ከበስተፊት ተቀድዶ እንደሆነ (እሷ)እውነት ተናገረች፡፡ እርሱም ከውሸታሞቹ ነው።

ቀሚሱም ከበስተኋላ ተቀድዶ እንደሆነ እሷ ዋሸች፡፡እርሱም ከእውነተኞቹ ነው" በማለት ፍርዱን ሰጠ።

አስተዳዳሪውም በመገረም ቀሚሱን ሲመለከት የተቀደደው ከኋላ ነው።ወደ ሚስቱ ዞር በማለት፦" እርሱ (የተናገርሺው) ከተንኮላችሁ ነው (ሴቶች) ተንኮላችሁ በእርግጥ ብርቱ ነውና" ብሎ ወቀሳት። ለዩሱፍም ወሬውን እንዳያሰራጭ ነገረው።

ነገር ግን በጥቂት ቀናት ውስጥ ወሬው በከተማይቱ እጅጉን ተሰራጨ። ወሬው ከአጥናፍ እስካጥናፍ ተፋፋመ። ይንህ የወሬውን መሰራጨት ዙለይካ ስትሰማ አንድ ሴራ ጠነሰሰች'ና አንድ ትልቅ ዝግጅት በማዘጋጀት የከተማውን የመሳፍንት እና የከበርቴ ሚስቶችን ባጠቃላይ ጠራች።

ከዚያም በዝግጅቱ ሁሉም ሴት መገኘቱን ስታረጋግጥ ፍራፍሬ እና ቢለዋ በመስጠት እሷ መብላት ጀምሩ ሳትል ማንም እንዳይበላ አዘዘቻቸው።

በዚህ መሀል አሁን መብላት ትችላላችሁ ብላ ሴቶቹ የያዙትን ፍራፍሬ መቆራረጥ ሲጀምሩ፦"ዩሱፍ ና ግባ" በማለት ድምጿን ከፍ አድርጋ ጠራችው።

ዩሱፍም ያማረ ልብስ አስለብሳው ነበር'ና ልክ የሌሊት ጨረቃ መስሎ ወደ ውስጥ ሲገባ ሴቱ ሁሉ አይናቸው በሱ ፈዘዘ፤ ፍራፍሬውን ረስተው እጆቻቸውን በያዙት ቢለዋ በመሸረካከት፦" አላህም ጥራት ይገባው፡፡ ይህ ሰው አይደለም፡፡ ይህ ያማረ መልአክ እንጅ ሌላ አይደለም" ማለት ጀመሩ።

እሷም፦"ታዲያ ይህ ያ በርሱ (ፍቅር) የዘለፋችሁኝ ነው፡፡ በእርግጥም ከነፍሱ አባበልኩት፡፡ እምቢ አለም፡፡ የማዘውንም ነገር ባይሠራ በእርግጥ ይታሰራል፡፡ ከወራዶቹም ይሆናል" አለቻቸው።

ዩሱፍም፦"ጌታዬ ሆይ! ወደርሱ ከሚጠሩኝ ነገር (ከዝሙት) ይልቅ መታሰር ለእኔ የተወደደ ነው፡፡ ተንኮላቸውንም ከእኔ ላይ ባትመልስልኝ ወደነሱ እዘነበላለሁ፡፡ ከስህተተኞቹም እሆናለሁ" ሲል አላህን ተማፀነው።

የከተማይቱ አስተዳዳሪም በሚስቱ ሰበብ የጠፋውን ስሙን ለማደስ ሲል ዩሱፍን እስር ቤት ለመጣል ወሰነ። ዩሱፍም እስር ቤት በገባ ግዜ እሱን በፊትም የሚያውቁት ሁለት እስረኞች (አንዱ የንጉስ የምግብ ሰራተኛ ሲሆን አንዱ ደሞ የንጉስ ጠጅ ጠማቂ ነው።) ለዩሱፍም እንዲህ ሲል አንደኛው ጠየቀው፦" እኔ በህልሜ የወይን ጠጅን ስጠምቅ አየሁ" ሁለተኛውም፡-"እኔ በራሴ ላይ ዳቦ ተሸክሜ ከእሱ በራሪ (አሞራ) ስትበላ አየሁ፡፡ ፍቺውን ንገረን፡፡ እኛ ከአሳማሪዎች ሆነህ እናይሃለን'ና" በማለት ጠየቀው።

ዩሱፍም እችን አጋጣሚ በመጠቀም እስር ቤት ውስጥ ላሉ እስረኞች ዳዕዋ ለማድረግ አሰበ'ና፦"ማንኛውም የሚመጣላችሁ ምግብ ለናንተ ከመምጣቱ በፊት ፍቹን የምነግራችሁ ቢሆን እንጂ አይመጣላችሁም፡፡

ይኸ ጌታዬ ካሳወቀኝ ነገር ነው፤ እኔ በአላህ የማያምኑን እነርሱም መጨረሻይቱን ዓለም እነርሱ ከሓዲዎች የሆኑትን ሕዝቦች ሃይማኖት ትቻለሁ።

የአባቶቼን የኢብራሂምንና፣ የኢስሐቅን፣ የያዕቆብንም ሃይማኖት ተከትያለሁ፤ ለኛ በአላህ ምንንም ማጋራት አይገባንም፤ ያ (አለማጋራት) በኛ ላይና በሰዎቹ ላይ የአላህ ችሮታ ነው፤ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያመሰግኑም።

የእስር ቤት ጓደኞቼ ሆይ! የተለያዩ አምላኮች ከብርና ከወርቅ ከእንጨት የተሠሩ ይሻላሉን ወይንስ አሸናፊው አንዱ አላህ?

ከርሱ ሌላ እናንተና አባቶቻችሁ (አማልክት ብላችሁ) የጠራችኋቸውን ስሞች እንጅ አትግገዙም፤ አላህ በርሷ ምንም አስረጅ አላወረደም ፍርዱ የአላህ እንጅ የሌላ አይደለም እርሱን እንጅ ሌላን እንዳትግገዙ አዟል።

ይህ ትክክለኛው ሃይማኖት ነው፤ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም" በማለት ወደ አላህ ከጠራቸው በኋላ የሁለቱንም ህልም እንዲህ ሲል ፈታላቸው፦

"የእስር ቤት ጓደኞቼ አንደኛችሁ ለ ንጉሱ ጠጁን በመጥመቅ ወደ ቀድሞ ስራው ሲመለስ ሁለተኛችሁ ደግሞ ስቅላት ተፈርዶበት ከተሰቀለ በኋላም ጭንቅላቱን አዕዋፍ ይበሉታል። ይህ የህልማችሁ ፍቺ ጥርጥር የለውም ተፋፃሚም ነው።"

ይህን ካላቸው በኋላ ዩሱፍ ዐ ሰ ህልማቸውን በፈታው መልኩ አንደኛው ተወስዶ ሲሰቀል አንደኛውም ወደ መጀመርያ ስራው ተመልሶ ለንጉሱ ጠጅ እንዲጠምቅለት ተወሰነ።

ለንጉሱ ጠጅ እንዲጠምቅለት የተወሰነለት ሊወጣ ሲል ዩሱፍ ዐሰ አስቆመው'ና፦ "ንጉሱ ዘንድ ስትሄድ አንድ ንፁህ ሰው ያለ ወንጀሉ በአስተዳዳሪው አማካኝነት ታስሯል ብለህ በደሌን ንገርልኝ" አለው።

እሱም፦"እሽ" ብሎ ከወጣ በኋላ ንጉሱ ዘንድ ወደ ስራ ገበታው ሲቀላቀል ዩሱፍን ከነአካቴው ረሳው። በዚህ ሁኔታ ላይ ዩሱፍ ለረጅም አመታት ያለጥፋቱ እስር ቤት ከረመ።

ከእለታት አንድ ቀን የጠቅላይ ግዛቱ ንጉስ፣ የአስተዳዳሪው አለቃ በደረቅ ሌሊት ህልም አየው ብሎ ተነስቶ ቤተ መንግስቱን ያናውጥ ጀመር።

በአስቸኳይ የኮከብ አዋቂዎችን እና የጣኦት ካህናትን በዚያ ሌሊት እንዲሰበሰቡ አደረገ። ከዚያ ህልሙንም እንዲህ ሲል ተረከላቸው፦" እኔ ሰባትን የሰቡ ላሞች ሰባት ከሲታዎች ሲበሉዋቸው፣ ሰባትንም ለምለም ዘለላዎች ሌሎችንም ደረቆችን (ሲጠመጠሙባቸው በሕልሜ) አያለሁ፤ እናንተ ታላላቅ ሰዎች ሆይ! ሕልምን የምትፈቱ እንደሆናችሁ ሕልሜን ፍቱልኝ "

ካህናቱ እና ጠንቋዮቹ የንጉሱን ህልም ሊፈቱ እጅጉን ተቸገሩ። ቢያወጡ ቢያወርዱ ምንም ሊያውቁት አልቻሉም'ና፦"ንጉስ ሆይ! የዚህን ህልም ፍቺ ልናውቅ ስላልቻልን ይህ ህልም ቅዠት ነው" አሉት።

ያን ግዜ ጠጅ ጠማቂው ያ የድሮ የእስር ቤቱን ህልም ፈቺ ጓደኛውን ዩሱፍን አስታወሰ። ከመሀከል ብድግ በማለትም፦ "እኔ የህልሙን ፍቺ ይዤ እመጣለሁ ግን የእስር ቤት ፍቃድ አውጡልኝ" ሲል ለንጉሱ ተናገረ።

ንጉስም አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግለት በማዘዝ ጠጅ ጠማቂውም ዩሱፍ ወደሚገኝበት እስር ቤት ብቅ አለ። ዩሱፍንም ስለረሳው ይቅርታ በመጠየቅ ንጉሱ ያየውን ህልም ተረከለት'ና ፍቺውን ጠየቀው።

ዩሱፍም፦" ሰባትን የተከታተሉ ዓመታት ትዘራላችሁ፤ ያጨዳችሁትንም ሁሉ ከምትበሉት ጥቂት በስተቀር በዘለላው ውስጥ ተዉት። ከዚያም ከነዚያ በኋላ፣ ካከማቻችሁት ጥቂት ሲቀር፣ ለነሱ ያከማቻችሁትን ሁሉ የሚበሉ ሰባት የችግሮች ዓመታት ይመጣሉ።

ከዚያም ከነዚያ በኋላ ሰዎቹ በርሱ የሚዘነቡበት፣ በርሱም (ወይንን) የሚጨምቁበት የጥጋብ ዓመት ይመጣል" በማለት ህልሙን ብቻ ሳይሆን መፍትሄውንም ጭምር ዘረዘረለት።

ጠጅ ጠማቂውም የህልሙን ፍቺ ይዞ በደስታ ወደ ቤተ መንግስት ይገሰግስ ጀመር። ልክ እንደደረሰም ለንጉሱ ፍቺውን ከነ መፍትሄው ሲተርክለት ንጉሱ ዩሱፍን አሁኑኑ አምጡልኝ አለ።

ዩሱፍንም ከእስር ቤት አውጥቶ የሚያመጣው ሰው ተመድቦ እስር ቤት ሲደርስ ዩሱፍ፦" ወደ ንጉሱ ተመለስ፤ የነዚያንም እጆቻቸውን የቆረጡትን ሴቶች ሁኔታ ጠይቀው፤ ጌታዬ ተንኮላቸውን አዋቂ ነውና" በማለት ይህ ጉዳይ ሳይጣራ ለመውጣት ፍቃደኛ እንዳልሆነ ለንጉሱ ለከ።

ይህን ግዜ ንጉሱም በዚያ ቀን ያን ዝግጅት ተካፍለው የነበሩ የመሳፍንት፣ የከበርቴ እና የአስተዳዳሪውንም ሚስት አንድ ላይ እንዲ ቀርቡ ካደረገ በኋላ፦ " ዩሱፍን ከነፍሱ ባባበላችሁት ጊዜ፣ ነገራችሁ (ምክንያታችሁ) ምንድነው?" ብሎ ሲጠይቃቸው።

ሴቶቹም በአንድ አፍ፦"ለአላህ ጥራት ይገባው፤ በርሱ ላይ ምንም መጥፎን ነገር አላወቅንም" አሉት። ያን ግዜ ከመሀል የአስተዳዳሪው ሚስት ቀበል አድርጋ፦" አሁን እውነቱ ተገለጸ፤ እኔ ነኝ ከነፍሱ ያባበልኩት፤ እርሱም ከውነተኞቹ ነው" በማለት በህዝብ ፊት የዩሱፍን ንፁህነት መሰከረች።

ንጉስ ይህን በሰማ ግዜ እውነተኛውን ዩሱፍን ለማየት እጅጉን ጉጉት አደረበት። "ነፃነትህን አስመስክረሀል ና" ብሎ ጠርቶት የግል አማካሪው ከማድረግም ባሻገር የሀገሪቱን ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ፈላጭ ቆራጭ አደረገው።

አሁን ዩሱፍ ዐሰ ህዝቡ ዘንድ ልዩ ቦታ አለው።አብዝሀኛውም የሀገሪቱ ነዋሪ የዩሱፍን ጥሪ ተቀብሏል።እንዲህ እንዲህ እያሉ 7 አመታት ካሳለፉ በኋላ የድርቁ ዘመን መጣ።

ድርቁን ተከትሎ ከተለያዩ ሀገራት በድርቅ የተመቱ እህል ሸማቾች ወደ ግብፅ ምድርም ይተሙ ጀመር። በዚያ መሀል በከንዓን ይኖሩ የነበሩ የዩሱፍ ቤተሰቦችም የድርቁ ሰለባ ነበሩ'ና 10 ወንድሞቹ እህል ፍለጋ የግብፅን ምድር ረግጠው በማያውቁት ወንድማቸው መጋዘን ለእህል ተሰለፉ።

በግዜው ከመንግስት መጋዘን ሁሉም እህል ሲሸምት ስሙን እና የመጣበትን ሀገር እያስመዘገበ ነበር የሚሸምተው።

እነዚህም ወንድሞቹ ስማቸውን እስመዝግበው እህላቸውን ከመረከባቸው በፊት ዩሱፍ የከንዓን ሰዎች መጥተዋል የሚል ወሬ ሰምቶ ሊያጣራ ሲሄድ ወንድሞቹን ተመለከታቸው። ምንም እንኳን እሱ ቢያውቃቸውም እነሱ ግን በፍፁም ሊያውቁት አልቻሉም።

ግና ዝም ብለው በግምት፦" ይህ ፊት አዲስ አልሆነብኝም ይባባላሉ" ጀመር እርስ በርስ። ዩሱፍም ከተለያዩ ሀገራት ከመጡ ቁጥር ስፍር ከሌለው ሰልፈኛ መሀል ለ40 አመት የተለያያቸውን ወንድሞቹን የሰሩበትን ተንኮል ወደ ጎን አድርጎ በናፍቆት ተሸንፎ ስለማንነቱ ምንም ሳይነግራቸው ወደሚኖርበት ቤተ መንግስት ይዟቸው ሄድ።

ይህችን ሌሊትም እሱ ጋር አሳልፈው በነጋታው እንደሚሄዱ ካሳመናቸው በኋላ በጥሩ መስተንግዶ እራት አብልቷቸው ያዕቁብ ስለተባለው ነቢይ መጠየቅ ጀመረ።

በህይወት እንዳለ እና ዩሱፍ ዐሰ በተባለው ልጁ ሀዘን ምክንያት በጣሙን እንደተጎዳ ነገሩት። ዩሱፍ ይህን ሁሉ ሲሰማ ሆድ እየባሰው ከእንባው ጋር ትንቅንቅ ቢገጥምም ይህን ሀዘኑን ግን ለወንድሞቹ ግልፅ ሊያደርግ አልፈለገም። ያውቁኛል ብሎ ሰግቶ።

በነጋታው ዩሱፍ አገልጋዮቹን ጠርቶ፦"ለእህሉ የከፈሉትን ገንዘብ በየከረጢታቸው ውስጥ ደብቁትና ሳያውቁ ስጧቸው" ብሎ አዘዘ።

ዩሱፍ ባዘዘውም መልኩ የከፈሉት ገንዘብ ተመልሶ በየከረጢታቸው ተጨመረላቸው። በመጨረሻም ሲሸኛቻው፦"በሚቀጥለው ዙር ስትመጡ ከንዓን ትታችሁት
የመጣችሁትን ትንሹን ወንድማችሁን ይዛችሁ ኑ። እሱን ካላመጣችሁት ግን ምንም አይነት እህል አንሰፍርላችሁም" ብሎ ሸኛቸው።

እነሱም እንደሚሞክሩ ቃል ገብተውለት ጉዞ ወደ ከንዓን ጀመሩ። ረጅም ተጉዘው ከንዓንም ሲደርሱም በግብፅ ከተማ የገጠማቸውን ሁሉ ለአባታቸው ያዕቁብ ዐሰ ተረኩለት'ና በቀጣይ ዙር ግን ታናሽ ወንድማቸውን ቢንያሚንን ካላመጡ ምንም አይነት ስፍር እንደማይሰፈርላቸው ነገሩት።

ዩሱፍ ክፍል 3 ይቀጥላል...

Sefwan Sheik Ahmedin

ምንጭ፦
البدايه والنهايه
الكامل في التاريخ

በመጨረሻም መላዕክቱ  ይህችን ከተማ ሊያጠፏት እንደሆነ እና ሉጥም ቤተሰቦቹን እና ተከታዮቹን ሁሉ ሰብስቦ ጎህ ሳይቀድ ከተማይቱን ለቅቆ እንዲወጣ አዘዙት። በዚህ ሁኔታ ሉጥ ዐሰ እንግዶቹን እ...
30/10/2022

በመጨረሻም መላዕክቱ ይህችን ከተማ ሊያጠፏት እንደሆነ እና ሉጥም ቤተሰቦቹን እና ተከታዮቹን ሁሉ ሰብስቦ ጎህ ሳይቀድ ከተማይቱን ለቅቆ እንዲወጣ አዘዙት።

በዚህ ሁኔታ ሉጥ ዐሰ እንግዶቹን እያወራ ሳለ ህዝቡ በሩን ሊገነጥል ተቃረበ። ያን ግዜ ጂብሪልም አላህን አስፈቀደ'ና አንድ ግዜ በሩን ከፍቶ በመውጣት በክንፉ ፊት ፊታቸውን ክፉኛ ይመታቸው ጀመር። አይኖቻቸውም እዝያው እየሟሸሹ መፍሰስ ጀመሩ።

ጠዋት ሲነጋ ሉጥን እንደሚገድሉት እየዛቱ ሁሉም ከበሩ እየተተራመሱ ሄዱ።ከዚያም ሉጥ መላዕክቱን፦"መቼ ነው እነዚህን ህዝቦች ምታጠፉት" አላቸው።
እነሱም፦"ጎህ ሳይቀድ ነው" አሉት።
ሉጥም፦"አሁኑኑ ብታጠፏቸውስ" ሲላቸው...
መላዕክቱም፦"እንዴ ሱብሂ ቅርብ አይደል ወይ!" አሉት።

በነጋታው ሉጥ ተከታዮቹን፣ ቤተሰቦቹን እና አመፀኛዋን ሚስቱን ይዞ ከመቅሰፍቱ ሽሽት ከከተማይቱ መውጣት ጀመረ።

ሲወጣም ለተከታዮቹ በከተማይቱ የሚወርደውን መቅሰፍት ማንም ዞሮ ማየት እንደሌለበት አስጠንቅቆ ተናገረ።

አሁን ሁሉም ጉዞ ጀምረዋል፤ መላዕክቱ እዝያው ከተማ ውስጥ ናቸው።ሉጥ ዐሰ እና ተከታዮቹ ከተማይቱን ልክ ለቀው እንደወጡ ከወደ ከተማይቱ በኩል ከፍተኛ ድምፅ ሰሙ።

ማንም ወደ ከተማዋ እንዳይዞር ማስጠንቀቂያ ስለተሰጠ ማንም አልዞረም ነበር። የሉጥ ሚስት ግን ወደኋላ በመዞር፦"ወይኔ ወገኔ!" በማለት ጮኸች።

ትልቅ የድንጋይ ፍንጣሪ መጥቶ እራሷን ለሁለት ከፈለላትና የመቅሰፍቱ ሰለባ ሆነች። አላህም ይህን ዘግናኝ ክስተት ሲተርክ እንዲህ ይላል፦"ትዕዛዛችንም በመጣ ግዜ (የከተማይቱን) ላይዋን ከታች አደረግን (ገለባበጥናት) ተከታታይም የሆነ የሸክላ ድንጋይ በርሷ ላይ አዘነብን" ። ሱረቱ ሁድ

እንዲህ አድርጎ ነበረ የገለባበጣቸው። መጀመሪያ ጂብሪል ክንፉን በከተማይቱ መሬት ውስጥ ዘቅዝቆ አስገባው።ከዚያም ከተማይቱን ከነ ህንፃዎቿ ነቅሎ ወደ ሰማይ ከፍ ካደረገ በኋላ ገለበጠው'ና መልሶ ወደ ምድር ተከለው።

ሉጥ ከነ ተከታዮቹ ብዙ ርቀት ከተጓዘ በኋላ ሱዒር የተባለ አከባቢ በመስፈር ይህ ነው ተብሎ በታሪክ መዛግብት እድሜው ባይሰፍርም እዝያው ሱዒር ላይ ህይወቱ አልፏል። (ዐለይሂ ሰላቱ ወሰላም)

ያዕቁብ ልጆቹን ሚስቶቹን እና አገልጋዮቹን ይዞ ከንዓን ምድር ላይ ኑሯቸውን ጀምረዋል። ያዕቁብ ልጆቹን ሁሉ እላፊ በመውደዱ የሚታወቅ አባት ቢሆንም ለየቲሞቹ ለዩሱፍ እና ለቢንያሚን ያለው ቦታ ልዩ ነበር።

ከእለታት አንድ ቀን ዩሱፍ በሌሊት ተነስቶ ለአባባቱ ያየውን ድንቅ ህልም እንዲህ ሲል ይነግረዋል፦ " አባቴ ሆይ! እኔ ዐስራ አንድ ከዋክብትን ፀሐይንና ጨረቃንም (በሕልሜ) አየሁ፡፡ ለእኔ ሰጋጆች ሆነው አየኋቸው"

አባትየውም፦"ልጄ ሆይ! ሕልምህን ለወንድሞችህ አታውራ፡፡ ላንተ ተንኮልን ይሰሩብሃልና፡፡ ሰይጣን ለሰው ግልጽ ጠላት ነውና፤ እንደዚሁም (እንዳየኸው) ጌታህ ይመርጥሃል፡፡

ከንግግሮችም ፍች ያስተምርሃል፡፡ ጸጋውንም ከአሁን በፊት በሁለቱ አባቶችህ በኢብራሂምና በኢስሐቅ ላይ እንዳሟላት በአንተ ላይና በያዕቆብ ዘሮችም ላይ ይሞላታል፡፡ ጌታህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና" ብሎ አብስሮት ህልሙንም ለማንም እንዳይናገር አስጠነቀቀው።

አባትየው ያዕቁብ የዩሱፍን ህልም ከሰሙ በኋላ ለዩስፍ ያላቸው ፍቅር ወደ አክብሮት እና ለሱ ወደ መተናነስ ያደላም ጀመር።ይህ ግን ለዩሱፍ ለአባቱ ልጆች የእግር እሳት ሆኖባቸው ቅናት እረፍት ነስቷቸዋል።

ከእለታት አንድ ቀን የዩሱፍ የአባት ልጆች በዩሱፍ እና በአባቱ መካከል ያለውን ፍቅር እንዴት በአጭሩ ማኮላሸት እንዳለባቸው ሊመካከሩ አንድ ቦታ ተሰበሰቡ። ብዙ ሀሳቦችን አንስተው በመጨረሻም ዩሱፍን በአንድ ውሀው ጨዋማ በሆነ ስምጥ ጉድጓድ ውስጥ ሊጨምሩት ወሰኑ።

ማታ ላይ አባታቸው ዘንድ በመሄድም፦ " አባታችን ሆይ! በዩሱፍ ላይ ለምን አታምነንም እኛም ለእርሱ በእርግጥ አዛኞች ነን። ነገ ከእኛ ጋር ላከውና ይደሰት፤ ይጫወትም፡፡ እኛም ለእርሱ ጠባቂዎች ነን" በማለት ዩሱፍ ከነሱ ጋር እንዲሄድ አባታቸው ያዕቁብን ተማፀኑት።

ያዕቁብም፦" እኔ እርሱን (ዩሱፍን) ይዛችሁ መሄዳችሁ በእርግጥ ያሳዝነኛል፡፡ እናንተም ከእርሱ ዘንጊዎች ስትሆኑ ተኩላ ይበላዋል ብዬ እፈራለሁ" በማለት መለሰላቸው።

ከዚህም ከዚያም ብለው አባታቸውን ካሳመኑት በኋላ የልባቸውን ሊፈፅሙ ዩሱፍን ወዳጅ መስለው አቅፈው ወሰዱት።ያሰቡበትም ጉድጓድ ውስጥም እየለመናቸው እጅ እግሩን አሳስረው ቀሚሱን አውልቀው ወረወሩት።

ማታ ሲሆንም የሁዳ ባመጣው ሀሳብ መሰረት ያወለቁትን የዩሱፍን ቀሚስ አንድ ፍየል አርደው ቀሚሱን በፍየሏ ደም ለወሱት።

በመጨረሻም ምሽቱ ሲደምቅ እንስሳቶቹን እየነዱ መንደር ከደረሱ በኋላ የዩሱፍን በደም የተለወሰ ቀሚስ ይዘው እዬዬዬ! በማለት እያለቀሱ ሰፈሩን አመሱት።

ይህን ሲያይ ያዕቁብ እግሩ ተብረከረከ ተንኮለኛ ልጆቹ በውዱ ልጁ ሴራቸውን ተግባር ላይ እንዳዋሉ ተረዳ።
እሱም፦ "ልጄ ምን ሆነ" ሲላቸው
እነሱም፦" አባታችን ሆይ! እኛ (ለሩጫና ለውርወራ) ልንሽቀዳደም ሄድን። ዩሱፍንም ዕቃችን ዘንድ ተውነው፡፡ ወዲያውም ተኩላ በላው፡፡ አንተም እውነተኞች ብንሆንም የምታምነን አይደለህም" አሉት።

አባታቸውም፦" አይደለም፤ ነፍሶቻችሁ (ውሸት) ነገርን ለእናንተ ሸለሙላችሁ፡፡ ስለዚህ መልካም ትዕግስት (ማድረግ አለብኝ) በምትሉትም ነገር ላይ መታገዣው አላህ ብቻ ነው" ብሎ ጉዳዩ ለአላህ ተወው።

ዩሱፍም እዚያ ጉድጓድ ውስጥ ሳለ ወደ ግብፅ የሚሄድ ቅፍለት (ተጓዥ ነጋዴዎች) በዚያ ጉድጓድ ሲያልፉ ውሀ ለመቅዳት ባልዲያቸውን ወደ ውስጥ ወርውረው ውሀ ለማውጣት ወደ ላይ ሲጎትቱ ቆንጅዬ ልጅ ባልዲው ላይ ተንጠልጥሎ ወጣ።

በዚህ ሁኔታ ላይ ውሀውን ሚቀዳው ሰውዬ ልጅ አገኘሁ እያለ ሲጮኽ የዩሱፍ ወንድሞች ሰምተው መጡ'ና፦"ከኛ ያመለጠ ባሪያ ነው ከፈለጋችሁ ግዙን እንጂ በነፃ አትወስዱም " በማለት ወንድማቸውን በርካሽ ዋጋ ለነጋዴዎቹ ሸጡላቸው።

ነጋዴዎቹ ደግሞ ሸቀጣቸውን ከሚገዙባት ግብፅ ከተማ ሲደርሱ ለግብፅ አስተዳዳሪ በውድ ዋጋ ሸጡለት። የሀገሪቱ አስተዳዳሪም ዩሱፍን ለሚስቱ በስጦታ መልኩ አበርክቶላት ልጅ ስለሌላት እንድ ልጇ አድርጋ እንድታየውም ነገራት።

ሚስቱም እጅጉን ተደሰተች የልጁ ውበትም ከልጅነቱ ጋር አጓጊነቱም ማረካት። ግዚያት ነጎዱ ቀን ሌሊትን ክረምት በጋን እየተተካኩ ብዙ አመታት ተቆጠሩ።

ዩሱፍም ወጣትነቱ እና የአዕምሮ ብስለቱ ይልቅ ውበቱን ጨምሮበታል። የአስተዳዳሪው ሚስት ይህን ስታይ ሁኔታዋ እየተቀያየረ መምጣት ጀመረ።

ዩሱፍ ዐሰ ክፍል 2 ይቀጥላል...

Sefwan Sheik Ahmedin

ምንጭ፦
البدايه والنهايه
الكامل في التاريخ

ያዕቁብም ፈራ፣ አላህንም ከወንድሙ ተንኮል እንዲታደገው ተማፀነ፣ ለአላህም ስለት ገባ። ከዚያም ወንድሙን ሊያስደስት በርከት ያለ ስጦታም አዘጋጀለት።200 ሴት ፍየሎችን እና 20 ወንድ ፍየሎች...
30/10/2022

ያዕቁብም ፈራ፣ አላህንም ከወንድሙ ተንኮል እንዲታደገው ተማፀነ፣ ለአላህም ስለት ገባ። ከዚያም ወንድሙን ሊያስደስት በርከት ያለ ስጦታም አዘጋጀለት።

200 ሴት ፍየሎችን እና 20 ወንድ ፍየሎች
200 ሴት በጎችን እና 20 ወንድ በጎች
30 (ኮርማ) በሬዎችን እና 40 ላሞች
20 ሴት ግመሎችን እና 10 ወንድ ግመሎች

አራቱንም የስጦታ አይነቶችን ለያይቶ ሊልክ በአራት ቡድን የተደራጀ አገልጋዮችን አዘጋጀና ቀድሞ አንዱን ቡድን ለከ።

የመጀመርያው ቡድን ስጦታዎቹን ይዞ ሂዶ ትንሽ ራቅ ሲል ሁለተኛውን ይልካል፤ ሁለተኛውም ትንሽ ራቅ ሲል ሶስተኛውን ይልካል። እንዲ እንዲ እያለ አራቱንም የስጦታ አይነት ከነ አገልጋዮቻቸው ጨምሮ፦ "ማንም የማን ነው ብሎ ከጠየቃችሁ ከያዕቁብ ለዒስ የተላከ ስጦታ ነው በሉ" ብሎ ላካቸው።

ይህንንም ሊያደርግ የቻለው ወንድሙ ዒስ ስጦታዎች በተከታታይ ሲመጡለት ደስታው የላቀ ይሆናል በሚል ነው።

ከዚያም የመጀመሪያውን ስጦታ የያዘው የአገልጋልይ ቡድን ዒስ እና ወታደሮቹ ያሉበትን ቦታ ሲደርሱ፦
ዒስ፦"ይህ የማን ነው?" ብሎ ጠየቀ።
አገልጋዮቹም፦" ከያዕቁብ ለዒስ የተላከ ስጦታ ነው" አሉት። እሱን ተቀበላቸውና ሁሉም የስጦታ ነጂ ቡድኖች ስጦታዎቻቸውን ተራ በተራ እየነዱ አስረከቡት።

ያዕቁብም ሚስቶቹን ልጆቹን እና የተቀሩ አገልጋዮቹን አስከትሎ በሌሊት ወደ ወንድሙ ጉዞ ጀመረ። በዚህች የሌሊት ጉዞ ነበር ክርስቲያን ወገኖች ያዕቁብ እና እግዚአብሄር ተደባድበው ያዕቁብ አሸነፈው የሚሉት።

ሌሊቱን ተጉዞ ፀሀይ ጀንበሯን አምልጣ መውጣት ስትጀምር ለ20 አመታት ያህል የተለያዩ ወንድማሞች አይን ለአይን ተገጣጠሙ።

ዒስ 400 ጦረኛዎችን አሰልፏል። ያዕቁብም ወንድሙን ሲያየው 7 ግዜ አጎበደደለት (ይህ በዘመናቸው ሀራም አልነበረም የዘመናቸውም ሰላምታ ነበር። በቀጣይ ክፍላችን ለዩሱፍ ሲሰግዱ እንዳስሳለን።

ዒስ ዱዓውን ከአባቱ የዘረፈውን ወንድሙን ሲያይ ሄዶ ተጠምጥሞበት ወንድሙን እየሳመ ያለቅስ ጀመር። በዚህ አጋጣሚ ከአጠገቡ ያሉትን ሴቶች ልጆችን እና አገልጋዮችን ሲመለከት፦"ይሄን ሁሉ ከየት አምጥተህ ነው?" አለው።

ያዕቁብም፦ "እነዚህ አላህ የሰጠኝ ስጦታዎቼ ናቸው" አለው። ይህን ግዜ የያዕቁብ ልጆች እና ሚስቶች ተራ በተራ እየመጡ ዒስን ከዘየሩ በኋላ ያዕቁብ በአገልጋዮቹ አማካኝነት ለዒስ የላከውን ስጦታ ዒስ መቀበል እንቢ አለ።

ያዕቁብም ዐሰ ለምኖት እንዲቀበል አደረገው'ና አብረው በረሀውን እያቆራረጡ አባታቸው ወደሚገኝበት የፊለስጢን ምድር መትመም ጀመሩ።

በዚህ ጉዞ ላይም ሳሉ ያኔ ያዕቁብ አጎቱ ጋ ሲሄድ ተኝቶ ህልም ያየበትን ቦታ ደረሱ። ያዕቁብም በ200 በግ ያንን ቦታ ከአንድ ገበሬ ገዛው'ና አንድ ትልቅ የአምልኮ ቦታ ሰራ፤ ቦታውም ቁድስ ተሰኘ።

ከዚያ በኋላ ነው በነቢ ሱለይማን ዐሰ ዘመን ሱለይማን ያደሰው። በዚህ ጉዞ ላይም ሳሉ ነበር አንድ ደስታ እና ትልቅ ሀዘን በያዕቁብ ቤተሰብ የተከሰተው።

ነፍሰ ጡር የነበረችው ትንሿ ራሂል ምጥ አስቸገራት። ብዙ ከተጨነቀች በኋላ ቢንያሚን የተባለ ልጅ ተገላግላ ለራሷም ዱንያን ተገላገለቻት።

ያዕቁብም ባለቤቱን መንገድ ላይ ቀብሮ ሀዘኑን ታቅፎ ወደ አባቱ ጉዞ ቀጠለ። ከአባቱም ተገናኝቶ በከንዓን ምድር ሀብሩን በምትባል (ኢብራሂም ይኖር በነበረበት) አካባቢ መኖር ጀመረ።

ኢስሀቅም ዐሰ እርጅና ተጫጭኖትም ስለነበር ጌታው የፃፈለትን 180 አመት ካጠናቀቀ በኋላ ነፍሱን ለጌታው አስረከበ።

አሁን የያዕቁብን ትርክት እዚህ ጋ ያዝ እናድርገው'ና አንድ ግዜ ወደኋላ ልመልሳችሁ። ምክንያቱም የያዕቁብን ዐሰ ትረካ አጠናቅቀን ወደ ሉጥ ዐሰ እንመጣለን ብንል የያዕቁብን ትርካ ተከትሎ ነው ዩሱፍ ዐሰ የሚቀጥለው።

ሉጥ የኢብራሂም ዐሰ የወንድም ልጅ ሲሆን የኢብራሂምን ጥሪ የተቀበለ ብቸኛ (ወንድ) ነው። ኢብራሂምም ዐሰ ወደ ግብፅ ስደት ሲያደርግ ሉጥን ዐ ሰ ሰዶም ወደምትባል ከተማ ልኮት ነበር።

ሰዶም ማለት ወንጀል እንደ ፅድቅ የሚታይባት፣ የአማፅያን መጠራቀሚያ፣ሴትን የማይፈልጉ እና የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት የተንሰራፋባት፣ በተሰበሰቡበት ፈሳቸውን በገሃድ የሚፈሱ ጋጠ ወጦች፣ ወንድ ልጅ አስገድዶ የመድፈር እና ሌሎች ወንጀሎች የሚተገበሩባት ፀያፍ ከተማ ናት።

እዝያች ከተማ ነው እንግዲ ነቢዩሏህ ሉጥ ዐሰ ወደ አላህ ሊጠራቸው የገባው። ይህን ሲመለከት እነዚህን ፀያፍ ተግባራት እንዲያቆሙ እና አላህንም በብቸኝነት እንዲያመልኩ ጥሪ አደረገላቸው።

ሉጥ ምንም እንኳ በለዘብተኝነት ጥሪ ቢያደርግላቸውም ጥመትን እና አመፅን እንጂ ምንም አልጨመረላቸውም ነበር።አላህ ያዘነላቸው ሲቀሩ ይልቁኑ ጥሪ ባደረገላቸው ቁጥር የግድያ የወገራ ዛቻ እና ከሀገሪቱም ሊያስወጡት እንደሚችሉ ይዝቱበት ነበር።

በርካታ አመታትን ወደ አላህ ተጣርቶ ምንም ለውጥ ባለማየቱ አላህንም፦"ጌታዬ ህዝቦቼ ባስተባበሉኝ ነገር ላይ አንተ እርዳኝ" ሲል ተማፀነው።

እነሱም ምላሻቸው፦"እስቲ አንተ እውነተኛ ከሆንክ የአላህን ቅጣት አውርድብን" ነበር። አሁን ነገሩ ሊቋጭ ነው አላህም ማንነቱን ሊያሳያቸው ነው።

(ባሳለፍነው የትረካ ክፍል መላዕክት ኢብራሂም ዘንድ መጥተው ልጅ እንደሚወልድ አብስረውት ከዝያ ሉጥ ጋር ልንሄድ ነው ብለዋል ብለን መዳሰሳችን ይታወሳል።)

ከዚያ እነዚያ መላዕክት በሚያማምሩ ወጣት ጎረምሳዎች ተመስለው የሰዶምን ከተማ ገቡ። እዚያች ከተማ ሲገቡ ወቅቱ አመሻሽ ነበርም። መንገድ ላይ ሉጥ ዐሰ ይመለከታቸውና ተቿክሎ እቤቱ አስገባቸው።

ምክንያቱም የከተማው ህዝብ እነዚህን ወጣቶች ካይዋቸው ግብረ ሰዶም ሊፈፅሙባቸው ይችላሉ በሚል ስጋት ነበር።

የከተማው ህዝብ ሉጥን ዐሰ ምንም አይነት እንግዳ እንዳይቀበል ስላስጠነቀቁትም ሉጥ እግዶቹን ካስገባቸው በኋላ እንዴት ላድናቸው በሚል ሀሳብ በጣሙን ተጨነቀ።

በዚህ መሀል እርጉም የሆነችዋ የሉጥ ባለቤት ቀስ ብላ ከቤት በመውጣት ለአመፀኛ ህዝቦች፦"ሉጥ ቆንጆ ቆንጆ ወጣቶችን እቤቱ አስገብቷል" በማለት ነገረቻቸው።

ህዝቡም እየተንጋጋ የሉጥን ቤት ከበበ። ሉጥም ሊያነጋግራቸው ወጣ'ና በለስላሳ አንደበት ይለማመጣቸውም ጀመር ምናልባት የአንዱ ልብ ይለሰልስ ይሆናል በማለት።

በመጨረሻም፦ "ከፈለጋችሁ እነዚህን ሴት ልጆቼን አግቡ እነሱ ለናንተ ንፁህ (ሀላል) ናቸው። አላህንም ፍሩ እንግዶቼንም አታዋርዱብኝ" በማለት ይማፀናቸውም ጀመር።

ይህ ሁሉ ሲሆን ሉጥ ህዝቡ በእንግዶቹ ላይ እንዳይገቡ በሩን ዘግቶባቸው ነበር የሚከራከረው። በዚህም አጋጣሚ በሩን ለመስበርም የሚታገልም ነበር።

ይህን የሉጥን ሁኔታ እና እንግልት የተመለከቱት በወጣቶች የተመሰሉት መላዕክትም ሉጥን ጠሩት'ና ሁሉንም ነገር ግልፅ አደረጉለት። መላዕክት መሆናቸውንም አክለው ነገሩት።
1፦ጂብሪል
2፦ሚካኢል
3፦ኢስራፊል ነበሩ የመጡት መላዕክት።

ይቀጥላል...

Sefwan sheik ahmedin

ምንጭ፦
البدايه والنهايه

ኢስሀቅ አባቱ ኢብራሂም ዐሰ በህይወት ሳለ በ40 አመቱ ነበር ረፍቃ ቢንት በትዋዪል ከተባለች እንስት ትዳር ያስያዘው። ምንም እንኳን ረፍቃ መውለድ የማትችል መሃን ብትሆንም በባለቤቷ ያላሰለሰ...
29/10/2022

ኢስሀቅ አባቱ ኢብራሂም ዐሰ በህይወት ሳለ በ40 አመቱ ነበር ረፍቃ ቢንት በትዋዪል ከተባለች እንስት ትዳር ያስያዘው። ምንም እንኳን ረፍቃ መውለድ የማትችል መሃን ብትሆንም በባለቤቷ ያላሰለሰ ዱዓ ሁለት መንታ ልጆችን ለመታደል በቅታለች።
አንደኛው፦ ዒስ ሲሆን
ሁለተኛው፦ያዕቁብ (ዐሰ) ይባላል።

ዒስ የሮም ህዝቦች ቅድመ አያት ሲሆን፤ ያዕቁብ ደሞ የእስራኢላውያን ቅድመ አያት ነው። የሁለቱም አባት ሁለቱንም ልጆቹን በጣም ቢወዳቸውም ከያዕቁብ ይልቅ ለዒስ ግን ለየት ያለ ቦታ ነበረው። እናታቸው ረፍቃ ግን ያዕቁብ ታናሽ ስለሆነ ይበልጥ እሱን ነበር የምትወደው።

ኢስሀቅ ከእርጅና የተነሳ አይናቸው ማየት ካቆመ ትንሽ ሰንበትበት ብሏል። ከእለታት አንድ ቀን ኢስሀቅ (ዐሰ) ስጋ ያምራቸውና የሚወዱትን ልጃቸውን ዒስን አደን አድኖ ስጋ እንዲያመጣለቸው እናም ከባድ ዱዓም እንደሚያደርጉለት ነግረውት እሱም ለአደን ሄደ።

ይህን በድብቅ ስትሰማ የነበረችውም የልጆቹ እናት ረፍቃ ለያዕቁብ ነግራው ከፍየሎቹ ወፍራሙን ሙኩት እንዲያርድ ካደረገች በኋላ የወንድሙን ዒስን ልብስ አልብሳው እራሱን (ዒስን) አስመስላ የሰራውን ስጋ ለአባቱ እንዲያቀርብ አደረገች።

ያዕቁብም ያዘጋጀውን ምግብ ይዞ አባቱ ዘንድ ሲያቀርብ
አባቱ፦"ማን ነህ አንተ?" አሉት።
ያዕቁብም፦"ልጅዎት ነኝ"አለ።
አባቱም (ኢስሀቅ)፦ "ድምፅህ የያዕቁብ ነው፤ ልብስህ ግን የዒስ ነው" በማለት የቀረበላቸውን ምግብ በሉት።

ምግቡን በልተው እንደጠገቡም ምግቡን ላቀረበው አላህ ክብሩን ከፍ እንዲያደግለት፣ የበላይ ዘርም እንዲያደርገው፣ ልጆቹንም ሪዝቁንም አላህ እንዲያበረክትለት ዱዓ አደረጉ።

ልክ ዱዓውን እንዳጠናቀቁ ያዕቁብ አሚን ብሎ የአባቱን ክፍል ለቆ ወጣ። ያዕቁብም ሲወጣ ዒስ በታዘዘው መልኩ ያደነውን ስጋ ጠባብሶ ለአባቶ አመጣ'ና አቀረበ። አባቱ ግን ቅድሙኑ ጠግበዋል።

ዒስ ምግቡን ሲያቀርብላቸው፦"ልጄ ይህ ምንድነው?" አሉት።
ዒስ'ም፦ "አምጣልኝ ያሉት ስጋ ነዋ" አላቸው።
አባትየውም፦ "አሁን አምጥተህልኝ በልቼ ዱዓ አላደረግኩልህም እንዴ!!!"ሲሉት ወንድሙ ያዕቁብ እንደቀደመው እና ዱዓውንም ሸውዶ እንደተቀበለ በመረዳት ሀይለኛ እልህ ያዘው።

ዒስ ከዝያን ግዜ ጀምሮ አባታቸው ኢስሀቅ ዐሰ ከሞተ ያዕቁብን እንደሚገድለውም ይዝትበት ጀመር።ያን ግዜ አባት ለልጃቸው ዒስ ማስተዛዘኛ ይሆን ዘንድ፦"አላህ ዝርያዎችህን ጠንካሮች ያድርጋቸው፣ ፍራፍሬዎችን እና ሪዝቆቹንም አላህ ሰፋ አድርጎ ይስጥህ" በማለት ዱዓ አደረጉለት።

ነገር ግን እናት ልጇ ያዕቁብ ላይ ሚዛተው ዛቻ እረፍት ነስቷት ስለነበር የዒስ ቁጣ እስኪበርድለት ድረስ ያዕቁብን ሀራን በሚባል አካባቢ ወደሚገኘው ወንድሟ (ላባን) ላከችው።

ያዕቁብም ስንቁን ይዞ ወደ አጎቱ ላባን እየተጓዘ ሳለ መንገድ ላይ መሸበት እና አንድ ድንጋይ ተንተርሶ እንቅልፍ ተኛ። እዛው በተኛበትም በህልሙ ወደ ሰማይ መወጣጫ ይመለከታል።

በዚያ መወጣጫም መላዕክት ይወጣሉ፤ ይወርዳሉ። በዚያ መሀከልም በህልሙ አላህ፦ "እኔ አንተን እባርክሀለሁ። ዝሪያዎችህንም አበዛልሀለሁ፣ ምድርንም ላንተ እና ለዝርያዎችህ አደርጋታለሁ" አለው።

ልክ ይሄን እንዳየ ከእንቅልፉ ነቃ። ባየው ነገርም በጣሙን ተደሰተ'ና፦ "ጌታዬ አሁን ከምሄድበት በሰላም ከመለስከኝ እዚህ ቦታ ላይ ላንተ አምልኮ እሚሆን ቤት እገነባለሁ። ከሚኖረኝም ሀብት አንድ አስረኛውን ባንተ መንገድ አውላለሁ" በማለት እዛ ቦታ ላይ የሆነ ምልክት አድርጎ ስለት ገብቶ ጎዞውን ቀጠለ።

ብዙ ተጉዞ የሀራንን ምድር ደረሰ'ና ከአጎቱም ተገናኘ።ለአጎቱ ሁለት ሴት ልጆች ነበሩት አንዷ (ለያ) ስትባል ታናሿ ደሞ (ራሂል) ትባላለች::

ትንሸኛዋ ራሂል ቆንጅዬ ስትሆን ትልቋ ግን እስከዚህም ነበረ ውበቷ። ከዚያም ያዕቁብ ዐሰ ትንሸኛዋ ራሂል በልቡ መግባቷን ሲያውቅ አጎቱን ላባንን እንዲድረው ጠየቀው።

አጎቱም፦ "7 አመት በጎችን ካገድክልኝ እድርሀለሁ" በማለት ቃል ገባለት'ና ያዕቁብም ቆንጂዬዋን ራሂልን ለማግኘት ለ7 ተከታታይ አመታት እረኛ ሆኖ አሳለፈ።

የማይደርስ የለም'ና ሰባቱ አመት ተጠናቅቆ የቀጠሮው ቀን ብቅ አለ።ላባንም ድል ያለ ድግስ ደግሶ ዘመድ አዝማድ ከጠራ በኋላ ኒካህ እስሮ ሙሽሪትንም ለያዕቁብ አስረከበው።

በማግስቱ ጠዋት ላይ ጨለማው በብርሀን መገፈፍ ሲጀምር ያዕቁብ ሙሽሪትን ተመለከታት። ነገር ግን 7 አመት ለሷ ብሎ በግ የጠበቀላት ራሂል ሳትሆን ብዙም እማታምረዋ ለያ ሆና አገኛት።

ያዕቁብ በጣም ተናደደ በጠዋት አጎቱ ጋ በመሄድ፦"አንተ ቃል ኪዳንን አፍርሰሀል።እኔ የተዋዋልኩት ልጅህን ራሂልን ሁኖ ሳለ እንዴት ለያን ትሞሽርልኛለህ" በማለት ወቀሰው።

የያዕቁብ አጎትም ላባን ብልጣ ብልጥ ነበር'ና፦"ይህማ በኛ ባህል ነውር ነው። እንዴት ታላቅ እያለች ታናሽ ትዳራለች! በል ራሂልን ምትፈልግ እንደሆን ለ7 አመት በጎችን አግድልኝ" አለው።

ያዕቁብም ራሂልን በጣም ወዷት ስለነበር 7 አመታትን ለመጠበቅ ተገደደ። የማይደርስ የለም'ና ይህም ቀን ደረሰ።ያዕቁብም ለ14 አመት የጠበቃትን ራሂልን በእጁ አስገባት። (ሁለት እህትማማቾችን በአንድ ግዜ ማግባት በነሱ ህግ ክልክል አልነበረም። ከዚያ በኋላ ነው ተውራት ሲወርድ ይህ ህግ የተሻረው።)

ከዚያ ያዕቁብ ሁለት እህትማማቾችን አግብቶ ሳለ አጎቱ ላባን ለሁለት ልጆቹ ሁለት አገልጋዮችን በስጦታ መልኩ አበረከተላቸው።

ለያ ለምትባለዋ ዘልፋ የምትባል አገልጋይ ሲሰጣት ራሂል ለምትባለዋም በልሃ የምትባል አገልጋይ ሰጣት። አላህም ለያ የምትባለዋን (ፉንጋዋን) 4 ወንድ ልጆችን በመስጠት
ካሳት። ልጆቿም
1፦ረውቢል
2፦ሸምዑን
3፦ላዊ
4፦የሁዳ ናቸው።

ትንሿ ረሂል ምንም እንኳ ቆንጅዬ ብትሆንም ልጅ መውለድ ግን አትችልም። በታላቅ እህቷ መውለድ በጣም ቅናት ይይዛት'ና እራሷ ዘንድ የምትገኘውን በልሀ የተባለችውን አገልጋይ ለገዛ ባለቤቷ ዳረችው'ና አገልጋይዋም ከያዕቁብ
5፦ዳን
6፦ኒፍታሊ የተባሉ ልጆችን ወለደች።

ያን ግዜ ፉንጋዋ ለያ ከእህቷ ረሂል እልህ ተያያዘች'ና እሷም ዘልፋ የምትባል አገልጋይዋን ለያዕቁብ ዳረችለት'ና ያዕቁብም ከዘልፋ
7፦ጃድ
8፦ዐሺር የተባሉ ልጆችን ወለደችለት።

ከዚያም ለያ (ታላቋ) አምስተኛ አረገዘች'ና
9፦ያሳካር የተባለ ልጅ ወልዳ ብዙም ሳትቆይ
10፦ዛብሎን የተባለ ልጅ ደገመች። አሁንም አላረፈችም።
11፦ዲና የምትባል ሴት ልጅ ለያዕቁብ አሳቀፈችው። ያ ማለት ለያ ከያዕቁብ 7 ልጆችንና ወለደች ማለት ነው።

ይህን ስታይ መቋቋም ያቃታት ራሂል አላህን ልጅ እንዲሰጣት መማፀን ጀመረች። አላህም በሩን ያንኳኳውን በከንቱ ማይመልስ ጌታ ነው'ና ዱዓዋን ተቀብሎ
12፦ዩሱፍ (ዐሰ) የሚባል ውብ እና ትሁት የሆነ ልጅን ሰጣት።

ይህ ሁሉ የሚሆነው በአጎቱ ሀገር በሀራን ምድር ላይ ነው። አሁን ያዕቁብ የትውልድ ሀገሩን ፊለስጢንን ለቅቆ የሀራንን ምድር ከረገጠ ከ20 አመታት በላይ አስቆጥሯል።

ያዕቁብም ዐሰ አጎቱ ዘንድ በመሄድ፦"አጎቴ አሁን ፍቀድልኝ'ና ሚስት ልጆቼን ሰብስቤ ቤተሰቦቼ ጋር ልሂድ" ይለዋል።

አጎቱ ላባንም፦"ያዕቁብ እኔ ባንተ ሰበብ ብዙ ንብረቴ በረካ ሆኖልኛል።ስለዚህ የፈለግከውን ያህል ንብረት ጠይቀኝ" አለው። ላባን በጣም ለቁጥር ሚያዳግት እንስሳት ስለነበረው
ያዕቁብም፦"በዚህ አመት የሚወለዱትን ሁሉ በጎች ስጠኝ። ከተቀረው እንስሳቶችህ መልካቸው ጥቁር በነጭ የሚወልዱትንም ስጠኝ። ነጭ ዳማዎችን እና ቀይ ዳማዎችንም ስጠኝ" ብሎ ጠየቀ።
አጎቱ ላባንም፦"እሺ" አለው።

ያዕቁብም ይህን ሀላፊነት ልጆቹ እንዲወጡ አዘዘ። በመጀመርያ ያዕቁብ እርጉዝ የሆኑ እንስሳቶችን ከሌሎቹ እንስሳት የሶስት ቀን መንገድ ያህል ርቀት አራራቃቸው። ነጭ ዳማዎችን እና ቀይ ዳማዎችን እንደዚያው አራራቃቸው።

ይህን ካደረገ በኋላ እርጉዞቹም ወለዱ ያዕቁብም ድርሻውን ለይቶ በአላህ ትዕዛዝ ለጉዞ ተዘጋጀ። አሁን ያዕቁብ የብዙ ሺህ በጎች፣ እንስሳቶች፣ እና የብዙ አገልጋዮች ባለቤት ሆኗል።

ወደ ፊለስጢን ጉዞ ሲዝጀምሩ ራሂል የተባለችዋ የያዕቁብ ሚስት የአባቷን ጣኦት ደብቃ ይዛ ወጣች።

ያዕቁብ ልጆቹን፣ ሚስቶቹን፣ አገልጋዮቹን፣ እንስሳቶቹን ሁሉ ሰብስቦ በረሀውን እያቋረጠ ብዙ ተጎዞ የሀራንን ምድር ካጋመሰ በኋላ አጎቱ ላባን እና የሀራን ከተማ ነዋሪዎች ተከትለውት ደረሱበት።

ልክ እንዳገኙት አጎቱ ላባን በወቀሳ መልኩ፦"ያዕቁብ ለምን ሳትነግረኝ ትተህ ትሄዳለህ! ምነው በደስታ ተሰነባብተን ከአከባቢው ህዝብ ጋር ጨፍረን ብንሸኛቹስ" በማለት አንድ ጣኦት ይዘው እንደመጡም አክሎ ጠየቀው።

ያዕቁብ ዐሰ ምንም አይነት ከጣኦት ጋር ግንኙነት ባይኖረውም ለአጎቱ ሲል የሚስቶቹን እቃ ሀሉ ፈተሸለት ምንም አላገኘም።

ራሂል ግን ጣኦቱን ይዛው ስለነበር ለፍተሻ ፍቃደኛ አልሆነችም ነበር አሞኛል አልነሳም አለች። ያን ግዜ ያ ጣኦት ምናልባት ጀልዓድ በተባለ ዳገት ላይ ይኖራል በሚል ግምት ላባን ልጆቹን እና የእህቱን ልጅ ያዕቁብን ተሰናብቷቸው ተመለሰ። ያዕቁብ የትውልድ ሀገሩን ሊገባ ጥቂት ሲቀራው መላዕክት እየወረዱ እንኳን ደህና መጣህ እያሉት ያልፉም ነበር።

አሁን ያዕቁብ ሳዒር የምትባል ቦታ ላይ ደርሷል ግና ሀገሩ ሊገባ የወንድሙን በቀል ፈርቷል። እዛው ሆኖ እንደማለማመጥ አይነት ነገር ፅፎ ደብዳቤ ለወንድሙ ላከለት።

በነጋታው ሌላ የዛቻ ደብዳቤ የያዘች ወረቀት ዒስ (የያዕቁብ ወንድም) 400 እግረኛ ጦር አሰልፎ እየመጣ መሆኑን የሚያስረዳ መልዕክት ከወደ ፊለስጢን በኩል ለያዕቁብ መጣችለት።
ያዕቁብም ፈራ ፤ አላህንም ከወንድሙ ተንኮል እንዲታደገው ተማፀነ፤ ለአላህም ስለት ገባ።

ያዕቁብ ዐሰ ክፍል 2 ይቀጥላል

Sefwan Sheik Ahmedin

ምንጭ፦
البدايه والنهايه
الكامل في التاريخ

አሁን ዒስማኢል ዐሰ ጎርምሷል፣ ለሁሉ ነገር ብቁ የሆነ ወጣትም ሆኗል። ውሀ ፍለጋ መጥተው እዛው ከዘምዘም ምንጭ ዘንድ ኑሮዋቸውን ያደረጉት የጁርሀም ብሄረሰቦችም ኢስማዒልን እጅጉን ይወዱታልም...
29/10/2022

አሁን ዒስማኢል ዐሰ ጎርምሷል፣ ለሁሉ ነገር ብቁ የሆነ ወጣትም ሆኗል። ውሀ ፍለጋ መጥተው እዛው ከዘምዘም ምንጭ ዘንድ ኑሮዋቸውን ያደረጉት የጁርሀም ብሄረሰቦችም ኢስማዒልን እጅጉን ይወዱታልም።

ቋንቋቸውንም አስለምደውት ባህላቸውንም አላብሰውታል።ለአቅመ አዳም መድረሱን በተመለከቱም ግዜ ከራሳቸው ዘር የሆነችን እንስትም ዳሩለት።

ኢስማዒል ዐሰ ትዳር እንደያዘ እናትየው ሀጀር ብዙም ሳትቆይ ነበር ለፈጣሪዋ ነፍሷን ያስረከበችው። ኢስማዒልም ያለ አባት ያሳደገችው እናቱ ስትለየው እጅጉን ቢያዝንም ምላሹ ግን ዱዓ ብቻ ነበር።

ምንም እንኳን የኢስማዒል አባት ኢብራሂም ዐሰ በዝያ ግዜ ትልቅ ሽማግሌ ቢሆኑም የአብራካቸውን ክፋይ ለመጎብኘት ከፊለስጢን ምድር መካ ድረስ በየግዜው ይመላለሱ ነበር። ነገር ግን አሁን በዚህኛው ዙር ትንሽ ሰንበትበት ብለዋል መካ ከመጡ።

ልክ መካ እንደደረሱ ልጃቸው ቤት ሲገቡ የልጃቸውን ሚስት ከቤት ያገኟታል።ኢስማዒል የት እንዳለም ሲጠይቋት ለአደን ከከተማ እንደራቀ ነገረቻቸው።

እሳቸውም ቀጠል አድርገው ፦"ልጄ ኑሯቸሁ እንዴት ነው?" ብለው ሲጠይቋት።
እሷም፦"ኑሮዋችን በጣም ዝቅተኛ ነው"በማለት ብዙ ስሞታ አቀረበች።
እሳቸውም፦"በይ ልጄ እኔ መሄዴ ነው። ኢስማዒል ሲመጣ ሰላምታዬን አድርሺልኝ። በመቀጠልም የበሩን መዝጊያ እንዲቀይርም ንገሪው" ብለዋት ትተው ሄዱ።

ኢስማዒልም ዐሰ ከአደን ሲመለስ ሚስቱ፦"አንድ ሽማግሌ ሰውዬ መጥቶ ነበር።ሰላም በይልኝ ብሎ የበርህንም መዝግያ እንድትቀይር አዞሀል" ስትለው አባቱ መሆኑን አውቆ የበር መዝጊያ ደሞ ሚስቱን እንደሆነ በመረዳት ሚስቱን ፈታት።

ኢስማዒልም ሌላ አዲስ ሚስት አገባ።ከእለታት አንድ ቀንም የልጃቸው ናፍቆት አላስቀምጥ ያላቸው ኢብራሂም ዐሰ ከ ፊለስጢን ምድር ልጃቸውን ሊያዩ ሲከንፉ መጡ።

ቤት ሲደርሱ ሌላ ሴት ተመለከቱ'ና፦"ልጄ ኢስማዒል የት ነው" ብለው ሲጠይቋት።
እሷም፦"ለአደን ራቅ ወዳለ ቦያ ሄዷል ኑ ግቡ"አለቻቸው።
እሳቸውም፦" ኑሮዋችሁስ እንዴት ነው?" አሏት።
እሷም፦"በጣም ጥሩ ነው ሁሌ ድሎት ሁሌ ምቾት ነው" ብላ መለሰችላቸው።
እሳቸውም፦" በይ ልጄ እኔ መሄዴ ነው።ኢስማዒል ሲመጣ ሰላምታዬን አድርሺልኝ። በመቀጠልም የበሩን መዝጊያ ጠበቅ አድርጎ እንዲይዝ ንገሪልኝ" ብለዋት ሄዱ።

ኢስማዒልም ከአደን ሲመለስ ሚስቱ፦"አንድ ሽማግሌ ሰውዬ መጥቶ ነበር።ሰላም በይልኝ ብሎ የበርህንም መዝግያ ጠበቅ አድርገህ እንድትይዝ አዞሀል" አለችው። ኢስማዒልም አባቱ ይህችኛዋን ሚስቱን እንደወደዱለት ተረድቶ ይልቅ ያከብራትም ጀመር።

ለዚያ አካባቢ እና በዙሪያዋ ላሉ ነገዶች፣ ለአማሊቃዎች፣ ለጁርሀሞች እና ለየመኖች በነቢይነት ሲያገለግል የነበረው ኢስማዒል ዐሰ ቀደምት አባቶቹ የቀመሱትን የሞት ፅዋ መቅመሻው ግዜ ሲደርስ ነስማ የተባለችውን ሴት ልጁን የወንድሙ የኢስሀቅ ልጅ የሆነው ዒስ እንዲያገባት ተናዝዞ በተወለደ በ173 አመቱ የሙታንን መንደር ተቀላቀለ።

ኢስሓቅ እና ያዕቁብ ዐሰ ይቀጥላል...

Sefwan Sheik Ahmedin

ምንጭ፦
البدايه والنهايه
الكامل في التاريخ

አሁን ነፍሰ ጡሯ የኢብራሂም ሁለተኛዋ ሚስት ሀጀር ወንድ ልጅን ተገላግላለች። ይህን ግዜ ሳራ የቅናት መንፈስ ያድርባትና ኢብራሂምን ዐሰ የተወለደለትን አዲሱን ልጅ እና አዲሲቷን ሚስቱን ራቅ ...
29/10/2022

አሁን ነፍሰ ጡሯ የኢብራሂም ሁለተኛዋ ሚስት ሀጀር ወንድ ልጅን ተገላግላለች። ይህን ግዜ ሳራ የቅናት መንፈስ ያድርባትና ኢብራሂምን ዐሰ የተወለደለትን አዲሱን ልጅ እና አዲሲቷን ሚስቱን ራቅ ወዳለ በረሀ ጥሏቸው እንዲመጣ አዘዘችው።

ኢብራሂምም ሚስቱን ሀጀርን እና ልጁን ኢስማዒልን ይዞ ጉዞ ወደ በረሀ ጀመረ።ብዙ ከተጓዙ በኋላም በዐረብያ ምድር ምንም ውሀም ይሁን አረንጓዴ ነገር ከሌለበት አንድ ተራራ ደረሱ።

የያዘውንም ስንቅ አስቀምጦላቻው ኢብራሂም ወደ መጣበት ሲመለስ ሚስቱ ሀጀር፦ " በዚህ በረሀ ትተኸን እየሄድክ ነው? ወይስ አላህ አዞሀል?" አለችው።

እሱም፦"አዎ" ብሏት ጉዞ ቀጠለ። ትንሽ ሄድ አለ'ና፦ "ጌታችን ሆይ! እኔ አዝመራ በሌለው ሸለቆ ውስጥ በተከበረው ቤት አጠገብ ከዘሮቼ አስቀመጥኩ፡፡

ጌታችን ሆይ! ሶላትን ያቋቁሙ ዘንድ (አስቀመጥኳቸው)፡፡ ከሰዎችም ልቦችን ወደእነሱ የሚናፍቁ አድርግ፡፡ ያመሰግኑህም ዘንድ ከፍሬዎች ስጣቸው፡፡" ብሎ ዱዓ አደረገ'ና ወደመጣበት ለመመለስ ጉዞ ጀመረ።

ብዙ ተጉዞ ሚስቱ ሳራ ወዳለችበት አካባቢም ሲደርስ ሚስቱ ወንድ ልጅ ታቅፋ አገኛት በጣምም ተደሰተ። ያችኛዋ ሚስቱ ምንም እንኳን አየሩ ለመቋቋም በሚያዳግት መልኩ ሞቃታማ ቢሆንም፤ የያዘችውም ውሀ ቢያልቅም በህይወት ግን ከልጇ ጋር እስካሁን አለች።

ውሀ ጥም አንገብግቧታል።ምንም የቀመሰችው ነገር ባለመኖሩ ልጇ ከጡቷ ምንም አይነት ጠብታ እንኳ ሊያገኝ አልቻለም።

ህፃኑ ኢስማዒል ዐሰ ረሀቡን መቋቋም አቅቶት በጣም እያመረረ ማልቀስ ጀምሯል። እናት ሀጀርም ምን ማድረግ እንዳለባት ግራ ገብቷት ትተክዛለች።

አየሩ በጣም ሞቀታማ ነው፣ፀሀይዋ ሙሉ ብርታቷን በዛ ምድር ምታሳርፍ ነው ሚመስለው። መሬቱ ግሏል፤ ነገር ግን ምንም አማራጭ የላትምና ውሀ ፍለጋ ልጇን አስቀምጣ ከበረሀው ለመሯሯጥ ወሰነች።

ከብዙ ፍለጋ በኋላ ውሀ ልታገኝ ባለመቻሏ ያለ ውሀ ህፃኗ ጋር መመለስ አልፈለገችም'ና ከአንዱ ተራራ ወደ አንዱ ስትሸጋገር ሰፋ እና መርዋ በተባሉ ሁለት ተራራዎች ዘንድ ደረሰች በመሀከላቸው ትልቅ ሸለቆ አለ።

ከዚያ ሀጀር ውሀ ይኖራል ብላ እየሮጠች ወደ ሰፋ ተራራ ወጣች ምንም የለም። አሁንም ወደ ሸለቆው ወርዳ ወደ መርዋ ተራራ እየሮጠች ወጣች ነገር ግን አይደለም ውሀ ይቅርና እርጥበት እንኳን የለም።በዚህ ሁኔታ ከሰፋ ተራራ ወደ መርዋ ተራራ ለ7 ግዜ ውሀ ፍለጋ በሩጫ ተመላለሰች።

አሁን ሀጀር ድካሟን መቋቋም በማትችለው ሁኔታ ላይ ደርሳለች፣ጉሮሮዋ ደርቋል፣ ዳግም ውሀ ፍለጋ ተራራዎችን መውጣት ተሳናት። ከዚህ በላይ ከቆየች ልጇ እንዳይሞትባት ስለሰጋች ልጇን ወዳስቀመጠችበት ድንኳን አቀናች።

ልክ ህፃኑ ጋር ስትደርስ ህፃኑ እያለቀሰ ሲፈራገጥ በእግሩ መሬቱን ሲደበድብ ከመሬቱ ውሀ ሲወጣ ተመለከተች። ደስታዋ ወደር አጣ፤ ውሀውን ጠጥታ ልጇን አጥብታ ለጌታው ምስጋናዋን አደረሰች።

በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለች መንገደኛ ነጋዴዎች በውሀ ጥም ተቃጥለው ያንን በረሀ ሲያቋርጡ ይህን ምንጭ ይመለከቱ'ና ሀጀርን አንድ ግዜ ከፍለዋት ሊጠጡ ለመኗት። እሷም ከውሀው ፈቅዳላቸው በአፀፋው ተምር ተቀበለቻቸው። እነሱም ጠጥተው አለፉ።

እንዲህ እንዲህ እያለ በውሀ ችግር የሚታወቀው የዐረብያ ምድር በሀጀር ምንጭ ወሬው ተጥለቀለቀ። የተለያዩ የዐረብ ነገዶችም ከሀጀር አቅራቢያ እየሰፈሩ ግንባታዎችን መገንባት ጀመሩ።


ከረጅም ግዜ በኋላም ኢብራሂም ዐሰ ልጁን ኢስማዒልን ዐሰ እና ሚስቱን ሀጀርን ከምን እንደደረሱ ለማጣራት ያስቀመጣቸው ቦታ ሲመጣ ቦታውን ሊያውቅ አልቻለም።

ምክንያቱም ያኔ ሲመጣ አከባቢው ምንም አይነት ነፍስ ያለው ነገር የማይኖርበት ምድረ በዳ ነበር። አሁን ግን ህንፃዎች ተገንብተዋል የብዙ ተጓዥ ነጋዴዎችም ማረፊያ ከተማ ሆኗል።

ይህን ሲያይ መንገድ ተሳስቼ ይሁን እያለ ያሰላስል ጀመር።በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለ የአከባቢውን ሰው ሀጀር ስለምትባል ሴት ሲጠይቃቸው ከነ ቤቷ ጠቆሙት።

ኢብራሂምም ቤቷ ሲሄድ በጥሩ ሁኔታ ላይ ከልጇ ጋር ተመለከታት፣ እንባ ተናነቀው፤ ሁለቱንም ለረጅም ሰዐት አቀፏቸው ያለቅስም ጀመር።

በዚህ ሁኔታ ከተገናኙ በኋላ ኢብራሂም ወደ መጣበት ተመለሰ። ምንም እንኳን የልጁ ኢስማዒል እና የሚስቱ ፍቅር እንደ አዲስ በውስጡ ማንሰራራት ቢጀምርም በመሀከላቸው ካለው ርቀት አንፃር በፈለገ ሰዐት እየመጣ ሊጎበኛቸው ምቹ አልነበረም'ና ሁሌ በአመት አመት ሊያያቸው መምጣት ጀምሯል።

ከእለታት አንድ ቀን ኢብራሂም ተኝቶ ሳለ በህልሙ፦ "ኢብራሂም ሆይ! አላህ ልጅህን ኢስማዒልን እንድታርደው አዞሀል" የሚል ድምፅ ሰማ'ና ደንግጦ ተነሳ። ከዚያም፦"ጌታዬ ኢስማዒልን እንዳርደው ምትፈልግ እንደሆን ታዛዥህ ነኝ" ብሎ ተመልሶ ተኛ።

አሁንም እንቅልፍ ትንሽ ሸለብ እንዳደረገው፦"ኢብራሂም ሆይ! አላህ ልጅህ ኢስማዒልን እንድታርደው አዞሀል" የሚል ድምፅ በህልሙ ተሰማው። አሁንም ደንግጦ ተነሳ'ና ሁለት ረከዐ ሰግዶ አላህ ትዕዛዙን ግልፅ እንዲያደርግለት ዱዓ አድርጎ ተመልሶ ተኛ።

አሁንም ልክ እንደተኛ ለሶተኛ ግዜ፦" ኢብራሂም ሆይ! አላህ ልጅህ ኢስማዒልን እንድታርደው አዞሀል" የሚል ድምፅ ሲሰማ ኢብራሂም ዐሰ ለጌታው ታዛዥ ሆኖ ከተኛበት ተነሳ። የጌታው ትዕዛዝ ምንም እንኳን ለህሊና ሚከብድ ቢሆንም ኢብራሂም ሊፈፅም ወሰነ።

ኢብራሂምም ትዕዛዙን ሊፈፅም ጉዞ ኢስማዒል እና ሀጀር ወደሚገኙባት ቅድስት ከተማ መካ ሄደ። ልክ እንደደረስ ኢስማዒልን ብቻውን ሊያናግረው ወጣ አድርጎ፦"ልጄ አንተን እንዳርድህ ጌታዬ አዞኛል ምን ትላለህ!?" አለው።

ኢስማዒልም ዐሰ፦"ዞር በል ከዚህ ስንት አመት ጥለኸኝ የትም የትም ብዬ ካደግኩ በኋላ አባትህ ነኝ ብለህ ስትመጣ መቀበሌ አንሶህ ልረድህ ትለኛለህ እንዴ!!!" አላለውም ነበር።

ነገር ግን በእናቱ መልካም አስተዳደግ ያደግው የመልካም ስነምግባር ባለቤት የሆነው ኢስማዒል፦"አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ፈፅም እኔንም ታጋሽ ሆኜ ታገኘኛለህ" ነበር መልሱ።

አሁን ኢብራሂም ልጁን ሊያርድ ዝግጅቱን ጀምሯል።የኢስማዒልን እጅ ወደኋላ አድርጎ ካሰረ በኋላ በጀርባው ካስተኛው አይኑን ሲያይ ሆዱ አይችልም'ና በሆዱ አስተኝቶ ፊቱን ወደ መሬት በመድፋት የጌታውን ትዕዛዝ ተፈፃሚ ሊያደርግ ቢለዋውን በልጁ ኢስማዒል አንገት ላይ ሲያሳርፍ ከወደ ላይ በኩል፦"ኢብራሂም ሆይ !!! ህልሙን እውን አድርገሀል እኛም እንደዚህ መልካም ሰሪዎችን እንመነዳለን" የሚል ድምፅ መጣ።

ኢብራሂምም ቀና ሲል ከሰማይ አንድ መልዐክ ለኢስማዒል ቤዛ ይሆን ዘንድ ሙኩት ይዞ መጣ'ና፦"ኢስማዒልን ፈትተህ ይሄን እረድ" አለው።

ከዚያም ኢብራሂም ደስታው ወደር አጣ። እየተቻኮለ የልጁን የአብራኩን ክፋይ እጆች መፍታት ጀመረ። ከዚያም ከሰማይ የመጣለትን ሙኩት አረደው።

ያን ቀን በማስመልከትም ቀኑ ክብረበአል ሁኖ እንዲከበር እና በአሉም የእርድ ስነስርዐት እንዲፈፀምበት ተደነገገ።

ኢብራሂምም ወደ ሀገሩ ተመልሶ ብዙም ሳይቆይ ዳግም ሌላ ትዕዛዝ ከጌታው በኩል መጣለት፦"ከልጅህ ጋር በመሆን ልጅህ በሚገኝባት ከተማ እኔ ምመለክበትን ቤት (ካዕባ) ስራ" የሚል ነበር ትዕዛዙ።

ኢብራሂምም ለጌታው ታዛዥ በመሆን ወደ ልጁ ሄዶ ሲያማክረው ልጁም ሀሳቡን ተቀብሎ የግንባታ መሳርያዎችን አሰባስበው ግንባታ ጀመሩ።

ኢብራሂም እላይ ሆኖ ሲመርግ ኢስማዒል ደሞ ከታች ድንጋይ ያቀብለው ነበር።በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ፦"ጌታችን ሆይ! የምንሰራውን ተቀበለን አንተ ሰሚም አዋቂም ነህ" በማለት ዱዓ ያደርጉ ነበር።

አሁን የታዘዙትን ቤት ሰርተው አጠናቀዋል ኢብራሂምም ከቤቱ ጎን በመቆም፦" ጌታዬ ሆይ! ይህንን አገር (መካን) ጸጥተኛ አድርገው፡፡ እኔንም ልጆቼንም ጣዖታትን ከመገዛት አርቀን።

ለእዚያ ከሽምግልና በኋላ ኢስማዒልን ኢስሐቅንም ለእኔ ለሰጠኝ አላህ ምሰጋና ይገባው፡፡ ጌታዬ ልመናን በእርግጥ ሰሚ ነውና።

ጌታዬ ሆይ! ሰላትን አዘውትሬ የምሰግድ አድርገኝ፡፡ ከዘሮቼም (አድርግ)፡፡ ጌታችን ሆይ! ጸሎቴንም ተቀበለኝ። ጌታችን ሆይ! ለእኔም ለወላጆቼም ለምእመናንም ሁሉ ምርመራ በሚደረግበት ቀን ማር" በማለት ዱዐ አደረገ።

ይህን ትልቅ ቤትም ገንብተው ካጠናቀቁ በኋላ አላህም ኢብራሂምን፦ "ሰዎች ከየሀገሩ በመምጣት ቤቴን ይጎብኙ ዘንድ ተጣራ" አለው። ኢብራሂምም፦"ጌታዬ እኔ ደካማ ባሪያህ ነኝ ድምፄ አይደርስም" አለው።

አላህም፦"አንተ ተጣራ ማድረስ የኔ ስራ ነው" አለው። ኢብራሂምም ትልቅ ተራራ ላይ በመውጣት ተጣራ።ያን ግዜ ከየሀገሩ ያሉ ህዝቦች ጥሪውን በመቀበል መካ መጥተው ሞሉ። ኢብራሂምም የሀጅን ስነስርዐት ለሁሉም አስተማራቸው።

ከዚያ በኋላ የኢብራሂም ሚስት ሳራ በከንዐን ምድር ሀብሩን በምትባል ቦታ በ127 አመቷ ዱንያን ተሰናበተች። ከዚያ በኋላ ኢብራሂም ለሳራ ልጅ ኢስሀቅ ሪፍቃ ቢንት በቱኢል የተባለችን እንስት አጭቶለት አጋባው።

ከዚያም ኢብራሂምም ለራሱ ቀንጡራ የተባለችን ሴት በማግባት
1፦ዙምራን
2፦የቅሻን
3፦ማዳን
4፦መድየን
5፦ሺያቅ
6፦ሸውህ የተባሉ ልጆችን ወለዱ።

በመጨረሻም በ200 አመታቸው ኢብራሂም ዐሰ ዱንያን ተሰናበቱ። ዐለይሂ ሰላቱ ወሰላም

ኢስሀቅ፣ ኢስማዒል እና ያዕቁብ ይቀጥላል...

Sefwan Sheik Ahmedin

ምንጭ፦

البدايه والنهايه
الكامل في التاريخ

Address

Addis Ababa

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ኢቅራዕ TUBE posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share