24/09/2026
የቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት አዋጅ እና የተቋማት ዝግጁነት ምን ይመስላል?
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የሀገራችንን የሳይበር ደህንነትና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ እና የቁልፍ መሰረተ ልማቶችን ከሳይበር ጥቃት ለመጠበቅ የሚያስችለውን የቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት አዋጅ ቁጥር 1426/2018 ማውጣቱ ይታወቃል።
ይህ አዋጅ በሀገራችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ሚና ያላቸውንና የጥቃት ሰለባ ቢሆኑ በሀገር ህልውና፣ በብሔራዊ ደህንነት እንዲሁም በሰላምና መረጋጋት ላይ ከባድ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ 12 ዋና ዋና ዘርፎችን በቁልፍ መሰረተ ልማትነት ለይቷል።
እነዚህም የተለዩት ዘርፎች፦ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ኮሙኒኬሽን፤ የፋይናንስ፤ የፀጥታና ደህንነት፤ የትራንስፖርት፤ የትምህርት፤ የጤና፤ የውሃና ኢነርጂ፤ የመንግሥት አገልግሎቶች፤ የአደጋ መከላከል አገልግሎቶች፤ ግብርና፤ ንግድ፤ እና ኢንዱስትሪ ናቸው።
አዋጁ በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የ1 ዓመት የቅድመ ዝግጅት ጊዜ (Grace Period) የተሰጠ በመሆኑ፣ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደ ሕግ ትግበራ ከመገባቱ በፊት በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም በእያንዳንዱ የቁልፍ መሰረተ ልማት ዘርፍ ላይ ያተኮረ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሁፎችን በገጻችን ማቅረብ እንጀምራለን።
በእነዚህ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሁፎች ውስጥ የምንዳስሳቸው ጉዳዮች፦
🔹 የዘርፎቹ ልዩ የሳይበር ባህሪና ተጋላጭነት፦ እያንዳንዱ ዘርፍ ያለው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የተሳሰሩ የኔትወርክ መዋቅሮች እና የሚጋረጡበት ልዩ የሳይበር ስጋቶች፤
🔹 የሳይበር ጥቃት ቢደርስ የሚያስከትለው ጉዳት፦ በየዘርፉ ላይ የሚሰነዘር የሳይበር ጥቃት የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳቶች እንዲሁም በሀገር ህልውናና ሉዓላዊነት ላይ ያለው ከባድ እንድምታ፤
🔹 የ1 ዓመት የቅድመ ዝግጅት ጊዜ (Grace Period) ትኩረቶች፦ ተቋማት በተሰጣቸው የዝግጅት ጊዜ ውስጥ ማሟላት የሚገባቸው አሰራሮች፣ የቴክኖሎጂ ደህንነት ፍተሻዎች እና ድርጅታዊ መዋቅሮች፤
🔹 የቁልፍ መሰረተ ልማት ባለቤቶች ግዴታዎች፦ የሳይበር ደህንነት ፕሮግራሞችን መቅረጽ፣ የብቃት ማረጋገጫ ያላቸውን ባለሙያዎች መቅጠር፣ የብሔራዊ ማዕቀፎችና ስታንዳርዶች ትግበራ፣ የሳይበር ኦዲት ማድረግ እና የቴክኖሎጂ ምርቶች ደህንነት ማረጋገጫ (Inspection & Evaluation Certificate) መያዝ፤
🔹 የአደጋ ስጋት ምላሽ እና የሪፖርት አቀራረብ ግዴታ፦ የሳይበር ክስተት ሲያጋጥም በ48 ሰዓታት ውስጥ ለብሔራዊ ድንገተኛ የኮምፒውተር አደጋ ምላሽ መስጫ ማዕከል (CERT) የማሳወቅና አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ የመውሰድ ግዴታዎች፤
🔹 የፈንድ አደረጃጀትና አቅም ግንባታ፦ ለቁልፍ መሰረተ ልማቶች ደህንነት መጠበቂያ የተቋቋመው የቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት ፈንድ ዓላማ እና አጠቃቀም፤
🔹 ሕጋዊ ተጠያቂነትና አስተዳደራዊ እርምጃዎች፦ በአዋጁ የተቀመጡ ግዴታዎችን አለመወጣት የሚያስከትላቸው አስተዳደራዊ ቅጣቶች እና የወንጀል ተጠያቂነቶች።
በመሆኑም የቁልፍ መሰረተ ልማት ተቋማት አመራሮች፣ የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎች እና ለመላው የገጻችን ተከታታዮች እነዚህን ተከታታይ ጽሁፎች በመከታተል፣ በማንበብ እና ለሌሎች በማጋራት የሀገራችንን የሳይበር ደህንነትና ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ሂደት የበኩላችንን ድርሻ እንወጣ፡፡
ተጨማሪ የሳይበር ደህንነት መረጃዎችን ለማግኘት፡-
• ድረ ገጽ፦ https://www.insa.gov.et
• ፌስቡክ፡- https://web.facebook.com/INSA.ETHIOPIA
• ቲክቶክ፡- https://www.tiktok.com/?_t=8qBKkyp092r&_r=1
• ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com//featured
• ቴሌግራም፦ https://t.me/insagovet
• ትዊተር (X) ፦ https://twitter.com/INSAEthio
• ሊንክድኢን:- https://www.linkedin.com/.../information-network.../
• የሳይበር ጥቃት ጥቆማ ለመስጠት፡- ነጻ የስልክ መስመር 933