05/08/2025
‹‹…በጎጃም መሬት በጣና ደሴት ዳጋ ከሚባል አገር ገቡ፡፡››
-------------------------------------
አለቃ ተክሌ ታዋቂ ሠዓሊና ቀራጺ ሲሆኑ ከዚህ በሻገር በታሪክ ጸሐፊነታቸውም ይታወቃሉ፡፡የታሪክ ጽሑፎቻቸው እነ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያው፣ብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ፣አለማየሁ ሞገስ፣ሮጀር ካውሊና ሌሎች ጸሐፍት ላሳተሟቸው የታሪክና የስነ ጽሑፍ ስራዎች በምንጭነት አገልግለዋል፡፡አለቃ ተክሌ ሁለት መጽሐፎችን ለትውልድ አበርክተው አልፈዋል፡፡የመጀመሪያው ስራቸው‹‹የጎጃም ትውልድ በሙሉ፣ከአባይ እስከ አባይ›የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹የጎጃም ታሪከ ነገስት››በመባል የሚታወቀው በኋላ በዶክተር ስርግው ገላው አማካኝነት ሀተታ ተሰርቶለት‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› በሚል ርዕስ ለህትመት የበቃ ስራቸው ነው፡፡
የመጀመሪያ የጽሑፍ ስራቸው የሆነው‹‹የጎጃም ትውልድ በሙሉ፣ከአባይ እስከ አባይ››የተሰኘው መጽሐፋቸው 11(አስራ አንድ) ዓመታትን የፈጀ ጥናትና ምርምር ተደርጎበት በ1889 የተጠናቀቀ የጎጃምን ትውልድ የሚያትት ስራ ነው፡፡አለቃ ተክሌ መጽሐፉን ሲያዘጋጁ በዘመናቸው የነበሩ ታሪክ አዋቂ ሽማግሌዎችንና በየገዳማቱ የሚገኙ ጥንታዊ መጽሐፍትን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመዋል፡፡ይህ ስራቸው በግርማ ጌታሁን ተዘጋጅቶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ አማካኝነት በ2003 ዓ.ም ለህትመት በቅቷል፡፡
አለቃ ተክሌ የጎጃምን የግዛት ወሰን አስመልክቶ በዝርዝርና በሰፊው በሁለቱም ስራዎቻቸው የገለጹ ሲሆን ለዛሬ ‹‹የጎጃም ትውልድ በሙሉ፣ከአባይ እስከ አባይ››በሚለው መጽሐፋቸው የጎጃም ንብረት ስለሆነው ጣና ሀይቅ ያሰፈሩትን ላካፍላችሁ፡፡አለቃ ተክሌ ከታች ያሰፈርኩላችሁን ቅንጫቢ ታሪክ የጻፉት የጎጃምን ደግነት ለማሳየት ቢሆንም ቅንጫቢው የጣና ሀይቅ ፣ በአጼ ዘርዓ ያቆብ ጊዜም(1434–1468) ሆነ ከዚያ በፊት የየትኛ ግዛት አካል እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡
‹‹…….አጼ ዘርዓ ያቆብ ከሞቱ በኋላ አጽማቸው በዋሻ ተቀምጦ ሳለ እንደ ቀዳሚ ሰማዕት እስጢፋኖስ ዳ እያለ ይናገር ነበር፡፡ዳ እያለ መናገሩ በየቀኑ ቢያስቸግር እግዚአብሄር የሚያርፉበትን ቦታ ቢያመለክተን ሲሉ አሽከሮቻቸው አጽማቸውን በሳጥን ይዘው አገር ላገር ይዞሩ ጀመር፡፡ወህኒ በሚባለው አገር ሰባት አመት ከተቀመጡ በኋላ ግን ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሄር አመለከታቸውና በጎጃም መሬት በጣና ደሴት ዳጋ ከሚባል አገር ገቡ፡፡ከዚያ ቦታ አጽማቸው ሲደርስ ዛቲ ይእቲ ምዕራፍየ ለአለም(ማረፊያ ስፍራየ ይቺ ናት)ብለው ተናገሩ፡፡ከዚህ በኋላ አሽከሮቻቸው ደጉ ቦታ ይህ ነው ሲሉ ዳጋ እስጢፋኖስ አኖሯቸው፡፡የጎጃምን ደግነት እንኳንና በህይወት ያሉት ነገሥታት፣የሞቱትም እንዲህ ይመሰክራሉ፡፡›› ገጽ 34-35
በዚህ ቅንጫቢ ታሪክ ሶስት ዘመናትን እናገኛለን፡-
1.የመጽሐፉ ጥናት ከተጀመረበት 1878 እስከ ተጠናቀቀበት 1889 ያለውን(የዛሬ
133 ዓመት)
2.የአጼ ዘርዓ ያቆብ ዘመንን(1434–1468) ና
3.ከአጼ ዘርዓ ያዕቆብ በፊት የነበረውን
የአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ቀጥታ በታሪኩ ሲገለጽ፣ መጽሀፉ የተጻፈበትና ከአጼ ዘርዓ ያዕቆብ በፊት የነበረው ዘመን ደግሞ በጸሐፊው አዘጋገብ ተገልጽዋል፡፡በነዚህ የታሪክ ዘመናት ሁሉ ጣና ሀይቅ የጎጃም ግዛት አካልና ንብረት እንደሆነም ጽሑፉ ላይ በማያወላዳ መልኩ ሰፍሮ ይገኛል፡፡‹‹....በጎጃም መሬት በጣና ደሴት ዳጋ ከሚባል አገር ገቡ፡፡››