St.George United Engineers

St.George United Engineers It focuses on general construction and consultancy services

05/05/2020

መረጃው ከ (Ethiopian Press Agency /የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/) የተገኘ ነው።

ዘመን ተሻጋሪው የነጻነት ሐውልት ዛሬም በቦታው ነው
‹‹ያለ አገር ክብርና ነጻነት አለመኖሩን ተረድተው የጠላት መሳሪያ ከመሆን መከራና ስደትን መርጠው አምስት ዓመት ሙሉ ተስፋ ባለመቁረጥ ሲንገላቱና ሲንከራተቱ ለኖሩ ስድተኞች የቆመ መታሰቢያ›› ሲል በነጻነት ሐውልት በአንደኛው አምድ ላይ ተፅፏል::
በሌላኛው አምድ ላይ ደግሞ ‹‹ከጠላት ጋር ተስማምቶ ከመኖር ሞትን መርጦ በጦር ሜዳ ላይ የሚገባውን ሰርቶና ደሙን አፍስሶ፤ አምስት ዓመት ሙሉ ሲታገልና ሲሟገት በስደት ላይ ኖሮ እንደገና ከእግዚአብሄር ጋራ በድል አድራጊነት ጠላትን አባርሮ ሰንደቅ ዓላማችንን ለመለሰልን ለቀዳማዊ ኃይለስላሴ የዘላለም መታሰቢያ›› ይላል::
‹‹አምስት ዓመት ሙሉ በጠላት የጭቆና ቀንበር ውስጥ ተቀምጠው የሞት ጥላ በራሳቸው ላይ እያንዣበበ ሐሳባቸውን ከአርበኞችና ከስደተኞች ሳይለዩ አገራቸውን በስውር ላገለገሉ የውስጥ አርበኞች የቆመ መታሰቢያ›› ሲልም እንዲሁ በሌላኛው አምድ ላይ ተጽፎ የሚነበብ ሲሆን፣ ‹‹ለአገራውቸው ነጻነት አምስት ዓመት ሙሉ በዱር በገደል እየተንከራተቱ ደማቸውን ላፈሰሱና አጽማቸውን ለከሰከሱ ለስመ ጥሩ አርበኞች የቆመ የዘላለም መታሰቢያ›› ሲል ደግሞ በአራተኛው አምድ ላይ ሰፍሮ የሚነበብ ዘመን ተሻጋሪ ጽሁፍ ይስተዋላል::
ከእነዚህ ዘመን ተሻጋሪ ጽሁፎች ከፍ ብሎ ወጥ በሆነውና የሐውልቱ ዋና አምድ ዙሪያ ደግሞ የተጻፈው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ገብተው በቤተ መንግስታቸው የተናገሩት ዲስኩር ሲሆን፣ የጽሁፉ ዋና ርዕስም ‹‹የአገሬ የኢትዮጵያ ህዝብ፤ በተለይም የታመናችሁ አርበኞች›› የሚል ነው::
ይህ በአራት ኪሎ አደባባይ በኩራት የቆመው የነፃነት ሐውልት የተሰራው ጣልያን ኢትዮጵያን ለአምስት ዓመታት ይዟት በነበረ ወቅት ህይወታቸውን ለገበሩ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ነው:: በየዓመቱ ሚያዝያ 27 የሚከበረው በዓል ዘንድሮ ለ79ኛ ጊዜ ሲሆን፣ ይህም በዓል ‹‹የአርበኞች የድል በዓል›› በሚል የሚታወቅ ነው::
ዛሬ በአራት ኪሎ አደባባይ በዓለም አቀፍ በተከሰተው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መሰባሰብ ባይኖርም፤ እንደወትሮው ለበዓሉ ድምቀት ይሆን ዘንድ በዓሉን ሊዘክሩ የሚችሉ የተለያዩ ዝግጅቶችና ጀግኖችን የሚያወድሱ የጎዳና ላይ ትርዒቶች ባይዘጋጁም፤ ታላቅ መስዋዕት መክፈላቸውን ሁሌም የሚያሳይ፤ የፋሽስቶችን የወራሪነት እና የቅኝ ገዢነት፤ የቂምና የበቀል እርምጃ ያፈረሰ፣ የኢትዮጵያውያንን ጽናት፣ አይበገሬነትና አንድነት ዳግም ያረጋገጠ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ክስተት የሆነውን ታሪክ የሚያስታውስ ዘመን ተሻጋሪው የነጻነት ሐውልት ግን ዛሬም በቦታው ነው:: ጽሁፉን ከተለያዩ መረጃዎችና ከራሱ ከነጻነት ሐውልቱ አሰባስበን የተጠናቀረ ነው::

16/04/2020

በሕማማት ሳምንት በየዕለቱ የተፈጸሙ ምሥጢራ ክፍል አራት
✞✞✞
(Mahibere Kidusan - ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል)
✞✞✞
ጸሎተ-ሐሙስ በዚህ ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ስላደረ ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡ በትሕትና፣ በፍቅር፣ በመታዘዝና በማገልገል አርአያ ለመሆን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም ይጠራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ «እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ እንዲህም አላቸው ያደረግሁላችሁን ታስተውሉታላችሁን?... እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል”(ዮሐ.፲፫፣፲፪-፳) በማለት እንደገለጠው፡፡ ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ በማለት ምስጢረ ቍርባንን የጀመረበት ቀን በመሆኑ የምሥጢር ቀን ይባላል። በዚህም የሰው ልጆች ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ከእርሱ ጋር አንድነትና ኅብረት እንዲኖረን ጥንተ ጠላት ዲለብሎስንም ፍጹም ድል ነሥተን ሰማያዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን፡፡ አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ በእነርሱ ጥበብና ፍላጐት ቀስ ብለው መጥተው የያዙበት ቀን ስለሆነ በዚህ ዕለት ጩኸት ሳይሰማ የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ ስለሆነም ሕዝበ ክርስቲያን የሕጽበት፣ የምሥጢር፣ የጸሎት ቀን በሆነው ዕለት በንስሓ ታጥበን ሥጋና ደሙን እንድንቀበል ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ ሕጽበተ እግር፡- የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ጌታ በፍጹም ትሕትና የደቀመዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ሕይወት ማኅተም የሆነውን ምሥጢረ ቍርባን ያከናወነበት ነው፡፡ እናንተም ለወንድማችሁ እንዲህ አድርጉ ሲል ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል፡፡ ይህ የሚያሳየው እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጠኋችሁ የተባለውን ነው። እውነት እውነት እላችኋለሁ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፤ ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ (ዮሐ.፲፫፣፲፮-፲፯) በማለት ትሕትናውን አሳይቷል፡፡ ጌታ በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር ሲያጥብ እኔ መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኳችሁ ምሳሌውን አሳየኋችሁ፡፡ ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ለሞት አሳልፎ ይሰጠኛል አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም እኔ እሆን? እኔ እሆን? ተባባሉ፡፡ ጌታም ኅብስት ቆርሼ፣ ከወጡም አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው አላቸው፡፡ ይሁዳን ማመልከቱ ቢሆንም ስለማን እነደተናገረ አልገባቸውም። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ትሕትናን ካስተማራቸው በኋላ፤ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመስጠት የኦሪትን መሥዋዕት የሻረው እና መሥዋዕተ ሐዲስን የሠራው በዕለተ ሐሙስ ነው፡፡ በዚህ ሃይማኖታዊ መነሻነትም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚከናወን ትውፊት አለ፡፡ ከጉልባን በተጨማሪ በተለይ በጸሎተ ሐሙስ ብቻ የሚጋገር የተለየ ዳቦ አለ፡፡ ይህ ልዩ ዳቦ በወሎ ትኩሴ፣ በጎንደር ደግሞ ሙገራ ይባላል፡፡ ዳቦው ጌታ ለሐዋርያት የሰጣቸው ኅብስት ምሳሌ ነው። ከዚህ ቀን ውጪ በሌላ ጊዜ እንዲህ አይነት ዳቦ አይጋገርም፡፡ ሰው ሁሉ ዳቦውን ለመብላት የሚጠባበቀው በታላቅ ጉጉት ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በሚከበርባቸው እንደ ማኅበርና ሰንበቴ በመሳሰሉት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ትውፊቶች የሚቀርብበት ጊዜ አለ፡፡ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስበከት በሚገኘው ይምርሐነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ጣርያ ላይ ካህኑ ትኩሴ ዳቦ ሲባርክ የሚያሳይ ሥዕል አለ፡፡ በትግራይ በዕለተ ስቅለት ከተለመደው የጾምና የስግደት ሥርዓት በተጨማሪ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ በዕለቱ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት መታሰቢያ ሲባል ወንዶች ልጆች በሙሉ ጸጉራቸውን እንዲላጩ ይደረጋል፡፡ ያን ቀን ያልተላጨ ልጅ ኃጢአት ይሆንበታል ስለሚባል ሳይላጭ የሚውል የለም፡፡ ልጃገረዶች ደግሞ በዛፍ ላይ ገመድ በማሰር ዥዋዥዌ ይጫወታሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት የጌታን መንገላታት ለማዘከር ነው ይባላል፡፡ እነሆ ይህንን ዕለት በማስታወስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ እስከ ቀሳውስት ያሉት አባቶች በየደብራቸው በመዓርግ ከእነሱ የሚያንሱ የካህናትን፣ የዲያቆናትን እና የምእመናንሠን እግር ያጥባሉ። የሚያጥቡትም የወይራና የወይን ቅጠል በውኃ በመዘፍዘፍ ነው፡፡

03/08/2019

( Ethio 360 Media)
ምኒልክን አለማወቅ ይቻላል ....
-... ግን! የመጀመሪያውን ባቡር፣ የቀደመውን መኪና፣ አንድ ብሎ የጀመረውን አስኳላ ማወቅ ምኒልክን ማወቅ ነው፡፡ ነጭና ጥቁር እኩል ነው ብሎ ማመን፣ ጥቁር ነጭን ድል እንዳደረገ መስማት፣ የመጀመሪያው ሆስፒታል ሪፈር ተጽፎ መምጣት ምኒልክን ማወቅ ነው፡፡
****
(ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ)
-
ሰሞኑን አንድ ሰው ምኒልክን አላውቅም አለ ተብሎ እዚሁ መንደር ከዚህም ከዚያም የሚባለውን አደመጥሁ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለች ከዛሬዋ ይልቅ በትናንትናዋ በምትመካ ሀገር # ምኒልክን አለማወቅ ብዙ አይገርምም፡፡ ምክንያቱን ታላቁ ነገስ ከታላላቅ ነገሮች ጀርባ አሉና፡፡
በምኒልክ ባቡር ተሳፍሮ መጥቶ የምኒልክ ሚስት የቆረቆሯት ከተማ የገባ ምኒልክን ባያውቅም አውቋቸዋል፡፡ ምኒልክ የትም ያሉ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ናቸው፡፡ ፖስታ ቤቱ በር ላይ የቆመ ሰው ፖስታና ኢትዮጵያ ማን አስተዋወቃቸው ብሎ ሲያሰላስል እየመረረው ከምኒልክ ይተዋወቃል፡፡
ጅማ ከተማ ቆሞ ጅሬን አሻግሮ የሚመለከት ሰው ሳይፈልግ በግድ አባ ጅፋርን ያስብና ከማይነጥላቸው ንጉሥ ጋር ያስተሳስራቸዋል፡፡ ያኔ ምኒልክን ለማሰብ ጤናማ አእምሮ ብቻውን በቂ ነው፡፡ ጅማን ልለፍ ያለ ቤኒሻንጉል ገብቶ አሶሳ ሲደርስም እንዲሁ ሼህ ሆጀሌን አስታውሶ ሊዘላቸው የማይችል ንጉሥ ፊቱ ድቅን ይላሉ፡፡ እኒያ ንጉሥ ምኒልክ ናቸው፡፡
ነቀምቴ ያለ ሰው የኩምሳ ሞሮዳን ቤተ መንግሥት እንደምን አላውቀውም ይላል፡፡ ከዚያ ቤተ መንግሥት መኳንንቶች ጀርባ ሸዋ የነበሩ የሀገር ንጉሥ ማስታወስ ደግሞ የአእምሮ ጤንነትን ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡
በየቀኑ ምኒልክ ሆስፒታል ሪፈር ሲባል የሚውል ታካሚ የሆስፒታሉን በር ጽሑፍ ማንበብ ባይሻ ካርዱ ላይ የሠፈረው ስም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሆስፒታል እየታከመ እንደሆነ ይነግረዋል፡፡ ያ ስም ምኒልክ ነው፡፡
ምኒልክን አለማወቅ ስምን የመርሳት ያክል መብት ነው፡፡ ስሙን የረሳ ሰው ስም የለውም ማለት አይደለም፡፡ ስሙን የረሳ ሰው ራሱን ከመርሳት ያለፈ ሌላ በደል በማንም ላይ አልፈጸመም፡፡
ምኒልክን መርሳት ይቻላል፤ ዓለምን አታስታውሱኝ ማለት ግን ሞኝነት ነው፡፡ ዓለም ጥቁር ለነጻነቱ የከፈለውን የድል ታሪክ ከምኒልክ ስም ጋር አቆራኝቶ ይገልጸዋል፡፡ # አድዋ የትም ጥቁር ልብ ያለ የነጻነት ታሪክ ነው፤ እንደ ሃያ ዓመት የሀሰት ታሪካችን ምኒልክን ከአድዋ ነጥለን እንይ ብንል ዓለም በዓይናችን ጣልቃ ባይገባም በዓይኑ ደግሞ አያስገባንም፡፡
ምኒልክን ማወቅ ግድ አይደለም፡፡ በስልክ ሽቦ የመገናኘት ቴክኖሎጂን ያወቀ ኢትዮጵያ ያኔ ቀድመው ያስተዋወቁትን ንጉሥ እንዳወቀ ይቆጠራል፡፡ ምኒልክን ማወቅ ግዴታ አይደለም፤ ሆቴል ተቀምጦ ባላውቃቸው ላለ የመጀመሪያውን ሆቴል ሲያስታውስ ከመቅጽበት ተዋውቋቸዋል፡፡
ምኒልክን ማወቅ ግዴታ አይደለም፤ ምኒልክን አላውቃቸውም ብሎ ለዓለም ነግሮ ፊደል ቆጥሬያለሁ ማለት ግን ያስቅበታል፡፡ የመጀመሪያው አስኳላ መስራች ቀለም ለቆጠረ ዓለም ሁሉ እውቅ ንጉሥ ናቸውና፤

23/08/2018

አትውረድ
(በዲያቆን ዳንኤል ክብረት)
አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር በዋናው በር በኩል ወደ አውራ ጎዳናው ይወጣል፡፡
ጥቂት እንደተጓዘ ደግሞ እዚያ አካባቢ ቆመው አላፊ አግዳሚውን ከሚላከፉ ጎረምሶች ጋር
ይጨቃጨቃል፡፡ ጭቅጭቁ በምን እንደተጀመረ ማናችንም አላወቅንም፡፡ እነዚያ ጎረምሶች
ግን በመምህሩ ላይ ‹ሙድ› ይዘውበታል፡፡ ‹እሺ - - ሊቁ› እያሉ በስድብ ጠረባ
ይረፈርፉታል፡፡ እርሱ ደግሞ ስድቡን አልቻለበትም፡፡ ‹‹ያልተማራችሁ፣ ማይሞች፣ ከስድብ
በቀር ሌላ የማታውቁ፣ ደደቦች›› ይላል ሥሩ እስኪገታተር ድረስ በቁጣ፡፡ በትከሻው
ያንጠለጠለው ቦርሳ ይወዘወዛል፣ መነጽሩም ልውደቅ ልውደቅ ይላል፡፡
‹‹እሺ ሊቁ፣ ለምን ላፕቶፕሺን ከፍተሺ ዕውቀት አትጭኝብንም›› እያሉ ጎረምሶቹ
ይሳሳቁበታል፡፡እርሱ ይበግናል፡፡ ‹ኤፍ ብቻ ነው እንዴ ቦርሳሽ ውስጥ የያዝሺው፤ በናትሺ
አንድ አምስት ኤ የለሽም›› ይሉታል፡፡ እርሱ ይንዘፈዘፋል፡፡ ‹‹አንድ ሁለት ኤ ብትሰጭን ቸብ
አርገን በርጫ እንገዛበት ነበር›› ይሉታል፡፡ ሰው እየተሰበሰበ፣ እየከበበው ይሄድና
የጎረምሶቹን ስድብ እንደመዝናኛ ቆጥሮት አብሯቸው ይሳሳቃል፡፡ እርሱን ኮሜዲ ፊልም
እንደሚሠራ ተዋናይ ቆጥረውት በነጻ ይኮመኩማሉ፡፡ ጎረምሶቹ አንድ ተረብ በወረወሩ ቁጥር
ከብቦ የተሰበሰበው ‹አስገቡለት› እያለ እንደ ጎጃም ልቅሶ ያጅባቸዋል፡፡
እየቆየ ከበባው እየሰፋ፣ ሳቁ እየደራ፣ የመምህሩ ንዴት ወደ እሳተ ገሞራነት እየተቀየረ ሄደ፡፡
መምህሩ ከዚያ ከበባ ልውጣ ቢል እንኳን ሰው በጎረምሶቹ ተረብ ስለተዝናና በቀላሉ
የሚያስወጡት አይመስልም፡፡ የተከፈለው አዝማሪ መስሏል፡፡ የሚያውቃቸው ስድቦች
አልቀውበት አሁን ጣቱን ማውጣትና ‹‹አሳይሃለሁ›› እያለ መዛት ጀምሯል፡፡ የአንዳንድ
የእንግሊዝኛ ስድቦችን ሲሳደብም
የኛ ሙሽራ ኩሪባቸው
በእንግሊዝ አናግሪያቸው›› ብለው ሳቁበት፡፡ በልቡ አንዳች የፖሊስ ኃይል መጥቶ
እንዲገላግለው እየተመኘ ነበር፡፡ ወደ ስድቡ ሜዳ አስቦ ስላልገባ አስቦ ሊወጣ አልቻለም፡፡
በዚህ መካከል በግራ እጃቸው ጋዜጣ አጣጥፈው የያዙ አንድ አዛውንት ሁላችንንም
እየገፈተሩ፣ እንደ ሙሴ የሕዝቡን ባሕር ለሁለት እየከፈሉ ወደ መካከል መጡና ያንን
መምህር እጁን ይዘው በዝምታ ጎትተው ከከበባው አወጡት፤ ጎረምሶቹም ‹ሼባው ልቀቀው
እንጂ›› እያሉ ተረቧቸው፡፡ እርሳቸው ቀናም አላሉ፣ መልስም አልሰጡ፡፡ እየሰነጠቁ
እንደገቡ፣ እየሰነጠቁ ወጡ፡፡
ከዚያም ወደ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን መታጠፊያ ዘወር አደረጉትና ‹‹ለምን ልጄ፣ ለምን?››
አሉት፡፡
‹‹ከዩኒቨርሲቲ ስወጣ ለከፉኝ፣ እኔም መልስ ሰጠኋቸው››
‹‹ተማሪ ነህ?››
‹‹የዩኒቨርሲቲ መምህር ነኝ››
‹‹እና መምህር ሆነህ ነው ከእነርሱ ጋር ስድብ የገጠምከው፤ ጥፋተኛው አንተ ነህ›› አሉት፡፡
እኛ ትንሽ ራቅ ብለን የሚሉትን መስማት ጀመርን፡፡
‹‹ተመልከት እዚያ›› አሉት በአመልካች ጣታቸው ወደ አንበሳ ግቢ አቅጣጫ እያመለከቱ፡፡
‹‹እዚያ ግቢ ውስጥ ምን አለ?›› አሉና ጠየቁት፡፡
‹‹አንበሳ ነዋ››
‹‹አንበሳ ግን መኖሪያው ግቢ ውስጥ ነው እንዴ?››
‹‹አንበሳማ የዱር እንስሳኮ ነው፤ ምን ዓይነት ጥያቄ ነው የሚጠይቁኝ፤ የዩኒቨርሲቲ
መምህር ነኝ እያልኩዎ›› መምህሩ ተናደደና ጥሏቸው ሊሄድ ከጀለ፡፡ እርሳቸውም ከእናቱ
ጋር መንገድ እንደሚሻገር ሕጻን እጁን አጥብቀው ያዙት፡፡ ‹‹ወዳጂ፣ ሰው በሁሉም ነገር
ሊቅ አይሆንም፡፡ በአንዱ ሊቅ ሲሆን በሌላው ማይም ነው፤ በአንዱ መምህር ሲሆን በሌላው
ተማሪ ነው፤ በአንዱ ጎበዝ የሆነ ለሌላው ሰነፍ ነው›› አሉት፡፡ ትንሽ ቀዝቀዝ አለ፡፡
‹‹አንበሳው በገዛ ጫካው ውስጥ ቢሆን ኖሮ ማን ይደፍረው ነበር? ማን ጀግና ነበር ሃምሳ
ሳንቲም ከፍሎ በሃምሳ ሜትር ርቀት የሚያየው? ማን ጀግና ነበር ቀርቦ ፎቶ የሚያነሣው?
ማን ጀግና ነበር ከአንበሳው ጋር ፎቶ ሲነሣ የሚውለው? ጫካው የእርሱ ክልል ነው፤
የእርሱ ሠገነት ነው፡፡ እዚያ የቀለበቱ ጌታ (Lord of the Ring) እርሱ ነው፡፡ ከተማው ግን
የአንበሳ መደብ አይደለም፣ እርሱ ለከተማ አልተፈጠረም፣ ከተማውን አይችልበትም፤ በግቢ
ውስጥ መኖር፣ በአጥር መከለል፣ ከአንበሳው ተፈጥሮ ውጭ ነው፡፡ ስለዚህ ከሚያውቀው
ወደማያውቀው፣ ከሠገነቱ ወደ ባርነቱ፣ ከሚያሸንፍበት ወደሚሸነፍበት፣ ከሚችልበት
ወደማይችልበት፣ አወደርነውና፤ በከተማ፣ ግቢ ውስጥ አሥረን እንደልባቸውን
እንጫወትበታለን፡፡ አሁን የሚፈልገውን አድኖ ሳይሆን የምንሰጠውን ይበላል፣ በፈለገው
ሰዓት ሳይሆን በሰጠነው ሰዓት ይመገባል፣ ወደፈለገው ቦታ ሳይሆን ወደፈለግነው ቦታ
ይሄዳል፣ የፈለገውን ሳይሆን የፈቀድንለትን ብቻ ያያል፡፡ ለምን? ወደኛ ሜዳ አውርደንዋላ፣
ሜዳውን ትቶ መጥቷላ፤››
ዝም አሉና ቀና ብለው አዩት፡፡ ቦርሳውን ወደ ላይ ገፋ ገፋ እያደረገ ይመለከታቸዋል፡፡ እኛም
መጨረሻውን ለማወቅ ጓጉተን አፍጠን እናያቸዋለን፡፡ ስድብና ድብድብ ለማየት ተሰብስቦ
የነበረው ሰውም ነገሩ ዕውቀትና ቁም ነገር ሲሆንበት ጊዜ ቀስ በቀስ ‹‹ሼባው ነገሩን
ትምሮ አደረጉት›› እያለ ከአካባቢው ሸሸ፡፡ ‹‹የሚቧቀሱ መስሎኝ ነበር፤ ሼባው አበላሸው፡፡
ስድድቡ ተመችቶኝ ነበር ›› እያሉ በቁጭት ጥለዋቸው ሄዱ፡፡
‹‹አንተም እንደ አንበሳው ሆንክ›› አሉ ሽማግሌው፡፡ ወረድክ ከመደብህ፣ ከምትችለው
የዕውቀት ክርክር ሜዳ፣ ከምታሸንፍበት የሃሳብ ክርክር ሜዳ፣ ከለመድከው የጥናት ክርክር
ሜዳ፣ ወረድክላቸው፡፡ ጎበዞች ናቸው ደግሞ አድንቃቸው፡፡ አወረዱህና በሚችሉት ሜዳ
ላይ በደንብ አድርገው ቀጠቀጡህ፡፡ አንተም ሞኝ ነህ በማታውቀው ሜዳ ላይ ትግል
ገጠምክ፡፡
‹‹ሶምሶን ከፍልስጤማውያን ዐቅም በላይ ሲሆንባቸው፡፡ ፍልስጤማውያን ምን አደረጉ?
በደሊላ በኩል ሶምሶን ወደማይችለው እነርሱ ግን ወደሚችሉት ሜዳ አወረዱት፡፡
በሚችሉት ሜዳ አውርደው ደኅና አድርገው ቀጥቅጠው ያንን ኃያል ሰው ወፍጮ ፈጭ
አደረጉት፡፡
‹‹ብልጥ ከሆንክ አትውረድ፣ ጀግና ከሆንክ የወረዱትን አውጣቸው፡፡አሁን አሁን ብዙ ሰው
በዚህ እየተሸነፈብን ነው፡፡ እስኪ ጋዜጣውን፣ መጽሔቱን፣ ፌስ ቡኩን፣ ሰልፉን፣ የፖለቲካ
ክርክሩንም ተመልከተው፡፡ ብዙዎቹ ከሜዳቸው ወርደዋል፡፡ ብልጦቹ ከፍ ወዳለው ሃሳብ፣
ዕውቀት ወደሚጠይቀው ክርክር፣ በመረጃና በማስረጃ ወደሚደረገው ውይይት፣ ላቅ ወዳለ
ትግል፣ ወደ ልዕልናና ወደ ሠለጠነ አስተሳሰብ ማደግ እንደማይችሉ ያውቁታል፡፡
በዕውቀትና በሃሳብ ክርክር፣ በሠለጠነና ደርዝ ባለው ትግል፤ ማንበብን፣ ማወቅን፣
መመራመርን፣ በሚጠይቅ መሥመር መጓዝ፣ ተጉዘውም ማሸነፍ እንደማይችሉ ያውቁታል፡፡
ስለዚህ አንተን መሰል ሰዎችን ወደ ሜዳቸው ‹ውረድ እንውረድ› ብለው ያወርዷችኋል፡፡
በእነርሱ አጀንዳ፣ በእነርሱ ዐቅም፣ በእነርሱ ተራ ነገር፣ በእነርሱ አሉባልታ፣ በእነርሱ
ስድድብ፣ በእነርሱ ጠባብነትና ጎጠኝነት፣ በእነርሱ ወንዘኛነትና መንደርተኛነት፣ በእነርሱ
ተረብ ይገጥሟችኋል፡፡ ከዚያም ያሸንፏችኋል፡፡ አሁንማኮ ሁላችንንም አወረዱን፣ እንደነርሱ
እንድናስብ፣ እንደነርሱ እንድንጽፍ፣ እንደነርሱ እንድንደራጅ፣ እንደነርሱ እንድንናገር፣
እንደነርሱ እንድንዘፍን፣ እንደነርሱ እንድናምን፣ እንደነርሱ እንድንለብስ አደረጉንኮ፡፡
አትውረድ ልጄ፣ ዕውቀት ዋጋ ወደማታገኝበት፣ ሃሳብ ልዕልት ወደማትሆንበት፣ ችሎታ
ወደሚያስቀጣበት አለማወቅ ወደሚያስከብርበት፣ ማይም አለቃ ወደሆነበት፣ ክርክር ተረብ
ወደሆነበት፣ ውይይት እንደ ኮካ ኮላ ጠርሙስ አንድ ዓይነት ወደሆነበት፣ አላዋቂዎች
ወደሠለጠኑበት፣ ከብት ካለው ይልቅ አፍ ያለው ወደተሾመበት ሜዳ አትውረድ፡፡ ከወረድክ
ግን በማታውቀው ሜዳ፣ በማታውቀው ስልት፣ በወረደ ትግል ይደበድቡሃል፡፡ አትውረድ
ልጄ፡፡ አትውረድ፡፡

20/10/2017

ሀገራዊ ዕብደት
( ዲያቆን ዳንኤል ክብረት)
ሁሉ በሽተኛ ሁሉ ራሴን ባይ
በቤታችን ደኅና መጥፋቱ ነወይ
የሚል የበገና ዘለሰኛ አለ፡፡ አሁን ያለችውን ሀገራችንን ቀድሞ ያየ ደራሲ መሆን አለበት የገጠመው፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ጤነኛ አካል የጠፋ ይመስላል፡፡ የገዛ ወገኑን አባርሮ የሚፎክር ወገን፣ ሕዝብ እንዳይሰደድ የሚያደርግ አሠራርና አስተዳደር መዘርጋት ሲገባው ሲያባብስ ኖሮ ሕዝብ ሲሰደድ መጠለያ ድረስ ሄዶ የሚጎበኝ ባለ ሥልጣን፣ የሀገሩን ሀብትና ንብረት አቃጥሎ በኩራት የሚደነፋ ጎረምሳ፤ ሕዝብን እያዋረደና እየተሳደበ መግለጫ የሚሰጥ የክልል ሹም፤ ነገሩ ሁሉ እንዳይሆን እንዳይሆን ሲበላሽ እያየ መንገዱን ለመመርመር የማይፈልግ መንግሥት፤ ሀገር እየጠፋ ግደል ተጋደል የሚል ተቃዋሚ፣ ለሌላው ይተርፋል ሲሉት የራሱ የሚያርበት የእምነት ተቋም፤ ጢሱ እንዳይነካው ተደብቆ ገሞራ ሊያስነሣ የሚባዝን የማኅበራዊ ሚዲያ ተዋናይ፤ የሀገሪቱን መጻኢ ዕድል ሳይሆን የምእመኖቻቸውን የጫማ ቁጥር የሚተነብዩ ‹ነቢያት›፣ ምኑ ቅጡ - ሁሉ በሽተኛ ሆኗል፡፡ በቤቱም ደኅና ጠፍቷል፡፡
ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት እየወደቅንም እየተነሣንም፣ እየተቃቀፍንም እየተቧቀስንም፣ ሆ ብለን እየወጣንም አድፍጠን እየተቀመጥንም፤ እየተከፋፈልንም አንድ ለመሆን እየሞከርንም፤ እያሠርንም እየታሠርንም ለመጓዝ ሞክረናል፡፡ ማንም የአንድ ዓመት የልጅነት ልብሱን በሃያ ስድስት ዓመቱ አይለብስም፡፡ ኢትዮጵያም እንዲያ ሆናለች፡፡ የዛሬ ሃያ ስድስት ዓመት የተሰፋው ልብሷ ጠቦ፣ ጠቦ፣ ጠቦ - እየተቀዳደደ ነው፡፡ ሊጣፍ፣ ሊሰፋ አይችልም፡፡ አሁን ሌላ ልብስ ያስፈልጋታል፡፡ ‹ሞኝ ማለት በተመሳሳይ መንገድ እየሄደ የተለየ ውጤት የሚጠብቅ ነው› ይባላል፡፡ የሀገሪቱን ችግሮች ለመፍታት በአንድ ዓይነት መንገድ ብቻ ማላዘናችን አላዋጣንም፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ መንገድ ልንሞክር ግድ ነው፡፡
ሰውዬው ሴትዮዋን ወዳጁ ለማድረግ በሠፈሯ በኩል በሚያልፈው መንገድ ያለማቋረጥ ሲመላለስ አየችውና
አምናና ታች አምና ሳይሆን እያየህ
ዛሬም በዚያው መንገድ ትታክታለህ› አለቺው አሉ፡፡
ይህ ችግር የሁለት ወገኖች ችግር ነው፡፡ የመንግሥትም የተቃዋሚውም፡፡ ሁላችን ላለፉት ዓመታት የሀገሪቱን ችግር ለመፍታት የተጓዝንበት መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡ ተመሳሳይ መንግሥታዊ መንገድ፤ ተመሳሳይ የተቃውሞ መንገድ፡፡ የሀገሪቱ ሁኔታ ግን እየባሰና እየተወሳሰብ ነው፡፡ የትውልድም ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ በ1983 ዓም የተወለደ ልጅ ዛሬ 26 ዓመቱ ነው፡፡ እኛ ግን በ1966 ባሰብነው መንገድ አሁንም እየተጓዝን ነው፡፡
ችግሩ ሲወሳሰብ ሀገራዊ ዕብደት ተፈጥሯል፡፡ ሰከን ብሎ፤ ለሀገርና ለወገን አስቦ፣ ሁሉም የሚያሸንፍበትን፤ ይበልጥ ደግሞ ሀገር የምታሸንፍበትን መንገድ ከመተለም ይልቅ ሁሉም ባገኘው መሣሪያ ይጫረስ ይዟል፡፡ ሀገራዊ ዕብደት ማለት ከምንደርስበት ግብ ይልቅ ለምንሄደው መንገድ መጨነቅ ነው፡፡ ሀገራዊ ዕብደት ማለት አንድን ስሕተት በስሕተትነቱ ከመኮነን ይልቅ የማን ወገን ይህን አደረገው ለሚለው ቅድሚያ መስጠት ነው፡፡ ሀገራዊ ዕብደት ማለት በሌላኛው ጥግ ያለው የመርከቧ ክፍል ሲቃጠል እኔ እተርፋሁ ብሎ በአንዱ ጥግ ቆሞ መሳቅ ነው፡፡ ሀገራዊ ዕብደት ማለት ዛፉ ከሥር እየተገዘገዘ ቅርንጫፉ ላይ ሆኜ እተርፋለሁ ብሎ ማለም ነው፡፡ ሀገራዊ ዕብደት ማለት ከአእምሮ ይልቅ ለስሜት ቅርብ መሆን ማለት ነው፡፡ ሀገራዊ ዕብደት ማለት ሁሉ የሚጫረስበት፤ ተው የሚል የሚጠፋበት፤ ተው ማለት የሚገባቸውም አብረው የሚያብዱበት ማለት ነው፡፡
ታዋቂው የጎንደር ዘመን ሊቅ፣ የሰባት መጻሕፍት ደራሲ፣ የዐፄ በካፋን ዜና መዋዕል የጻፈው አዛዥ ሲኖዳ ‹ፍጻሜ መንግሥት› የሚል መጻሐፍ አለው፡፡ በዚያ መጽሐፉ ላይ ‹ እነዚያ ሰዎች የገዛ ቤታቸውን አቃጥለው (እሉ ሰብእ ይኮሰትሩ ቤቶሙ ወይትዋነዩ በነዲዱ፣ ወዝንቱ ዘመን ይሰመይ ዘመነ አብዳን) በእሳቱ የሚጫወቱበት ዘመን ይመጣል፡፡ ያም ዘመን ዘመነ አብዳን ተብሎ ይጠራል› ይላል፡፡ ያ ዘመን አሁን ይመስላል፡፡ የሀገራችን ሰዎች በነውሩ ይዝናናሉ፣ በግፉ ይኩራራሉ፣ በጥፋቱ ይመካሉ፣ በችግሩ ያቅራራሉ፣ በመከራው ይስቃሉ፡፡ የገዛ ሀገራቸው እያቀጠሉ እሳት ይሞቃሉ፡፡ የተረፈውም የዕብድ ገላጋይ ሆኖ ጎራዴ ያቀብላል፡፡
ሀገር ከዘመነ ዕብደት እንድትወጣ ሰከን ብለው ከስሜታቸው፣ ከጥቅማቸው፣ ከክብራቸው፣ ከጎሳቸውና ከሥልጣናቸው በላይ የሚያስቡ ዜጎች ያስፈልጓታል፡፡ እንግሊዝ የኦጋዴንን መሬት ለኢትዮጵያ እኤአ በ1954 ከመመለሷ በፊት ካሊ በተባለ ቦታ ላይ የኢትዮጵያ ሶማሌ የጎሳ መሪዎችን ሰብስበዋቸው ነበር፡፡ በዚያ ሸለቆ ውስጥ የተሰባሰቡ የጎሳ መሪዎች ሦስት አማራጭ እንደቀረበላቸው በወቅቱ ልጆች ሆነው ነገሩን የተከታተሉና ከሽማግሌዎቹ የሰሙ የሀገር ሽማግሌዎች በቦታው ላይ ሲናገሩ ሰምቻቸዋለሁ፡፡ ከታላቋ ሶማሊያ ጋር ትዋሐዳላችሁ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ትዋሐዳላችሁ ወይስ ራሳችሁን ትችላላችሁ፡፡ እንዲያውም የእንግሊዙ መኮንን አንድ ከሸማ የተሠራ ልብስ አምጥቶ በቁጥቋጦው ላይ ጣለውና መልሶ አነሣው፡፡ ልብሱ በቁጥቋጦው እሾህ ተቀዳዶ ነበር፡፡ ‹ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታዋ እንዲህ ነው› አላቸው፡፡ እነዚያ የጎሳ መሪዎች ግን ኢትዮጵያ ድኻ፣መንግሥቷም የማይስማማን መሆኑን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ከእርሷ ተገንጥለን አንወጣም› ማለታቸውን ሽማግሌዎቹ ተናግረዋል፡፡
አሁን ያ ዘመን አልፎ የዕብደቱ ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ የሀገሬ መሬት ማለቱ ቀርቶ የጎሳዬ መሬት እንላለን፤ የክልል ድንበሮች አጥሮች ሆነዋል፡፡ ከክልል ክልል ከመሄድ ከኢትዮጵያ ኬንያ መሄድ ቀላል ሆኗል፡፡ ቋንቋ መግባቢያ መሆኑ ቀርቶ መለያያ ሆኗል፤ የጨቋኝ ተጨቋኝ ታሪክን ተርከን ተርከን ሁሉ ዐርበኛ ሆኗል፡፤ 3000 ዓመት የነጻነት ታሪክ አለን እያልን 3000 የነጻ አውጭ ድርጅቶችን መሥርተናል፡፡
ከጎርፉ ጋር በፍጥነት አብሮ የሚወርድ ዋናተኛ ለራሱም አይበጅ ሌላውንም አያድን፡፡ ወንዙን አቋርጦ ራሱንም ሌላውንም ለመታደግ ሦስት አማራጭ ነው ያለው፡፡ የዋናተኛው ዐቅም ከወንዙ ዐቅም በላይ ከሆነ ያቋርጠዋል፡፡ የወንዙ ዐቅም ከዋናተኛው ዐቅም እኩል ከሆነ እንዳይነቃነቅ አድርጎ ይቸክለዋል፡፡ የወንዙ ዐቅም ከዋናተኛው ዐቅም በላይ ከሆነ ይዞት ይሄዳል፡፡ አሁን ሀገሬ ያለችው ሁለተኛው ላይ ነው፡፡ የወንዙ ዐቅምና የኛ ወንዙን የማቋረጥ ዐቅም እኩል ሆኗል፡፡ ስለዚህም ወይ ችግሩ አይፈታም፤ ወይ እኛ አንፈታም - ተቸክለናል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን የወንዙ ኃይል እየጨመረ፣ የኛም ዐቅም እየቀነሰ መጥቶ ይዞን መሄዱ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ሀገራዊ ዕብደት ላይ ስላለን፤ መሐል ወንዙ ላይ እንዳንነቃነቅ ሆነን ቆመን ወንዙን እያቋረጥኩት ነው ብለን እናስባለን፣ እንደሰኩራለንም፡፡
መሐል ወንዝ ላይ ማቋረጥ አቅቶት የቆመ ሰው አማራጩ ሦስት ነው፡፡ ወይ ዋናውን ትቶ በሌላ መንገድ (ቢችል በእግሩ መሬት ረግጦ ለመውጣት) ይሞክራል፤ ወይ ኡኡ ብሎ የሌሎችን ርዳታ ይጠይቃል፤ አለያ ደግሞ ወደ ፈጣሪው ይማጸናል፡፡ አሁን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃንም ያሏቸው አማራጮች እነዚህ ናቸው፡፡ ያለበለዚያ ግን ሀገራዊ ዕብደቱ እየጨመረ ሄዶ ወንዙ ሁላችንንም ጠራርጎ ይወስደናል፡፡ የማንፈልግበት ቦታም ያደርሰናል፡፡

06/10/2017

አስተምር ብሎ ሄዶ ተምሮ የሚመጣበት ሀገር
(ዳንኤል ክብረት)

‹የበረታ ጀሃነምም ወስጥ ሶላት ያደርጋል› የሚል የዐረቦች አባባል አለ፡፡ ሰው ከጠነከረ አይደረግም የተባለውን በማይቻልበት ቦታ እንደሚያደርገው ለመግለጥ፡፡ ሰሞኑን እኔም ያየሁት ይሄንን ነው፡፡ ሚዞሪ ሴይንት ሉዊስ፡፡
ወደ ሚዞሪ ሴይንት ሉዊስ ስሄድ የመጀመሪያዬ ነበር፡፡ ገና ከአዲስ አበባ ስነሣ ያገኘኋቸው የአሜሪካ ሰዎች ‹አይ፣ እዚያኮ ብዙ ሰው አለ ብለህ ነው› የሚል ቅሬታ ያሰሙ ነበር፡፡ ያው በተለመደው መሥፈርት ጉባኤን በሰው ብዛት ስለምንለካው፡፡ ለሳምራዊቷ ሴት ብቻ ሲባል፣ በሲካር ምንጭ አጠገብ የተደረገውን ጉባኤ ስለምንረሳው፡፡ ‹ሞቀ፣ ደመቀ፣ ተቀወጠ፣ › የሚሉ ከመንፈሳዊነት የተለዩ የጉባኤ መለኪያዎች ስላመጣን፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ አምስት ሺ ሆኖ በጉባኤ ተሰብስቦ፣ ያውም ዓሣና እንጀራ ከጌታ እጅ በልቶ ከደመቀው ጉባኤ ይልቅ፣ ለብቻው በሌሊት መጥቶ የተማረው ኒቆዲሞስ ጉባኤ ይበልጣል፡፡ በቁጥር የጥብርያዶሱ፣ በፍሬ የኒቆዲሞሱ ጉባኤ ይበልጣል፡፡ የጥብርያዶሱ ጉባኤተኛ በዕለተ ዓርብ ‹ስቀለው፣ አስወግደው› ሲል፤ ብቻውን የተማረው ኒቆዲሞስ ግን በጥብዐት በዕለተ ዓርብ ተገኝቶ የጌታችንን ሥጋ ለመሸከምና ለመቅበር በቅቷል፡፡
ይህንን እያሰብኩ ነበር ከ24 ሰዓት ጉዞና ሽግግር በኋላ ሴይንት ሉዊስ የገባሁት፡፡ ጉባኤው የተጀመረው በዕለቱ ነው፡፡ እናቶቻችን የሚጣፍጥን ወጥ በሰታቴ አይሠሩትም፤ በድስት እንጂ፡፡ ወርቅና ብርም በትልቅ አገልግል አይቀመጥም፣ በሙዳይ እንጂ፡፡ የሴይንት ሉዊስ ክርስቲያኖችም እንደዚያው ናቸው፡፡ ‹ነጋ ለኪዳን፣ መሸ ለቁርባን› የሚባሉ ዓይነቶች፡፡ ጉባኤው ለአምስት ቀናት ያህል ጠዋትና ማታ የተደረገ ነው፡፡ ከጠዋቱ 3(9) ሰዓት እስከ 6(12)፣ ከሰዓት ደግሞ ከ11(5) ሰዓት እስከ 3(9) ሰዓት በየቀኑ፡፡ ሥራ፣ ልጆች፣ ኑሮ በሚያናውዘው ማኅበረሰብ ውስጥ ነው የሚኖሩት፣ ደልቷቸው፣ ተመችቷቸው አይደለም፡፡ መንነው፣ ዓለምን ንቀውም አይደለም፡፡ ቆርጠው፣ ወስነው እንጂ፡፡

በአሜሪካ ታሪክ ሕዝብ ጠዋትና ማታ፣ ሳይሰለችና ሳያመካኝ ሲማር ያየሁበት ቦታ፡፡ እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶች፣ በሞያቸው አንቱ የተባሉ፣ በሥራቸው ፋታ የሌላቸው፣ የቻሉ ፈቃድ ወስደው፣ ያልቻሉ የሥራ ሰዓታቸውን ቀይረው፣ ከዚያም የባሰባቸው ሲቀሩ በስልክ እየተከታተሉ፣ በብርታት የሚማሩበት ቦታ፡፡ በዚህ መልኩ የማስታውሳቸው የኬንያ፣ የኡጋንዳና የማልታ ጉባኤያትን ነው፡፡ በሀገር ቤት ደግሞ በምዕራብ ወለጋ የሚገኙትን የቂልጡ ካራ ምዕመናንን፡፡ እነዚህ ቀንም ማታም፣ ሌሊትም የሚማሩ ናቸው፡፡ ግን ቢያንስ የተሻለ ጊዜ አላቸው፡፡ የሴይንት ሉዊስ ክርስቲያኖች ግን ከጊዜና ከሥራ መርሐ ግብራቸው ጋር እየታገሉ ይመጣሉ፡፡ ሌሊት ሥራ አድረው ከዕንቅልፍ ጋር እየታገሉ ሲማሩ አያቸዋለሁ፡፡ ለመምጣት እንጂ ለመቅረት ምክንያት አይሰጡም፡፡ በተለይ በዓርብና በቅዳሜ ጉባኤያት ላይ ለመካፈል በታክሲ ሥራ ላይ የተሠማሩት ምእመናን የከፈሉትን ዋጋ ሳይ ‹ኢይኃድጋ ለሀገር ዘእንበለ አሐዱ ኄር› የተባለውን ያስታውሳሉ፡፡ ጎንደር እንደ ኒውዮርክ በደመቀችበት የመዲናነት ዘመንዋ ‹ለእመ አእመረ ባቲ፣ ጎንደርሰ ዋልድባ ይእቲ› ይባል ነበር፡፡ ‹ላወቀባት ጎንደርም ዋልድባ ናት› ማለት ነው፡፡ ላወቀባት አሜሪካም እንዲሁ ናት፡፡
ጥቂት ግን ብርቱ፣ ትንሽ ግን ጽኑ፣ የማይሞቅ ግን የሚያጸድቅ ጉባኤ የምትፈልጉ- ሴይንት ሉዊስ ቅድስት ማርያምና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሂዱ፡፡ አስተምር ብሎ ሄዶ ተምሮ የሚመጣበት ሀገር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ዘመን በአካል ቢኖር ኖሮ - ‹ወደ ሴይንት ሉዊስ ሰዎች› የሚል አንድ መልእክት ይጽፍላቸው ነበር፡፡

27/08/2017

የዳንኤል. ክብረት. እይታዎች
‹ድኻ ወርቅ አይግዛ›
‹ድኻ ወርቅ አይግዛ ከገዛም ይጥፋበት› ይላሉ የምንዳዬ እናት አባዬ፡፡ ‹ምነው አባዬ ድኻ በመከራ የገዛውን ወርቅ እንዴት ይጥፋበት ይላሉ› ብለን ሞገትናቸው፡፡ ‹እይውልህ እኛ ሠፈር አራት ኪሎ አዲሴ የሚሏት አንዲት ጎረቤታችን ነበረች፡፡ ቁርስ፣ ምሳና እራት የተዘበራረቁባት፡፡ ለነገሩ ላለው ነው እንጂ ለሌለው ሰው ምግብ ስሙ ያው ምግብ ብቻ ነው፡፡ ምግብ - ቁርስ፣ ምሳ እራት የሚሆነው በሰዓቱ ስታገኘው ነው፡፡ በሰዓቱ ካላገኘኸው ያው ምግብ ብቻ ነው፡፡ ከድንጋይ ትፈልቅቀው፣ ከሳጥን ትስረቀው ሳናውቅ አንድ ቀን በድንገት አራት ኪሎ ወርቅ ቤት ሄዳ ወርቅ ገዛች ተብሎ ተወራ፡፡ የቡና ሴቶች ‹ግማሽ ግራም ወርቅ ገዝታ በከረጢት ቋጥራ አስቀመጠችው› ብለው ያሽሟጥጧታል፡፡
የገዛች ለት ምሽት እኛ ቤት ቡና ተጠርታ መጣችልህ፡፡ ሴቱ ሁሉ ግጥም ብሏል፡፡ ተርብ ተርቦቹ ደግሞ የዛን ቀን አንድም ሳይቀሩ ተለቃቅመው መጥተውልሃል፡፡ ገና ወደቤት ስትገባ ከሁላችን ለይታ ‹ወይዘሮ የወርቅ ውኃ ደኅና አመሹ› አትልልህም፡፡ አሁን በእርሷ ቤት ወርቅ መግዛቷን ልትነግረን እኮ ነው፡፡ ተያየንና ‹ኡኡቴ› ብልን ዝም አልን፡፡ ገና ከጠፍር ወንበሩ ላይ ሳትደላደል ‹እኔኮ በዚህ ዘመን ድኻ እንዴት ይኖራል፤ እኛስ እሺ› ብላ አረፈችው፡፡ ‹እናንተ እነማን ናችሁ› አለቻት እቴኑ በዓይኗ ቂጥ እያየቻት፡፡ ከምንም ሳትቆጥራት ‹ኧረ እንዴው ተውኝማ፣ ወርቅ እንደዚህ ሰማይ ይንካ› አለች ቆሎውን እየዘገነች፡፡ ‹እኛ ወርቅ ዘመን እንጂ ወርቅ ምን ያደርግልናል› አሏት እማማ ትጓደድ፡፡ ላምሮት ተናደደችና ‹ምን ዳር ዳር ትያለሽ፣ ወርቅ ገዝተሻል› አለችና አፈረጠችው፡፡ ሴቱ ሁሉ አንድ ጊዜ ቤቱን በሁካታ ሞላው፡፡ መቼም እርሷ አፍርጠው ናት፡፡
ሳቃችንን ሳንጨርስ ‹ቆይ ቆይ እስኪ› አለች አዲሴ ጆሮዋን እንደ አንቴና ሰቅላ፡፡ መቼም ከአራት ኪሎ ሠፈር ጯሂና አስጯሂ አይጠፋም ብለን ጸጥ አልን፡፡ አራት ኪሎ ጠብና ዕርቅ የተለመደ ነው፡፡ ተደባዳቢና ገላጋይ በየተራ ነው፡፡ ዛሬ ትደባደባለህ፣ ነገ ደግሞ በተራህ ገላጋይ ትሆናለህ፡፡ ሁላችን ኮንዶሚኒየም ላይ እንደተሰቀለ ዲሽ ጆሮአችንን አከታትለን ብንሰቅልም የመንገደኛ ተረብ ብቻ ነው የምንሰማው፡፡ አዲሴ ተነሣችና ሳንዱቁ ላይ በልብስ ተሸፍኖ የተቀመጠውን ራዲዮ እስከ አንጀቱ ድምጹን ለቀቀችው፡፡ አበደች እንዴ ብለን በግራ ዓይናችን ገላመጥናት፡፡
‹ዛሬ በዋለው የዓለም ገበያ› ይላል ራዲዮኑ፡፡ እርሷ እዚያው እንደተለጠፈች ናት፡፡ እዚህ አራት ኪሎ ያለው የጉልት ገበያ የሚናፍቃት ሴትዮ የዓለም ገበያ ምን ሊያደርግላት ነው ብለን ሳቅን፡፡ ለወትሮው በዱቤ የሰጧት እንዳያንቋት ገበያ ድርሽ አትልም ነበር፡፡ እንዲያውም እማማ ትጓደድ ‹አዲሴኮ ገበያ ብቻ ሳይሆን ገበያው የሚባል ሰውም ትፈራለች› እያሉ ይተርቧት ነበር፡፡ ራዲዮው ‹ዛሬ በዓለም ገበያ ወርቅ በካራት ይህን ያህል ተሽጧል› ሲል ‹እንዴው በደኅና ጊዜ ባልገዛ ይቆጨኝ ነበር፡፡ ለካስ ሰው ልጁን ወርቁ፣ ወርቂቱ፣ ወርቄ፣ ወርቅ አገኘሁ፣ ወርቅ አለማሁ፣ ጥሩ ወርቅ፣ አመለ ወርቅ እያለ የሚጠራው ወርቅ እየተወደደበት ነው› አለችና የግራ እጅ መዳፏን በቀኝ አራት ጣቶቿ ደበደበችው፡፡
ከዚያ በኋላ አዲሴን ማን ይቻላት፡፡ ከሱቅ በዱቤ ዕቃ ስትወስድ እንደ ድሮው መለመን፣ መለማመጥ ቀረ፡፡ ‹ማነህ ባለ ሱቅ፣ እስኪ አንድ አምስት ኪሎ ስኳር አምጣ› ትለዋለች፡፡ ‹እንዴ እማማ አዲሴ፣ በኋላ ባይከፍሉኝስ፤ ያለፈውን በመከራ አይደል እንዴ የከፈሉኝ› ሲሏት ‹ያለፈው አለፈ፣ በቃ እናንተ ሰው ይቀየራል ብላችሁ አታስቡም፤ አምጣ ባክህ፣ ቢበዛ ወርቄን ሽጬ እከፍልሃለሁ› ትላቸዋለች፡፡ ኧረ እንዲያውም አንድ ቀን አንድ ቄስ በዚያ ሲያልፉ ጠራቻቸውና ‹ዛሬ ሲያቃዠኝ አድሯል ይርጩኝ› ትላቸዋለች፡፡ ‹የክርስትና ስምሽ ማነው› ይሏታል ‹እኅተ ወርቅ› ትላቸዋለች፡፡ ቄሱ ደንግጠው ‹እኅተ ማርያም› ማለትዎ ነው› ይሏታል፡፡ ቀኝ እጇን ወደ ጎን እያውለበለበች ‹እርሱ የነዛ የነዛ ስም ነው› አለቻቸው፡፡ ‹ታድያ እኅተ ወርቅ፣ አይ፣ ያልተማረ ሰው ሰጥቶዎት እንዳይሆን› ይላሉ ያልገባቸው ቄስ፡፡ ‹ይኼው ነው አባቴ፣ካልተረዱት ይተውት› አለቻቸው፡፡
ድሮ አዲሴ ቀበሌ መሄድ አትወድም ነበር፡፡ ‹እነርሱ መዋጮ ብቻ ነው ሥራቸው› ትላለች፡፡ ወርቅ በገዛች ሰሞን ‹ምነው ስብሰባ በተጠራ፣ ልክ ልካቸውን ነበር የምነግራቸው› ማለት አበዛች፡፡ በልኳ ለብሳ የማታውቅ ሴትዮ ድንገት ተነሥታ ልክ ልክ ነጋሪ ሆችልህ፡፡ የስብሰባው አጀንዳ ‹ሴቶች በልማት ይሳተፉ› የሚል ነው፡፡ አዲሴ ተነሣችና ‹ለሴቶች ዕድገት ወሳኙ ወርቅ ነው፡፡ እኛ ሴቶች ከወንዶች እኩል እንድንሆን ወርቅ ያስፈልገናል› ስትል አንዷ ‹ታዲያ እንደ መሠረት ደፋር አትሮጭም፣ ማን ከለከለሽ› ብላ አሳቀችባት፡፡ ‹የሴቶችን ችግር ለመፍታት ስብሰባ ሳይሆን ሴቶች ወርቅ የሚገዙበት መንገድ መመቻቸት አለበት› ብላ ስትቀመጥ ሰብሳቢዋ ምናልባት መልስ ቢሰጡ ብላ ነው መሰለኝ ለወይዘሮ ወርቅ ያንጥፉ ዕድል ሰጠቻቸው፡፡ ሊያነጥፉላት ነው፡፡
‹ድኻ ወርቅ አይግዛ፣ ከገዛም ይጥፋበት› ትል ነበር አያቴ፡፡ ወ/ሮ አዲሴ ትናንት ግማሽ ግራም ወርቅ ስለገዛሽ ወሬሽ ሁሉ ምነው ወርቅ ብቻ ሆነሳ› ሲሉ ሁሉም የኮረኮሩት ያህል በሳቅ ፈነዳ፡፡ ‹ባለፈው እዚህ ሠፈራችን ያለ ጎረምሳ መጽሐፍ አሳተመ ተብሎ ደስ አለን፡፡ ምንም ቢሆን ያሳደግነው ልጅ ነው ብለን፡፡ እሱ ግን ፊደል የፈጠረ እንጂ መጽሐፍ ያሳተመ አልመሰለውም፡፡ ቡና ልንጠጣ ቤታቸው ስንሄድ የዛሬው የቡና ቁርስ የኔ ግጥም ነው ብሎ ግጥም ሊያነብልን ጀመረ፡፡ ምነው ሸዋ! ሐዲስ ዓለማየሁም እንዲህ አላደረጉ፡፡ ደግሞኮ
አራት ኪሎ ኪሎ
አራት ኪሎ ኪሎ
የድንጋይ አሎሎ› የሚል ግጥምኮ ነው፡፡› ሰብሳቢዋማ ከጠረጴዛው መነሣት እስኪቸግራት ተደፍታ ነው የሳቀችው፡፡ ያው ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ ከሳቅክላቸው ማንጠፍ ነው፡፡ ‹ይባስ ብሎ ቀበሌ አዳራሽ ልጆቹን ሰብስቦ ‹ታዋቂው ደራሲ› የሚል ፖስተር ለጥፎ ልምድ አካፍላለሁ ይላቸዋል፡፡ ‹እርሟን ጠምቃ፣ ሰጠች ጠልቃ› አሉ፡፡
አንበሳ ተኝቶ ፍየል ዘለለችው
ንቆ ቢያሳልፋት ሞኝ አደረገችው› አለ የሀገሬ ሰው፡፡ በብጥሌ ወረቀት አላሳተምንም እንጂ ስንት ግጥም ነበረንኮ፡፡
መቶ ታምሳ ዜማ የሚሰማብሽ
ድኻ ባለጠጋ የማይጠፋብሽ
ፀሐይ እንደ እንግሊዝ የማይጠልቅብሽ
የሁሉ እኩል ሀገር አራት ኪሎ ነሽ› ብሎ እንደመግጠም ‹አራት ኪሎ ኪሎ፣ የድንጋይ አሎሎ› ብሎ አሎሎ የሚያህል ግጥም የጻፈን ልጅ ልምድ አካፍላቸው ማለት በአሎሎ ደብድባቸው እንደ ማለት ነው፡፡› ሳቅና ጭብጨባ አጀባቸው፡፡ ድኻ ወርቅ አያግኝ ማለት ይኼ ነው፡፡ አሁን እኛን የቸገረን እንዲህ እንደ አዲሴ የሚባርቅባቸው ድኾች ናቸው፡፡ ሥልጣን አይቶ ለማያውቀው ሥልጣን ትሰጡትና ይባርቅበታል፡፡ የቢሮውን መኪና በሠፈራችን እያፈጠነ ካላሳየን ሞቶ ይገኛል፡፡ በታክሲ ሲሰቃይ ለከረመ ሰው ቪ ኤይት መኪና መስጠት በውኃ ጥም ለከረመ ሰው ቅቤ አቅልጦ እንደማጠጣት ነው፡፡ ሁለቱም ጤና አይሆናቸውም፡፡ አበሉ፣ ስብሰባው፣ ግብዣው፣ ፊርማው፣ ብርቅ ይሆንበታል፡፡ ቀበሌውና ክፍለ ከተማው የግል ንብረቱ ይመስለዋል፡፡ እኛም አሽከሮቹ እንመስለዋለን፡፡ የተሾመ ሰሞን ብርቅ ስለሚሆንበት ያገኘውን ገንዘብና መሬት ይጠበጥበዋል፡፡ ያልራሰ መሬት ማለትኮ ነው፡፡ ምን ውኃ ይመጥነዋል፡፡ ‹አይቶ አያውቅ ዳቦ ፍሪዳው ነው› ይባላል፡፡ አንድ ስብሰባ ላይ አንዲት እንግሊዝኛ የሰማ ዕለት እኛን ሰብስቦ እርሷን ካልተናገረ ይሞታል፡፡ ውጭ ሀገር ሄዶ አንዲት ነገር ካየ፣ ብርቅ ስለምትሆንበት ‹ቻይና ሳለሁ፣ ኮርያ ሳለሁ› እያለ መከራ ያሳየናል፡፡ ድኻ ወርቅ አይግዛ የተባለውኮ ለዚህ ነው፡፡
አላያችሁም እንዴ በድንገት ሀብታም የሆነን ሰው፡፡ ሳይነግራችሁ ታውቁታላችሁኮ፡፡ የውሻ ማሠሪያ የሚያህል የአንገት ወርቅ፣ ክብደት መለኪያ የሚሆን የእጅ ሰዓት፣ የሚታይ ከናቴራ፣ ከከናቴራው ላይ አዲስ ሸሚዝ፣ በሸሚዙ ላይ አዲስ ሹራብ፣ በሹራቡ ላይ አዲስ ኮት፣ በኮቱ ላይ አዲስ የውጭ ካፖርት፣ በካፖርቱ ላይ ስካርፕ ደርቦ ታዩታላችሁ፡፡ ይህን ስታዩ ‹ድኻ ወርቅ አይግዛ› በሉና ሽሹ፡፡ መኪና ከገዛማ አይጣልባችሁ፡፡ በግራ እጁ መሪ ይዞ፣ ወንበሩን ወደ ኋላ ስቦ፣ ልጥጥ እያለ፣ የአስፓልት ውኃ እየረጨባችሁ ያልፋል፡፡
እና አዲሴ ተይን እባክሽ፣ አንቺ ዛሬ ወርቅ ስትገዥ የችግራችን ሁሉ መፍቻ ወርቅ መሰለሽ፡፡ የክፉ ሐኪም ምክር አትምከሪን፡፡ ክፉ ሐኪም ሥጋው የገጠጠ በሽተኛ በቀበሌ ደብዳቤ በነጻ እየታከመ እያየ ከምግብ በፊትና ከምግብ በኋላ ሦስት ጊዜ የሚዋጥ መድኃኒት ያዛል፡፡ ይህ ማለትኮ ሰውዬውን አትድንም ተስፋ ቁረጥ ማለቱ ነው፡፡ መድኃኒቱንስ በነጻ አገኘ፡፡ ምግቡን ማን ይሰጠዋል? አሁን ያስቸገሩን እንዳንቺ ያሉት ናቸው፡፡ ሲበሉ የበላን፣ ቤት ሲሠሩ የሠራን፣ አበል ሲከፈላቸው የተከፈለን፣ ሲሾሙ የተሾምን፣ የእነርሱ ችግር ሲፈታ የእኛ የተፈታ የሚመስላቸው የአእምሮ ድኾች፡፡ ድኃ ወርቅ አይግዛ ከገዛም ይጥፋበት የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ ወርቁ ጠፍቶባቸው ከሥልጣን ሲወርዱ፣ ከሀብት ሲናዱ ምን እንደሚመስሉ አይተናቸዋላ፡፡
ሞቅ አድርገን አጨበጨብንላቸው፡፡ ራሷ ሰብሳቢያችን አጨበጨበች፡፡ እኔም ከእርሷ ወስጄ ‹ድኻ ወርቅ አይግዛ ከገዛም ይጥፋበት› እላለሁ፡፡
አሉኝ የምንዳየ እናት አባዬ፡፡

16/08/2017

፠፠፠ ምኒልክ ፠፠፠
ድምፃዊት።። ራሔል ዮሐንስ
ገጣሚ።።።ይልማ ገብረ አብ
፨፨፨★★★
ብወጣው በግሬ እንጦጦን ፣
አላገኝም ወይ ጣይቱን፣፣
ፍቅሩን አብዝቶት ያለ ልክ፣
ዛሬም ይባላል ምኒልክ፣፣
አሆይ ይወራል ዘንድሮ፣
እኛ በላን ድሮ፣፣ (የተበላው ድሮ)
እስቲ ወደ አንኮበር ተነሱ እንዝለቀው፣
እኛ አናየውም ወይ ምኒልክ ቢለቀው፣፣
የጣይቱን ማጀት ቢፈልጉት እዛ፣
አይጠፋም እስካሁን የጠጇ መዓዛ፣፣
ከልፍኝ ካዳርሹ ባካል ባናገኛት፣
በግብሯ ትዝታ ዛሬም ከግቢ ናት፣፣
ሙያዋ ቢጣፍጥ የዛች እመቤት ፣
ተበላ ተጠጣ በምኒሊከ ቤት፣፣
እስቲ አንተ ሸውዬ እንዳባትህ ስራ፣
ከጓዳ እንድንቀዳው ወተቱን በእንስራ፣፣
ደግነትክን ሳላይ በዋልክበት ውዬ፣
ደርሶ እንደ ምኒሊክ አልልክ እምዬ፣፣
ያገኘክ እንደሆን ግቢ ካዲሳባ፣
የደግ አዳራሽ ነው ሰተት ብለህ ግባ፣፣
አይቆረቁረውም እንግዳ ደጁን፣
ገብቶ ይጥገብ እንጂ ሥጋና ጠጁን፣፣
ያ ሁሉ ደስታ ፊቴ ይደቀናል፣
ሰው እንዴት በሄደው ባለፈው ይቀናል፣፣
ያ የፍቅር ጊዜ ያ የደስታ ቀን፣
ደግሞ ባይኔ መጣ እፊቴ ሊደቀን።
ነሐሴ 12 የእቴጌ ጣይቱና የአጤ ምኒልክ የልደት ቀን ነው።

07/08/2017

መጀመሪያዎቹ.. . በማስተርስ ስራ ያጣን፣ በድግሪ
ኮብልስቶን የፈለጥን፣ መቶ ብር የአንድን ብር ዋጋ ሲያጣ
የታዘብን፣ ጤፍ በሶስት ሺህ ብር የሸመትን፣ ደሞዝ 3ቀን
የማይበረክትልን ፣ ኑሮ ባላየ ያለፈን፣ ፋሲካን በበግ ቅርጫ
ያከበርን እኛ የመጀመርያዎቹ ነን. . . .
_
ለእንጀራ ለሚሰደደዉ ፀልየን ሳንጨርስ እንጀራም ሲሰደድ
(ኤክስፓርት ሲደረግ) ያየን፣ ጤፍ ትቶን ላብራቶሪ የገባ፣
ማስቲካ በስድሳ ብር ገዝተን
ሳይጠዘጥዘን አላምጠን የተፋን፣
ግድግዳችንን የሚያስንቅ TV ያየን፣ በ3D የተደመምን
በ7D ነፍሳችን
እስኪወጣ የጮህን፣ ባቡር ብርቅ የሆነብን እኛ
የመጀመርያዎቹ
ነን. . .
_
ቡና ከአቦል ወዲያ አመድ አመድ ያለብን፣ ቡና በቂቤ
ያልቀመስን፣ ነጭ ጠጅ የጠጣን፣ በወጉ ያልሰከርን፣
ሲያብዱ አይተን ያበድን እኛ
የመጀመርያዎቹ ነን. . .
_
በፌስቡክ ያጨን፣ በሰርጋችን ማግስት
'ብርአምባር ሰበረል ሆ' ተብሎ ያልተዜመልን፣ ድንግልና
ከምድረገፅ የጠፋን (አይተን የማናዉቅ)፣ ቀብርን እንደሰርግ
የቀረፅን፣ ሞተን በተቀበርንበት እያለ በሚያስመኝ የሬሳ
ሳጥን ሲቀበሩ ብናይ በሟች የቀናን እኛ
የመጀመርያዎቹ ነን. . .
_
አንድ መሆን የጠፋን፣ የጀበና ቅርፆ ቢፈርስብን ክዳን
የሌለዉ ማንቆርቆሪያ መሳይ የእናት ሃገር ካርታ የሳልን፣
ከ97 የተረፍን፣ ከኢቦላ ብናመልጥ ከአይኤስ የወደቅን እኛ
የመጀመርያዎቹ ነን.
_ . . ለቦብ ሃዉልት ያቆምን፣ የኛን የረሳን የሰዉ ያሰብን፣
በሌጋሲ የተመራን በራእይ የበለፀግን፣ ታሪክ ስናነሳ ታሪክ
ስንጥል የ3ሺ አመት ታሪክ ስናጎድፍ የ24 አመት ታሪክ
ስናደምቅ የከረምን፣ መዉደቅን በተግባር የኖርን እኛ
የመጀመርያዎቹ ነን. . .
_ . . "ታሪክ የመጨረሻዎቹ
እስኪያደርገን፤ እኛ የመጀመርያዎቹ ነን!"
_
ዳንኤል ክብረት

31/07/2017

‹አባባ ተስፋዬን - ‹አንድ ሰው ሞተ› አሉ ?››
(መላኩ አላምረው)...
‹‹ወግ ትውፊት አርጅቶ
ተረክ ተሰልችቶ
መመከር ተጠልቶ
ግብረ-ገብ ተረስቶ
አባትነት ቀርቶ
በወግ በተረኩ - መክሮ ሚያስተምረው
ያ መፃኢ ትውልድ - ደግ አባት ላይኖረው
ቁጥር የሌለውን - አበ-ሀገር ቀብረው
ያላዋቂ ነገር - አንድ ሰው ሞተ አሉ
‹የአንድን ሰው ሺህነት› የማያውቁ ሁሉ !
በዘልማድ መርዶ - በተለምዶ ወሬ
‹‹አባባ ተስፋዬ አረፈ›› አሉን ዛሬ::
አካልህን አይተው ‹‹አንድ ሰው ሞተ›› አሉ;
የመንፈስህን ጽናት፣
የፍቅርህን ብዛት፣
የአዕምሮህን ምጥቀት፣
የሥራህን ጥልቀት… የማያውቁ ሁሉ !
(አንተማ ብዙ ነህ - አንድ ብቻ አይደለህም
የአንተን ‹‹ስንት መሆን›› ማያውቅ አያውቅህም፡፡)

አንተን እንደ አንድ ሰው
አንድ ጉድጓድ ምሰው
አንድ ከፈን አልብሰው
አንድ ፍትሐት አድርሰው
አፈሩን መልሰው…… ‹‹አባባ ሞተ›› አሉ፤
‹የአንድን ሰው ብዙነት› የማያውቁ ሁሉ !

የሀገሬን ወጓን
የአባትነት ሕጓን
የእምዬን ተረቷን
የባህል ትውፊቷን
የጨዋታ ፍቅሯን
የምክር ቀመሯን
የተግሣጽ ምሥጢሯን…. ጠቅልለው በመቅበር
‹‹አንድ ሰው ሞተ›› አሉ - አወይ አለማፈር !

የሁሉንም አባት
የሁሉንም ሐውልት
የሁሉንም መካር
የሁሉንም አድባር
ሥራውን ሳይቆጥሩ - ፍቅሩን ሳያስተውሉ
አካሉን ብቻ ዓይተው - ‹‹አንድ ሰው ሞተ›› አሉ ?
‹የአንድን ሰው ስንትነት›... የማያውቁ ሁሉ !

‹‹ወግ ትውፊት አርጅቶ
ተረክ ተሰልችቶ
መመከር ተጠልቶ
ግብረ-ገብ ተረስቶ
አባትነት ቀርቶ
በወግ በተረኩ - መክሮ ሚያስተምረው
ያ መፃኢ ትውልድ - ደግ አባት ላይኖረው
ቁጥር የሌለውን - አበ-ሀገር ቀብረው
ያላዋቂ ነገር - አንድ ሰው ሞተ አሉ
‹የአንድን ሰው ሺህነት› የማያውቁ ሁሉ !

14/07/2017

የዮፍታሔና የአድማሱ ነገር
(በዳንኤል ክብረት)
የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬንና የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ዐጽም በተመለከተ የሰጠውን ማብራሪያ ተመለከትኩት፡፡ ካቴድራሉ ሐሳቡን ለማስረዳት መትጋቱን አደንቃለሁ፡፡ የካቴድራሉ ሐሳብ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊት የራቀ በመሆኑ ግን ተገርሜያለሁ፡፡
ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤና መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬን በተመለከተ ካቴድራሉ ያየበት መነጽር ነው ስሕተቱን ያመጣው፡፡ ካቴድራሉ አገልጋዮቹን የሚያያቸው በቤተሰብና በጎጥ ደረጃ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን አገልጋዮቿን የምታያቸው በሀገርና ከዚያም ሲያልፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ የወሎ ቦረና፣ ቅዱስ ያሬድ የትግራይ አኩስም፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሸዋ ጽላልሽ፣ አቡነ አረጋዊ የሮም ተወላጆች እንጂ ሀብቶች አይደሉም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ ካቴድራላችን ግን የቤተሰቦቻቸውና የተወላጆቻቸው አድርጎ ያያቸዋል፡፡ ስሕተቱ የመጣው ቤተ ክርስቲያንንና ሀገርን ሲያገለግሉ የኖሩ ሊቃውንትን ዐጽም በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት መሠረት ከማፍለስ ይልቅ ‹ቤተሰቦቻቸው ተገኝተው ያፍልሱ› ብሎ ዐዋጅ ከመንገሩ ላይ ነው፡፡ የካቴድራሉ ካህናትና ዲያቆናት ለመልአከ ብርሃን አድማሱና ለቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ቤተሰቦቻቸው አይደሉምን? በዚህ ዓይነት እጨጌ ዕንባቆም ወደ የመን፣ አቡነ አረጋዊ ወደ ሮም፣ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም ወደ ግብጽ የሥጋ ቤተሰቦቻቸውን ፍለጋ ይሂዱን? ይህ የካቴድራላችን እንጂ የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አይደለም፡፡
‹ቅንጣቱ ከምሉዑ ውጭ አይሆንም› የሚል ፍልስፍና አለ፡፡ አንድ ነገር የነገሩ ማኅበረሰብ ከሆነው ውጭ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ የቤተ ዘመድና የተወላጅነት አሠራር የቤተ ክህነት ሰዎችን እየተዋሐደን ስለመጣ ሊቃውንትንና ቅዱሳንንም ከጎጥና ከቤተሰብ ውጭ ልናያቸው አልቻልንም፡፡
ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ያረፉት ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም. ነው፡፡ የዛሬ 70 ዓመት፡፡ ሊቀ ሥላጣናቱ በመግለጫቸው እንደነገሩን የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ዐጽም ተነሥቶ ሌላ ቦታ የተቀመጠው ‹የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ቤተሰቦች በወቅቱ ባለመምጣታቸው› ነው፡፡ ከሰባ ዓመት በኋላ ትውልድ እንጂ ቤተሰብ እንዴት ይገኛል? በምን ሂሳብ ነው ቤተ ክርስቲያኒቱን አምነው የዛሬ 70 ዓመት የተቀበሩትን ክርስቲያኖች ዐጽም በክብር የማፍለስ ኃላፊነት የልጅ ልጆቻቸው የሚሆነው? አሠራሩ ችግር እንዳለበት የሚያሳየው ካቴድራሉ ባስነገረው ዐዋጅ መሠረት የሚመጣ ጠፍቶ ‹ስምንት ዓመት ዐጽሙ ተነሥቶ ሌላ ቦታ መቆየቱ› ነው፡፡ የዛሬ ስምንት ዓመት ካቴድራሉ የሊቁን ዐጽም ሲያነሣ ምን በዓል አዘጋጅቶ ነበር? ለመሆኑ የእኒህን በቤተ ክርስቲያን በምርግትና ያገለገሉ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም በዓለም ዐቀፍ መድረክ ያስጠሩ፣ ቤተ ክርስቲያን እንኳን ልጄ ሆንክ ብላ የምትኮራባቸውን ሊቅ ዐጽም እያነሣ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር? ለመሆኑ የሀገሪቱ የኪነ ጥበብ ሰዎች ሳይቀር መጋበዝ እንደነበረባቸው ካቴድራሉ ያውቃል? አድባር እኮ ነው እየነቀላችሁ ያላችሁት? ታድያ እናንተ እኒህን የመሰሉ ሊቅ ዐጽም አንሥታችሁ በማይገባ ቦታ ስታስቀምጡ የሀገሩ ሰዎችማ ምን ያድርጓችሁ? ኃላፊነቱን መውሰድ የነበረባቸው ሀገርና ቤተ ክርስቲያን፣ እንደ ልኳንዳ ቤት ሥጋ ቆጥረው ኃላፊነቱን ለልጅ ልጆቹ ሲሰጡ ምን ያድርጓችሁ? ‹ተወላጆቹ› በ19/10/2009 በጻፉላችሁ ደብዳቤ ዐጽሙን ወደ ደብረ ኤልያስ(ጎጃም) የወሰዱት ሌላ አማራጭ በማጣታቸው መሆኑን ገልጠውታል፡፡ ምን ያድርጉ?
የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ጉዳይ የእኛው የራሳችን የካቴድራሉ አባቶች፣ ከዚያም አልፎ የጠቅላላዋ ቤተ ክርስቲያን፣ ተሻግሮም ሀገራችን የኢትዮጵያ ጉዳይ እንጂ የአጥንትና ጉልጥምት ጉዳይ አይደለም ብላችሁ አትመልሱም ነበር? የዮፍታሔ ታሪክ የዚህች ሀገር ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ታሪክ በሚሰጥበት ትምህርት ቤት ሁሉ ይሰጣል፡፡ የነገው ታሪክ ላይ ግን እንዲህ የሚል ትምህርት ጨምራችሁበታል ‹ካቴድራሉ ዐጽሙን አንሥቶ ለክብሩ በማይመጥን ቦታ ስላስቀመጠው፣ በተቀበሩ በ70 ዓመት እንደገና ዐጽሙ ፈልሶ፣ ዓባይን ተሻገረ›፡፡
ለመሆኑ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የማን ናቸው? የቤተሰቦቻቸው ናቸው? ያስተማሩትና የጻፉት ለቤተሰቦቻቸው ነው? የተጋደሉት ለቤተ ክርስቲያን አይደለም? ካቴድራሉ ምን ቢደፍር ነው ለቤተሰቦቻቸው ኃላፊነቱን ሰጥቶ ማስታወቂያ የሚያወጣው? ለመሆኑ በካቴድራሉ ቤተ መጻሕፍት ያሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ መጻሕፍት ይህንን ነው የሚናገሩት?
በገድለ ተክለ ሃይማኖት መጨረሻ ላይ ‹መጽሐፈ ፍልሰቱ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት› የሚል መጽሐፍ አለ፡፡ የተጻፈው በ1418 ዓ.ም. በሰባተኛው የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት በእጨጌ ዮሐንስ ከማ ነው፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዐጽም ካረፉ ከ57 ዓመት በኋላ ከደብረ አስቦ ወደ ዔላም ሲፈልስ የነበረውን ሥርዓት ይናገራል፡፡ አራተኛው እጨጌ አቡነ ሕዝቅያስ ለፍልሰተ ዐጽሙ ደቀ መዝሙሮቻቸውን ጠሩ እንጂ በጽላልሽ የሚገኙ ዘመዶቻቸውን አልጠሩም፡፡ ካቴድራሉ ግን የእኒህን ሊቅና ጻድቅ ዐጽም ለማንሣት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊት ውጭ ‹ወንድማቸው መጡ፣ ልጃቸው መጣ› በሚል ጠባብ ምልከታ ጉዳዩን ወደ ዘመድ አዝማድ አወረደው?
የሦስተኛው የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት የአቡነ ፊልጶስ ዐጽም ከደቡብ ጎንደር ደብረ ሐቃሊት ገዳም በ1481 ዓም ፈልሷል፡፡ ይህንን ታሪክም በወቅቱ የዓይን ምስክር የነበረውና ‹መጽሐፈ ፍልሰቱ ለአቡነ ፊልጶስ› የተሰኘውን መጽሐፍ በእጨጌ ጴጥሮስ ዘመን(1489-1516) የጻፈው ፍሬ ቅዱስ በሚገባ ይተርከዋል፡፡ ፍሬ ቅዱስ እንደሚነግረን ዐጽሙን ያፈለሱት ደቀ መዝሙሮቻቸውና መላው ክርስቲያኖች እንጂ ዘመዶቻቸው አይደሉም፡፡ የፈለሰውም ወደ ትውልድ ቦታቸው አይደለም፤ ወደ ገዳማቸው እንጂ፡፡ እንዲያውም በሚያስደንቅ ሁኔታ በንጉሥ ሰይፈ አርእድ ተሰደው በሄዱበት ሀገር ያረፉትን የአቡነ ፊልጶስን ዐጽም ለመጀመሪያ ጊዜ በ1411 ዓ.ም. ለማፍለስ የሞከረው በርናባስ የተባለ ከአገው አውራጃዎች በአንዷ ፍርቃ በምትባለው የሚኖር ክርስቲያን ነው፡፡ ‹ቤተሰባቸው› አይደለም፡፡ ለአባ ፊልጶስ የሥጋ ዘመዱ አይደለም፤ የመንፈስ ልጁ እንጂ፡፡ የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጉዳይ የእኛ የመንፈስ ልጆቻቸው፣ የቀለም ልጆቻቸው፣ የሃይማኖት ልጆቻቸው ጉዳይ እንጂ የሥጋ ዘመዶቻቸው ጉዳይ አይደለም፡፡ የሚመለከተው ቅዱስ ሲኖዶስንና ካቴድራሉን ነው፡፡
መጋቢት 27 ቀን 1551 ዓ.ም. ከአዳሎች መሪ ከመሐመድ ኑር ጋር ገጥሞ ንጉሥ ገላውዴዎስ ተሸንፎ ተሠዋ፡፡ አብሮት የነበረው የደብረ ሊባኖሱ አበ ምኔት እጨጌ ዮሐንስም ተሠዋ፡፡ አንድ ምእመንም የእርሱንና የአባ መቃርዮስን ሥጋ ወስዶ በትንሽ መቃብር ቀበራቸው፡፡ በኋላም ሀገር ሲረጋጋ የመንፈስ ልጁ አባ ቴዎሎጎስ ወደሚያስተዳድረው ደብር አመጣው፡፡ የአባ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የሚሆን አባ መብዐ ድንግልም ከዚያ አፍልሶ ወደ ደብረ ሊባኖስ በክብር አመጣው፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን እንጂ ቤተ ዘመድ የለበትም፡፡ ለሊቃውንትና ለቅዱሳን ቤተዘመዶቻቸው የመንፈስ ልጆቻቸው፣ ቤታቸውም ቤተ ክርስቲያን ናትና፡፡
ሩቅ ሳንሄድ ሁለት የቅርብ ዘመን ታሪክ ልጥቀስ፡፡
የአሁኑ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስና የዝዋይ ሐመረብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የሠሩትን ተጠቃሽ ሥራ መጥቀሱ ይገባል፡፡ በብጹዕነታቸው መሪነትና በአባ ማርቆስ ተፈራ አስተባባሪነት ትልቁ የዝዋይ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሲታነጽ የነፍስ ኄር የብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ (ካልዕ) ዐጽም ከትንሿ ቤተ ክርስቲያን ፈልሶ ወደ ትልቁ ደብር ገብቷል፡፡ ያን ጊዜ ግን ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ(የአሁኑ) የነፍስ ኄር አቡነ ጎርጎርዮስን ዘመዶች ከወሎ አልጠሩም፡፡ ጉዳዩ የዘመድ ጉዳይ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን ነውና፡፡ የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ትምህርት፣ መጻሕፍትና አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ነውና፡፡ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ልክ እንደ እጨጌ ሕዝቅያስ የጠሩት በመላው ዓለም የሚገኙ የቀለምና የመንፈስ ልጆቻቸውን ነው፡፡ የሰበሰቡት ጳጳሳትንና ካህናትን ነው፡፡ እንደ ካቴድራሉ ‹ዐጽም አንሡልን› ብለው ዐዋጅ አልነገሩም፡፡ በጸሎትና በቅዳሴ፣ በዝማሬና በማዕጠንት፣ እንደ ጥንቱ ሥርዓት በክብር እንዲፈልስና እንዲያርፍ አደረጉ እንጂ፡፡ ጎርጎርዮስ ጎርጎርዮስን እንዳከበሩ፣ አክባሪ ይላክላቸው፡፡
በደርግ ዘመን በሰማዕትነት አልፎ ዐጽማቸው የትም ተጥሎ የነበሩትን የታላቁን አባት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዐጽም ማፍለስ ቤተ ክርስቲያናችን ‹ቤተሰቦቻቸውን› በዐዋጅ አልጠራችም፡፡ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መሪነት ራስ ቅዱስ ሲኖዶሱ በክብር አፍልሶ ወደ ጎፋ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አፈለሰው እንጂ፡፡ ይህ የሆነው ግን አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመድ ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም፡፡
ካቴድራላችን ይህንን ትውፊት እንዴት ዘንግቶት ነው ጉዳዩን አውርዶ የቤተሰብና የተወላጅ ያደረገው? እንዴው ስንቱን ነገር አውርደንና ወርደን እንችለዋለን? ይህንን በዘመድ መሥራት መቼ ነው የምንተወው?
ይላል ጋዜጣው፡፡ ባያመለክቱስ ኖሮ ምን ልታደርጓቸው ነበር? እንደ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ አንድ ቦታ ከትታችሁ የተናደደ ወገን ሲመጣ ወንዝ ልታሻግሩ? ለመሆኑስ ከልጃቸው ባለቤት ይልቅ ለመልአከ ብርሃን አድማሱ እናንተ አትቀርቧቸውም? ለመሆኑስ ይህን ከማን ነው የተማራችሁት?
አሁንም ሦስት አካላት እንዲያስቡበት አደራ እላለሁ፡፡ ሲኖዶሱ፣ ካቴድራሉና ምእመናኑ፡፡ ሲኖዶሱ ቢያንስ ቢያንስ ነግ በኔ ብሎ ጉዳዩን በቤተ ክርስቲያኒቱ ደረጃ መመልከት አለበት፡፡ ሊቅ አይውጣላችሁ ተብለን ተረግመን ካልሆነ በቀር፡፡ ካቴድራሉም አሁን እንዳደረገውና እንደሚያደርገው ‹የልጅ ሚስት፣ የልጅ ባል› የሚባለውን ጨዋታ ትቶ ጉዳዩን የቤተ ክርስቲያኒቱ ያድርገው፡፡ ያ ካልሆነ ደግሞ እኛ ምእመናን መንግሥትንም ሆነ ቤተ ክርስቲያንን ጠይቀን ለክብራቸው የሚመጥን ሥራ እንሥራ፡፡ ቢያንስ ከታሪክ ተወቃሽነትና ከርግማን እንድናለን፡፡

11/07/2017

ካልፎሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ
(ታሪካዊ ልቦለድ)
(በእውቀቱ ስዩም)
To be honest with you ሲያትል በተደረገው የዲያስፖራ
የግርኳስ ውድድር ወደ ሚደረበት ስቴዲየም የሄድኩት
ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ሳልነካካ መፅሃፌን ሸጬ
አገሬ ለመግባት ነበር፤
(ከመፅሃፍ ሻጭ የሚገኘው ገቢ አስር በመቶ ለእኔ ሲሆን ፤
ቀሪው ለቤት አከራየ ለጋሽ ጣሰው መጦርያ ይሆናል)
እና እዚያ ስደርስ፡ ከመላው አሜሪካ የመጣ ህዝበ -ዲያስፖራ
ወደ ስቴድየሙ በር ይንቆረቆራል፤
የስደት ወዳጁን ለማግኘት የመጣ! ያበሻ ፊት ናፍቆት የመጣ!
የነገስታት ፊት የታተመበት ካናቴራ ሊቸበችብ የመጣ!
የመጨረሻ የጠበሳ ሙከራ ለማድረግ የመጣ! የእግኳስ
ፍቅር ነድቶት የመጣ::ዝምብሎ መሄጂያ አጥቶ የመጣ::
በየፍላጎቱ ተመርቶ የመጣ ያገርሰው -ስቴድየሙን ወረሰው::
ከሜዳው ራስጌ ላይ ባለው ስፍራ ላይ የሸቀጥ መሸጫ
ድንኳኖች ተደርድረዋል፡፡
አንዱ ድንኳን አጠገብ ሄጄ ቆምኩ፡፡ ወደ ድንኳኑ በር
ስመለከት"የኢሳት ቲሌቭዥን ጊዚያዊ ጣቢያ "የሚል ፅሁፍ
ጋር ተገጣጠምሁ:: ፈጠን ብየ ስልታዊ ማፈግፈግ አረግሁ::
አፈግፍጌ የተጠለልኩበትን ድንኳን ቀና ብየ ሾፍ ሳረግ"
ኢህአፓ" የሚል ተፅፎበታል:: አጥብቄ ሮጥሁ :: በመስኩ ላይ
እንደቄጤማ የተነሰነሰ" ቦይኮት ጎሳየ ተስፋየ" የሚል
ማሳደሚያ ፖስተር እየደቀደቅሁ ሮጥሁ:: ግን ብዙ
አልሮጥኩም:: የብሬ ነጋ መልክ የታተመበት ቲሸርት የለበሰ
ወጣት ጋር ተላተምኩ:: ወጣቱ ማጅር ግንዴን ይዞ ሰልፊ ሊነሳ
ሲጥር አምልጨው ሸሸሁ:: በዚህ አይነት ሳፈገፍግ
ከስቴድየሙ ልወጣ ትንሽ ነበር የቀረኝ::
በመጨረሻ "በውቄ ከፈለግህ ይህን ጠረጴዛ መጠቀም
ትችላለህ" የሚል ድምፅ ሰማሁ፤
ዞር ስል የፌስቡክ ባለንጀራየ አዲስ ናት:: ከባለቤቷ ጋር ሆነው
አንድ ጠረጴዛ አዋሱኝ:: ጠረጴዛው ላይ መፃህፎቼን ዘርግቼ
ሸማች መጠባበቅ ጀመርሁ::
ብጠብቅ ብጠብቅ ብጠብቅ መጣፌን አደለም የሚገዛ ዞር
ብሎ የሚያይ የለም::
ፒፕሉ ተጉዳይ ሳይጥፈኝ ተፊትለፊቴ እየተጋፋ ይነጉዳል::
በጋ ስለሆነ ወንዱም ሴቱም ባለቁምጣ ነው:: ለምን እንደሆን
እንጃ ከሰሜ ባላገሩ በቀር ቁምጣ የሚያምርበት ያበሻ ወንድ
ገጥሞኝ አያውቅም:: ሰሜ ባላገሩ ያን የመሰለ አርበ -ሰፊ
ቅልጥም ይዞ ለምን ለብሄራዊ ቡድናችን እንደማይጫወት
አይገባኝም:: ያብዛኞቻችን እግር በቁምጣ ማሃል ሲታይ
የመፈክር እጀታ ይመስላል:: ቁምጣን ሴቶቻችን ይታጠቋት!!
የተልባ ማሻው ሚካየል ያለህ! ያንዲቱ እግር ላይ አይኔን
ተክየ ያለሁበትን ረሳሁ:: የድሃ አገር ተወላጅ መሆኔን ረሳሁ::
ከነጋ አንዲት መፃፍ እንኳን አለመሸጤን ረሳሁ:: ልጂቱ ይባስ
ብሎ በታፋዋ ላይ የይሁዳ አንበሳን ተነቅሳዋለች:: ተራማጁ
ሰውየ በሰኮንድ የድሮ ናፋቂ ሆንሁ:: ወያኔ ነፍስህ አይማርም!
ስንት መንደፍያ እግር በቸርቺል ጎዳና እየተርመሰመሰ አሁን
ይህን የመሰለ ታፋ መሰደድ ነበረበት?
ዞር ስል አንድ ጎረምሳ ሚጢጢ ባንዲራ በሁለት ሁለት ዶላር
ሲቸበችብ ሾፍኩት:: ግዞተኛው እየተጋፋ ይሸምታል::
ባንዲራ ሻጩ በግራ እጁ የኪሱን ተርዚና በዶላር እየወጠረ
በቀኝ እጁ በያዘው ማይክ " እንዲህ ነው ኢትጵያዊነት !" እያለ
ያሟሙቃል::
ከሁለት ሰአት ጥበቃ በኃላ አንዱ መጥቶ መፅሀፍ ገዛኝ::
ማመን አቃተኝ::
እጄን ትከሻው ላይ ጭኘ እንዲህ ስል መረቅሁት::
"እጅህን ከቁርጥማት -ጉሮሮህን ከቢራ ጥማት ይሰውረው::
ከይሉኝታ ቢስ ቀፋይ- ጠላ ጋብዞ ውስኪ ከሚያስከፍል ግብር
አስከፋይ -ይሰውርህ!
ደስታህ ፍፃሜ አይኑረው:: ሞትህን ያስቀረው:: ካልሆነ
አሟሟትህን ያሳምረው- እግርህን በቀይ ምንጣፍ ላይ
ያውለው- ስንቅህን ያክብደው እዳህን ያቅለለው-
አለባበስህን ፋሺን-ኪስህን ATM ማሺን ያርግልህ-
ምቀኛህን ለዘብጥያ ይዳርግልህ..
ጠላቶችህ እንደባዘቶ ይዳመጡ-ሽንት ቤት ሲቀመጡ-
ይበርታባቸው ምጡ-"
በመጨረሻ ያትላንታው ወዳጄ ፊደል -ኮስታሮ ከፊቴ መጥቶ
ተገተረ::
"ይሄ ነገር ተዝፍዝፎ ቀረ እንዴ?" አለኝ ወደ መፃፌ ባገጩ
እየጠቆመ::
እንግዲህ ምን ማድረግ ይቻላል ?! በሚል አይነት እጄን
ዘረጋሁ::
"ለመጣፍ ሽያጭ ማስታወቂያ ወሳኝ ነው!! አሁን ተመልከት
እንዴት እንደምቀውጠው!" አለና ከመፃፌ መካከል ሁለት
አንስቶ ያዘ:: ከዚያ በቀኝ እጁ ይዞት የነበረውን ጥሩንባ
አውጥቶ ድብልቅልቅ አድርጎ ነፍቶ " እንዳያመልጣችሁ" ብሎ
ጮኸ::
የጥሩባውን ልፈፋ ተከትሎ ብዙ አጃቢ ከበበን:: ከከባቢዎች
አንዱ ጠጋ አለና እንዲህ አለ::
"ነፍሴ! እሱን ጥሩንባ ስንት ትሸጥልኛለህ?"

Address

Bahir Dar
AAIT

Telephone

+251912662981

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when St.George United Engineers posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share