24/10/2020
በሀገራችን የሚገኘው የረድኡ ሐዋርያ የቅዱስ ፊሊጶስ ቤተክርስቲያን-"ደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ ካቴድራል!"
ይኸውም ሐዋርያ ቅዱስ ፊሊጶስ እግዚአብሔር ልኮት ኢትዮጵያዊውን ጃንረባ ባኮስን ያጠመቀው ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታረክ፣ ምስረታ እና ልደት የሚያወሳ የታሪክም ሆነ የቤተክርስቲያን ምሁር ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስን እና ቅዱስ ባኮስን ሳያነሳ ማለፍ አይቻለውም፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እንዲሰበክ መነሻ የሆኑ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የወንጌል አባታቶቻችን ስለሆኑ ነው፡፡ ሐዋ 8፣ 26-39።
✞ ✞ ✞
አ.አ ኮልፌ አጠናተራ የሚገኘው የቅዱስ ፊልጶስ ካቴድራል ሊመሠረት የቻለው በወቅቱ በአዲስ አበባ አድባራት ከፍተኛ የሆነ የቀብር ቦታ እጥረት ስለነበር 700 የሚደርሱ እድርተኞች መዘጋጃ ቤት በመሄድ ቀብር ቦታ ይሰጠን በማለት በማመልከታቸው ምክንያት ኮልፌ አጠናተራ እስላም መቃብር ፊት ለፊት ያለው ባዶ መሬት እንዲወስዱ ተፈቀደላቸው፡፡ ነገር ግን የተፈቀደላቸው ቦታ አቶ ስፍር መዝጊያ የሚባሉ ግለሰብ ይኖሩበት ስለነበር እድርተኞቹ ቦታውን ለቀብር ቦታ እንደሚፈልጉት ገለጹላቸው፡፡ አቶ ስፍርም በህልሜ እዚህ ቦታ መኖር እንደማልችል ታይቶኝ ነበር በማለት በ45,000 ብር በመሸጥ ለቀቁላቸው፡፡ ከዚህም በመቀጠል ፍቃድ ለማግኘት ወደ ቤተክህነት የእድሩ ሊቀመንበር አቶ አበባው ግዛው እና አቶ ወልደ ሚካኤል እና ሌሎችም በመሆን በጊዜው የኢ/ኦ/ተ ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ተክለሃይማኖት በመሄድ ስለሁኔታው በግልጽ ቦታውን እንዲባርኩላቸው ጠየቁ፡፡ አባታችንም ክርቲያን ቤተክርስቲያን በሌለበት ቦታ አይቀበርም ብለው በመመለሳቸው የእድሩ አባላት በአማኑኤል ቤተክርስቲያን ተሰብስበው ተወያዩ፡፡ በውይይታውም አቶ ስፍር ይኖሩበት የነበረውን ቤት እንደቤተክርስቲያን ለመጠቀም በመነጋገር ወደ አቡነ ተክለሃይማኖት ሄደው ሀሳባቸውን ገለፁላቸው፡፡ ብፁእ አባታችንም ፈቃዳቸው ሆኖ ጊዜያዊ ወደፊት ግን ቤተክርስቲያን ስሩለት በማለት ቤተክርስቲያን ለመሆን የሚያባውን ጸሎት በማድረግ ከመኖርያ ቤተ ወደ ቤተክርስቲያን የካቲት 20 ቀን 1978 ዓ.ም ሃያ አራት ሊቃነ ጳጳሳት በማስከተል የዲያቆኑን የቅዱስ ፊልጶስ ታቦትን አምጥተው ቤተከልርስቲያኑን መሠረቱት፡፡ ቤተክርስቲያኑን እንዲያስተዳድሩ ለሊቀ ካህናት ክፍሌ ገ/መስቀል ጽላቱን ደግሞ ለጳውሎስ ካህን ለነበሩት ለቄስ ዘመንፈስ በአደራ አስረከቧው፡፡ በዕለቱም ጥቅምት 14 እረፍቱ፣ የካቲት 20 ቅዳሴ ቤቱ በጋራ እንዲያከብሩ በማሳሰብ ተናገሩ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኃላም በቆርቆሮ የተሰራ መቃኞ በማዘጋጀት ታቦቱ ወደዚያ ገባ፡፡ አሁን ላይ በዚህ መልኩ በሚያምር ሁኔታ የተሠራው የደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ ካቴድራል ተሠርቶ አልቆ የተመረቀው ጥቅምት 14 ቀን 2000 ዓ.ም ሲሆን አሁን ላይ ካቴድራሉ 34 ዓመት ሆኖታል፡፡
የቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለውለታ የሆነው የጥምቀት የክርስትና አባታችን የሐዋርያው የቅዱስ ፊልጶስ በዓለ ዕረፍት ጥቅምት 14 ቀን አዲስ አበባ ኮልፌ አጠና ተራ በሚገኘው በደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ ካቴድራል በደመቀ ሁኔታ ይከበራል።
የሐዋርያ የቅዱስ ፊሊጶስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!