Bini

Bini marketing

26/06/2024
05/05/2022

+ ከሁሉ በኋላ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ታየኝ +

ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን ስለ ጌታ ትንሣኤ ማስረጃ እያቀረበ ነው:: በዚያን ዘመን ለጌታ ትንሣኤ ማስረጃ ስትጠቅስ በማቴዎስ ወንጌል እንዲህ ይላል ብለህ እንዳትጠቅስ ገና ወንጌላት አልተጻፉም:: ቢጻፉም ማቴዎስ በሕይወት እያለ በቃሉ መመስከር ሲችል ጽሑፉን ማስረጃ ማድረግ አያስፈልግህም:: ስለዚህ ለመነሣቱ ማስረጃዎች ከተነሣ በኋላ ያዩት ሰዎች ነበሩ:: በሕይወት ያሉትን የዓይን ምስክሮችን መጥቀስ ይቻላል:: የዓይን እማኞች ምስክርነት ከጽሑፍ በላይ የታሪክ ማስረጃ ነው:: ስለዚህ ጳውሎስ ስለ ጌታ ትንሣኤ "እነ እገሌ አይተውታል" እያለ መዘርዘርን መረጠ::

ጌታ ከተነሣ በኋላ እንደ ቀድሞው ለሁሉ አልታየም:: እርሱን ለማየት የተገባቸው ጥቂት ወደ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ነበሩ:: በማኅበር ያዩት አሉ:: በግል ያዩት አሉ::
ያዩት ነገር ወንጌል የሆነላቸው ብፁዓን ዓይኖች ያሏቸው እንዴት የታደሉ ናቸው? የተሰቀለውን ተነሥቶ ያዩት! ዳግም በሚመጣበት አካል የተገለጠላቸው ምንኛ የታደሉ ናቸው? ከመድኃኔ ዓለም አፍ ተቀብለው ኪዳን ያደረሱ! የጌታን ቅዳሴ ተቀብለው ያስቀደሱ! የትንሣኤው ማግስት ምስክሮች እንዴት ዕድለኞች ናቸው? ቢሞቱም እንኳን መነሣታቸውን በጌታ ትንሣኤ አይተው ደስ ብሎአቸው ያንቀላፉ እነርሱ ምንኛ የታደሉ ናቸው?

ቅዱስ ጳውሎስ በወንጌል ከተጠቀሱት ከነ ኬፋ በተጨማሪ ለይቶ ጌታ ለማን ለማን እንደታየ ገለጸ:: ለያዕቆብ ታየ ብሎ የእልፍዮስን ልጅ ለይቶ ጠቀሰው:: የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፍት እንደሚሉት ይህ ሐዋርያ ከሌሎች በተለየ የጌታን ትንሣኤ ሳላይ እህል አልቀምስም ብሎ የተሳለና አክፍሎትን የጀመረ ነበርና ጌታ ለይቶ ክብሩን አሳይቶታል:: ከዚያም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ ብሎ የጌታን ድኅረ ትንሣኤ አስተርእዮ ዘረዘረ:: እኔ ማለትን የማይወደው ትሑት ቅዱስ ጳውሎስ "ከሁሉ በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ አለ::

ጭንጋፍ ምንድር ነው? ጭንጋፍ (ጸዕጻዕ/ ተውራድ) ለፅንስ የሚነገር ቃል ነው:: መወለድ ያለበትን ጊዜ ያልጠበቀ ያለ ጊዜው የተወለደ ፅንስ ነው:: በመጠኑ ከሌላው ጊዜውን ከጠበቀ ፅንስ የሚያንስ ሲሆን ዕድገቱን በተገቢው ጊዜ ከሚወለድ ልጅ ጋር ለማስተካከል ሲባል በሙቀት ማቆያ ክፍል እንዲቆይ ይደረጋል:: ይህ ፅንስ ሲወለድ በሕመም ውስጥ ሆኖ ተሰቃይቶ ተጨንቆ ነው::

ቅዱስ ጳውሎስ ራሱን ለመግለጽ የተጠቀመበት ይህ አንድ ቃል የሕይወት ታሪኩን ጠቅልሎ የያዘ ድንቅ ቃል ነበር::
ቅዱስ ጳውሎስ ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያን ብርሃን የሆነ ሐዋርያ ቢሆንም እንደ ዓሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በጊዜው የተጠራ አልነበረም:: እርሱ ከሐዋርያት ጋር አብሮ በዳግም ልደት የተወለደ ሳይሆን ያለ ጊዜው ክርስቶስ ባረገ በስምንተኛው ዓመት የተጠራ ነበረና ራሱን ካለ ጊዜው ከተወለደው ፅንስ ጋር አመሳስሎ እንደ ጭንጋፍ የምሆን ብሎ ጠራ::

ጭንጋፍ ሲወለድ በመጠኑ ከሌላው ፅንስ ያነሰ ይሆናል::
ቅዱስ ጳውሎስም ራሱን ጭንጋፍ ካለ በኋላ "እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ" ብሎ አብራርቶታል:: (1ቆሮ 15:9)

ልጅ ጭንጋፍ ሆኖ ሲወለድ በሥቃይ ነው:: ጤና ያጣል ይታመማል:: እናቲቱም ትታወካለች በድብታ በጭንቀት ትቸገራለች:: ባለሙያዎቹ እንደሚሉት እናት ያለ ጊዜው ከተወለደ ልጅዋ ጋር እናታዊ ትስስር ለመፍጠርና የእናትነት ፍቅርዋን ለመሥጠት ባልጠበቀችው ጊዜ የመጣ በመሆኑ ምክንያት ለጥቂት ጊዜ ትቸገራለች:: በአጭሩ ጭንጋፍ ሆኖ ሲወለድ እሱም ይሰቃያል እናቱንም ያስጨንቃል:: ወዲያው እንደሌላ ሕፃን በሰው እጅ አይታቀፍም:: ከተፈጥሮአዊ እስከ ሰው ሠራሽ እንደየጊዜው እየዘመነ በሔደው የልጅ ሙቀት መስጫ መንገድ እየታገዘ የሰውነት አካሎቹ በአግባቡ መሥራት እስከሚችሉና በሽታ መቋቋም እስከሚችል ይቆያል::

ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ጭንጋፍ ነበርኩ ያለው ለዚህ ነው:: በዳግም ልደት የተወለደው በደማስቆ መንገድ ወድቆ ሊቋቋመው ባልቻለው ብርሃን ተመትቶ ነበር:: "ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ?" የሚል ድምፅ ሲሰማ ፅንስ ነውና ዓይኑን እንኳን መግለጥ አልቻለም ነበር::
ከተወለደ በኋላም ወዲያው ወደ ቤተ ክርስቲያን እቅፍ ወደ ሐዋርያት ማኅበር አልገባም:: እንደ ጭንጋፍ የምሆን እንዳለ ሙቀት ያስፈልገው ነበርና የሰው እጅ ሳያቅፈው ሦስት ዓመት በሱባኤ ቆይቶ በመንፈስ ቅዱስ ተማወቀ::

"ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥ ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። ከሦስት ዓመት በኁዋላ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ" ብሎ ስለ መንፈሳዊ ኃይል መልበሱ ይናገራል:: (ገላ 1:15-18)

ጭንጋፍ ሆኖ የተወለደ ልጅ የሚገጥመው ችግር ከወላጆቹ ጋር በሥነ ልቡና ለመተሳሰር መቸገሩ ነው::
ቅዱስ ጳውሎስን ለማመንና እንደ ልጅ ለመቀበል የቤተ ክርስቲያን ማኅበርም ተቸግራ ነበር::
"ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርት ጋር ይተባበር ዘንድ ሞከረ፤ ሁሉም ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ ስላላመኑ ፈሩት" ሐዋ 9:26 ስለዚህ ሐዋርያው እንደ ጭንጋፍ ነኝ አለ::

ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታ መነሣት ምስክሮች ብሎ ሌሎችን ከዘረዘረ በኋላ "ከሁሉ በኋላ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ታየኝ" ብሎ ተናገረ:: ክርስቶስ ተነሥቶአል ወይ ብለው ሲጠይቁህ አዎ ተነሥቶአል እነ እገሌ አይተውታል ብለህ ዘርዝረህ
"ከሁሉ በኁዋላ ለእኔም ታየኝ" ብለህ መናገር መቻል እንዴት መታደል ነው!?

ወዳጄ ክርስቶስ መነሣቱን ታምናለህ:: ልክ ነህ ለብዙዎች ታይቶአል:: አንተስ ከሁሉ በኁዋላ ለእኔም ታየኝ ማለት ትችል ይሆን? ጌታ ከተነሣ በኁዋላ ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ለብዙዎች ታይቶአል:: ብዙዎቹ ቅዱሳን አይተውታል:: ቅዱስ እስጢፋኖስ አይቶታል : ቅድስት አርሴማ አይታዋለች : አቡነ ተክለ ሃይማኖት አይተውታል : አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ተመልክተውታል:: አባ ጳኩሚስ በዕንባ ተመልክቶታል : ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ አይታዋለች::

ሁሉም ቅዱሳን ብዕር ቢሠጣቸው ከዕንባ ጋር
"ከሁሉ በኁዋላ ለእኔም ታየኝ" ብለው የትንሣኤውን ማስረጃ ዝርዝር ይቀጥላሉ:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በበረሃ ሲጸልይ አይቶት ነበርና ሰው ባገኘ ቁጥር
ወቅቱ የፋሲካ ሰሞን ባይሆንም እንኳን በፈገግታ ተሞልቶ
"ክርስቶስ ተነሥቶአል!" ብሎ ያበሥርና ሰላምታ ይሠጥ ነበር::

ጌታ ሆይ ለእኔ ለኃጢአተኛው የምትታየኝ መቼ ይሆን? ቸርነትህን አይቻለሁ! ፍቅርህን አይቻለሁ! ብሩሕ ገጽህን የማየው መቼ ይሆን? መች እደርሳለሁ የአምላኬንስ ፊት መቼ አየዋለሁ? እኔም እንደ ቅዱሳንህ "ከሁሉ በኁዋላ ለእኔ ታየኝ" ብዬ የተቀመጠውን ብዕር አንሥቼ የምጽፈው መቼ ይሆን? አቤቱ ፊትህን እሻለሁ! አቤቱ ፊትህን ከእኔ አትመልስ! አቤቱ ፊትህን እሻለሁ!

"ኢየሱስ ክርስቶስ በግዕ ዘቀራንዮ
ለላሕይከ ንትሜነይ ከመ ንርአዮ"
"የቀራንዮው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ
ውበትህን ልናየው እንመኛለን"

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ማዕዶት 2012 ዓ ም
አዲስ አበባ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-

የፌስቡክ ገጽ :- https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
የቴሌግራም ቻናል : https://t.me/deaconhenokhaile
የዩቲዩብ ገጽ: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g

23/04/2022

ቀዳም ሥዑር
የተሻረችው ቅዳሜ

* በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የምናገኛት የዛሬዋ ዕለት "ቀዳም ሥዑር" ትባላለች፡፡ በዚች ዕለት ከወትሮው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ ለመዘከር በጾም ታስባ ስለምትውል "የተሻረችው ቅዳሜ" ትባላለች፡፡

* የማትጾመዋ ቅዳሜ ስለምትጾም ስዑር /የተሻረች/ ተብላለች።

* በቀዳም ሥዑር ሌሊት ሥርዓቱ የሚጀመረው በመኀልየ ሰሎሞን ምንባብ ነው፡፡ ማኀሌቱም እዝሉ እየተቃኘ እየተመጠነ፣ እየተዘመመ እየተመረገደ እየተጸፋ ያድራል፡፡

*በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጤማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጨሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡

* ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለሆነ "ለምለሟ ቅዳሜ" ተብላም ትጠራለች።

* ቀጤማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል፡፡

* በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለዓዋዲ/ እየመቱ "ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ" የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር፤ ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡

* ምእመናኑም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ቄጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሠሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡

* የቀጤማው አመጣጥና ምስጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

* ምድር በጥፋት ውኃ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሰረችው ቀጤማ ይዛ በመግባት ነው፡፡ ቀጤማው የትንሳኤው ብስራት ምልክት ነው።

* ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ሁሉ ያረፈባት በመኾኑ ቅዱስ ቅዳሜ ተብላም ትጠራለች፡፡

* በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፣ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብላለች፡፡

፨፨፨

ለትንሳኤው ያብቃን!!!

17/04/2022

+ ንጉሥ በአህያ ላይ ++
(ሽራፊ ሃሳብ ከሆሳዕና ምንባብ)

"አህያ" ስምዋ ስድብ ከሆነ የቆየች እንስሳ ናት። የዚህች በዓለም ሁሉ የምትገኝ እንስሳ የሕይወት ታሪክዋ በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው። በሚበዙት ሀገራት አህያ ከባድ ሸክም ስትሸከም ትውላለች ፣ ደክሟት ለማረፍ ብትፈልግና ሸብረክ ብትል እንኳን በዱላ የሚመታት እንጂ "እስቲ አረፍ በይ" የሚላት የለም። ጀርባዋ በሸክም ብዛት የቆሰለ ፣ እግርዋ በጭነት ብዛት የተብረከረከ ፣ ዱላ ያስመረራት ፣ ዕረፍት የናፈቃት እንስሳ ናት።

ይህችን የተዋረደች እንስሳ በኪሩቤል ላይ የሚቀመጠው ሰማያዊው ንጉሥ ክርስቶስ በትሕትናው ዙፋኑ አደረጋት። ዱላ በለመደችው ፣ ዕረፍት በናፈቃት በዚህች ምስኪን ላይ "ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜ ቀሊል ነው" ያለው ንጉሥ ተቀመጠባት።

ኃያላን ነገሥታት ባማረ ሠረገላ ላይ ሆነው ፣ በሠራዊት ታጅበው ፣ ነጋሪት እያስመቱ ፣ መለከት እያስነፉ ፣ ሰይፍ በታጠቁ ጦረኞች እየተፎከረላቸው ወደሚገቡባት ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በአህያ ላይ ተጭኖ ፣ በዓሣ አጥማጆች ተከብቦ ፣ በሕፃናት ዝማሬና በዘንባባ ዝንጣፊ ታጅቦ ገባ።

ፈርተውት ሳይሆን ወደውት የሚዘምሩለት ንጉሥ ፣ ልብስ ገፍፎ የሚረግጥ ሳይሆን ልብሳቸውን አውልቀው ረግጠህ እለፍ የሚሉት ንጉሥ ፣ በቅንጦት ሠረገላ የሚሣፈር ሳይሆን "በአህያ ላይ ከተቀመጥኩ ይበቃኛል" የሚል ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ።

"የጽዮን ልጅ ሆይ ደስ ይበልሽ ፣ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያና በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል" የተባለላት ኢየሩሳሌም ምንኛ የታደለች ናት? "የዋህና ትሑት ንጉሥ" ያላት ሀገር ፣ ከተማይቱን እያየ የሚያለቅስላት ንጉሥ ፣ መልካምነቱን ለመሸፈን የሚፈልጉ ሰዎች ስለ እሱ አትናገሩ ቢሉ እንኳን የቢታንያ ድንጋዮች አፍ አውጥተው የሚመሰከሩለት ንጉሥ ያላት ኢየሩሳሌም ምንኛ የታደለች ናት? የታሰሩትን አስታውሶ "ያስፈልጉኛል ፣ ፈትታችሁ አምጡልኝ" የሚል ንጉሥ የነገሠባት ፣ ዘንባባ ተይዞ ስለ ሰላም የተዘመረባት ፣ "ሰላምሽ ዛሬ ነው" የተባለላት ያቺ ከተማ ምንኛ የታደለች ናት?

ወደ አህያይቱ ነገር እንመለስ ያቺን "ሸክም ያቆሰላትን ፣ ዕረፍት የናፈቃትን አህያ ክርስቶስ ፈትታችሁ አምጡልኝ ብሎ ዙፋኑ አደረጋት" የሚለው ታሪክ ለአህያ ብቻ ክብር የተሠጠበት ቀን መሆኑን የሚያሳይ ከመሰለን የዋሆች ነን። አህዮች አንብበው የማይጽናኑበት ወንጌል ላይ ይህ ክስተት የተጻፈው ለእኛ እንጂ ለምንም አይደለም።

እንደ አህያ ዕቃ ባንሸከምም ፣ ጀርባችን ባይቆስልም የልባችን ጀርባ በኃጢአት ሸክም የጎበጠ ፣ በበደል ብዛት የቆሰለብን ብዙዎች ነን። "መቼ ነው ይህንን የኃጢአት ሸክም አራግፌ ዕርፍ የምለው?" እያልን የምንሠቃይ ሞልተናል። መድኃኔ ዓለም ያኔ የላካቸውን ካህናት ዛሬም ወደ እኛ ልኮ "ፈትታችሁ አምጡልኝ" ብሎ እኛንም ቢያስፈታን ምናለ? እኛን ይፍቱኝ ለማለት ያብቃን እንጂ ጌታ ለካህናቱ "የፈታችሁት የተፈታ ይሆናል" "ፍቱትና ይሒድ" ብሎ ካዘዘስ ቆይቶአል::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሆሳዕና 2010
ናይሮቢ ኬንያ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-

የፌስቡክ ገጽ :- https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
የቴሌግራም ቻናል : https://t.me/deaconhenokhaile
የዩቲዩብ ገጽ: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g

12/04/2022

ፖሊስ ሌባን ከመያዙ በፊት ደውሎ "እየመጣን ነው" ይላል እንዴ? ዌል... እንደዛ ካለ የሆነ ችግር አለ ማለት ነው!

ሌብነት እና ብልሹ አሰራር በዘመቻ፣ ቀነ ገደብ በማስቀመጥ እና ደጋግሞ ዜና በማሰራት አይጠፋም። It rather needs structural adjustments and critical thinking in each level of the government so as to make it impossible for thugs and crooks make profits out of their own criminal activities.

Address

Addis Abeba
Dessie

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Bini posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share