18/03/2022
Amhara National Regional State Environment and Forest Protection Authority
4 ኤፕሪል 2019 ·
የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ መመሪያ ቁጥር 001/2010 ክፍል 2 የቀጠለ……………..
1 የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ሪፖርት ዝግጅት
የሚዘጋጀው የአካባቢ ተፅእኖ ግምገማ ሪፖርት የኘሮጀክቱን አሉታዊና አወንታዊ ተጽዕኖዎች የለየ፣ ፕሮጀክቱ ሲተገበር ስለሚወሰዱ የአካባቢ ተጽዕኖ ማቃለያ እርምጃዎች በቂ መረጃ የያዘ መሆን አለበት፡፡ የፕሮጄክቱ ባህሪ የሚያስገድድ ካልሆነ በቀር ሪፖርት የሚቀርበው በአማርኛ ቋንቋ ይሆናል፡፡
የፕሮጄክቱ ባለቤት የውጭ አገር ዜግነት ያለው ከሆነ በእንግሊዝኛ ሪፖርት ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ከሚቀርበው ሪፖርት ውስጥ የአካባቢ አያያዝና የክትትል እቅዱ ክፍል በአማርኛ ተተርጉሞ የሪፖርቱ አካል ሆኖ ይቀርባል፡፡ የአካባቢ ተጽዕኖ ጥናት ዘገባ ሲዘጋጅ መካተት የሚገባቸዉ ዝርዝር ጉዳዮች የሚከተሉት ይሆናሉ፡-
1.1 አጠቃላይ መግለጫ (Executive Summary)
ይህ ክፍል ከሁለት ገጽ ያልበለጠ ሆኖ የፕሮጀክቱ ገምጋሚዎችና ውሳኔ ሰጭ አካላት የፕሮጀክቱን ምንነት፣ ተጽዕኖዎችንና የተጽእኖ ማቃለያ መንገዶችን በቀላሉ እንዲረዱት የሚያስችል ክፍል ነው፡፡ በመሆኑም አጠቃላይ መግለጫው ስለፕሮጀክቱ ግልፅ፣ ትክክለኛና የማይጣረስ መረጃ ሊይዝ ይገባል፡፡
ይህ ክፍል ገምጋሚዉ የውሳኔ ሀሳብ ለመስጠት የሚያግዙትን ዋና ዋና ግኝቶችና ምክረ-ሀሳቦች የሚዳስስበት ክፍል ነው፡፡ በዚህ ክፍል የሚከተሉት ጉዳዮች መካተት ይኖርባቸዋል፡- የፕሮጀክቱ ስምና አድራሻ (መገኛ ቦታ)፤ የፕሮጀክቱ ባለቤት ስም፤ ጥናቱን ያጠናው አማካሪ ድርጅቱ ስም፤ የፕሮጀክቱ ምንነት አጭርና ግልጽ ማብራሪያ፤ የፕሮጀክቱ ቦታ አጭርና ግልጽ የመነሻ መረጃ፤ የፕሮጀክቱ አማራጮች፤ በፕሮጀክቱ ምክንያት ይከሰታሉ ተብሎ የሚገመቱ ዋና ዋና የአካባቢ ተፅእኖዎች፤ የተለዩ የተጽእኖ ማቅለያ ዘዴዎች (የገንዘብ ወይም በአይነት ካሳን ጨምሮ)፣ የአካባቢ ክትትል ስራዎችና የማስተግበሪያ ስልት፡፡
1.2 መግቢያ (Introduction)
ይህ ክፍል የፕሮጀክቱ አጠቃላይ የመነሻ ሀሳብ የሚገለጽበትና የአካባቢ ተፅዕኖ ጥናቱ አደረጃጀት የሚመላከትበት ክፍል ሲሆን ጽሁፉ ከሁለት ገጽ መብለጥ የለበትም፡፡ የጥናቱም መግቢያ የሚከተሉትን ነጥቦች በግልፅ ማሳየት ይኖርበታል፡፡
1) የፕሮጀክቱ ወይንም የጥናቱ መነሻ ሀሳቦች፤
2) የፕሮጀክቱ ፕሮፖዛል መግለጫ ባጭሩ (ዓላማ፣ የፕሮጀክቱ መገኛ ቦታ፣ የተለዩ አማራጮች ለምሳሌ ከቦታ፣ ከዲዛይን፣ ከአሰራር ሂደት፣ ከሚጠቀምበት ቴክኖሎጂ፣ ከግብዓትና ጥሬ ዕቃ አንጻር ወዘተ፣ የሚጠይቀውን የኃይል ዓይነት፣ ፍጆታና ምንጭ እንዲሁም የሌሎች ሃብቶችን ፍላጎትና የፕሮጀክቱን የቆይታ ጊዜ)፤
3) የአካባቢ ተጽእኖ ጥናት ዘገባው አደረጃጀት፤
4) የጥናት ዘገባው አላማ፣ የባለሀብቱን ግዴታ፣ የህግ ተጠያቂነትንና በቀጣይ የሚከናዎኑ ተግባራትን የሚያገልጽ መሆን አለበት፡፡
1.3 የአካባቢ ተጽእኖ ጥናቱ ዓላማ
ከፕሮጀክቱ ትግበራ በፊት የአካባቢ ተጽዕኖ ጥናት ማካሄድ ያስፈለገበት ጥቅል አላማና የአካባቢ ተጽዕኖ ጥናቱ የሚያረጋግጣቸው ዝርዝር አላማዎች በዚህ ክፍል በአግባቡ ሊገለጹ ይገባቸዋል፡፡ የአካባቢ ተጽዕኖ ጥናቱ በዚህ ክፍል ለተለዩት ዝርዝር አላማዎች ምላሽ የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡
1.4 የጥናቱ ወሰን
ፕሮጀክቱ የአካባቢ ተጽእኖ ጥናት የሚያስፈልገዉ ከሆነና የአካባቢ ወሰን ልየታ ጥናት የተካሄደለት ከሆነ በዚህ ጥናት በተካተተዉ ቢጋር ውስጥ የጥናቱ ጥልቀትና ስፋት በግልጽ መጠቀስ ይኖርበታል፡፡ ፕሮጀክቱ የአካባቢ ተጽእኖ ጥናት ማካሄድ የሚያስፈልገው ከሆነ የጥናቱ ወሰን እንደ ፕሮጀክቱ አይነትና ፕሮጀክቱ እንደሚተገበርበት አካባቢያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ተለይቶ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ የጥናት ወሰኑ የፕሮጀክቱን የጥናት ክልል የሚያሳይ ካርታ ሊያካትት ይገባዋል፡፡
1.5 የጥናቱ ስልት ወይም ዘዴ
በዚህ ክፍል አወንታዊና አሉታዊ የአካባቢ ተፅእኖዎችን ለመለየት፣ ለመተንበይና ለመተንተን፣ እንዲሁም ያሉ አማራጮችንና የማቃለያ እርምጃዎችን ለመለየትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማሳተፍ ጥቅም ላይ የሚውሉ ዘዴዎች የሚገለጽበት የዘገባ ክፍል ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ክፍል የሚከተሉትን ነጥቦች በግልፅ ማስቀመጥ ይገባል፡-
1) ጥናቱን ለማካሄድ ጥቅም ላይ የሚውል የጥናት ስልት፣
የሚያስፈልግ ግብዓት፣ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችና የትንተና ዘዴዎች (ለምሳሌ የባለሙያዎች ሙያዊ አስተያየት፣ የአዋጭነት ትንተና፣ የመገምገሚያ ቅፆች፣ ከአሁን በፊት ያሉ ልምዶች፣ የቦታ ሽፋን፣ ወዘተ)
2) የሚመለከታቸውን አካላት ለማሳተፍ ጥቅም ላይ የሚውል የማሳተፊያ ዘዴ ወይም ስልትና የተሳትፏቸው ደረጃ
3) በጥናቱ የሚሳተፉ ባለሙያዎች ብዛት፣ የሙያ ስብጥር፣ ኃላፊነትና ሙሉ አድራሻ
1.6 በጥናቱ ወቅት የተወሰዱ ታሳቢዎች እና የነበሩ የእውቀት ክፍተቶች
በቂ የመረጃ ምንጭ ባለመገኘቱ የተነሳ ሊተገበር በታሰበው ፕሮጀክት ዙሪያ የሚሰበሰቡ መረጃዎች ከአጠራጣሪ ምንጮች ሊሰበሰቡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት አንዳንድ የጥናት ዳሰሳዎች በግምት ወይም በመላምት ላይ ተመርኩዘው ሊሰሩ ስለሚችሉ ተፅእኖዎችን ለመተንበይና ለመተንተን ክፍተት ሊገጥም ይችላል፡፡ ስለዚህ ጥናቱን የሚያዘጋጀው አካል የሚከተሉትን ነጥቦች በማካተት የዳሰሳ ጥናቱን የእርግጠኛነት ደረጃ በግልፅ ማመላከት ይኖርበታል፡፡ በዚህ ክፍል፡-
1) በጥናት ሂደት ያጋጠሙ የእውቀት ክፍተቶችን፣ በይሆናል የተወሰዱ መረጃዎችንና የመረጃ ምንጭ ያልተገኘላቸውን ጉዳዮች ይለያሉ፣
2) መላምቶች ያልተሟሉ የሆኑበትን ምክንያት ይዘረዘራል
3) የተለዩት የእውቀት ክፍተቶችና መላምቶች በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሚኖራቸው እንድምታ
4) ያጋጠሙ እጥረቶችንና ውስንነቶችን ለማስወገድ የተወሰዱ መፍትሄዎች መገለጽ ይኖርባቸዋል፡፡
1.7 የፖሊሲ፣ የህግና የአስተዳደር ማዕቀፎች
ይህ ክፍል ፕሮጀክቱ ሲተገበር ሊፈጽማቸውና ሊመራባቸው የሚገቡ የፖሊሲና ህጋዊ ማዕቀፎችን የሚዘረዝር የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ሪፖርት ክፍል ሲሆን ፕሮጄክቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የፖሊሲ፣ የህግና የአካባቢ ደረጃ ማዕቀፎች በጥናቱ ይዳሰሳሉ፡፡ ከቦታውና ከፕሮጀክቱ ጋር ተገቢነትና ተያያዥነት ያላቸው ተጨማሪ የህግ ክፍሎች በዕዝል ይያያዛሉ፡፡
1.8 የፕሮጀክቱ ገለፃ
በዚህ ክፍል የሚከተሉት ነጥቦች መካተትና መገለፅ አለባቸው፡-
1) የፕሮጀክቱ ስፋትና ባህሪ፣
2) ለፕሮጀክቱ የተለያዩ አማራጮች ግልፅ ማብራሪያ፣
3) የጥሬ እቃዎች ምንጭ፣ አይነት፣ ባህሪና መጠን፣
4) በምዕራፎች የተከፋፈለ የፕሮጀክቱ የትግበራ የጊዜ ሰሌዳ፣
5) የቴክኖሎጂ አይነትና የቴክኖሎጅ አጠቃቀም ገለጻ፣
6) የአመራረት ሂደት፣ የተረፈ-ምርቶችና ዋና ምርቶች አይነትና መጠን
7) የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ የማፅዳትና የማስወገድ ስርዓት፣
😎 የሰውና የግብዓት ፍጆታ ወጪዎች፣
1.9 የባዮፊዚካልና ማህበረ-ኢኮኖሚ መሰረታዊ መረጃዎች ትንተና
በዚህ ክፍል የፕሮጀክቱን አካባቢዊ ሁኔታ የሚገልፅ መሰረታዊ መረጃ በመሰብሰብ አካባቢውን በትክክል የሚያሳይ ዘገባ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ክፍል በፕሮጀክቱ ምክንያት ጉዳት ወይም ተጽዕኖ ስለሚደርስባቸው አካባቢዎች ትኩረት በመስጠት ግልፅ ማብራሪያ ማካተት/መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ በመሆኑም መካተት የሚገባቸው መረጃዎች፡-
1) ፕሮጀክቱ የሚተገበርበትን ልዩ ቦታ የሚመለከት መረጃ (ለምሳሌ የአካባቢውን የመሬት ስሪት ወይም የይዞታ ሁኔታ፣ በዙሪያው ስለሚገኝ የመሬት ሁኔታ፣ በአካባቢው ላይ ያሉና በግልፅ የሚታዩ ተግዳሮቶች፣ በፕሮጀክቱ ውስጥና በአካባቢዉ ያለው የመሰረተ-ልማት አገልግሎት ሁኔታ ወዘተ)፣
2) አሃዛዊና አሃዛዊ ያልሆኑ ፊዚካላዊና ስነ-ህይወታዊ የአካባቢ መረጃዎች (ለምሳሌ፡- የአየር ንብረት፣ የአፈር፣ የውሃ ሀብት፣ የስርዓተ ምህዳር፣ የመሬት አቀማመጥ፣ የዕፅዋትና የእንስሳት አይነት ስርጭትና ብዛት ወዘተ…….)፣
3) አሃዛዊና አሃዛዊ ያልሆኑ የማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ መረጃዎች (ለምሳሌ የህዝብ ቁጥርና ስርጭት፣ የዕድሜ ስብጥር፣ የኢኮኖሚ እድገት ሁኔታ፣ የውልደትና የጤና ሁኔታ፣ የቤተሰብ የገቢ ሁኔታ መረጃ፣ የኑሮ ሁኔታ፣ የመሰረተ-ልማት አገልግሎት፣ የቤቶች ሁኔታ፣ የሃይል ፍጆታ፣ የውሃ አቅርቦት ወዘተ…..)
4) የባህላዊና ታሪካዊ ቦታዎች ገለጻ (ለምሳሌ ብሄራዊ ፓርኮች፣ የዱር እንስሳት መጠለያ ቦታዎች፣ የመስህብ ቦታዎችና ሃውልቶች፣ በሰውና በእንስሳት ምስል የተሰሩ ሀውልቶች፣ ትኩረት የሚሰጣቸው ሃይማኖታዊ ቦታዎች ወዘተ…..)፣
5) ተጽዕኖ የሚደርስበትን ቦታ የሚያመለክቱ ኮኦርድኔቶች፣ ከለር ፎቶግራፎች፣ ሰንጠረዥና ሌሎች ገላጭ መረጃዎች፣
6) የፕሮጀክቱ የትግበራ ቦታ ካርታና የፕሮጀክት ሳይት ፕላን፣
7) ፕሮጀክቱ ድንበር ተሻጋሪ ተፅዕኖ የሚያደርስ ከሆነ ተጽእኖ የሚደርስበት አካባቢ የፊዚካላዊና ስነ-ህይወታዊ እንዲሁም የማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ መረጃዎች ናቸው፡፡
1.10 የአካባቢ ተጽዕኖ ትንተና ማካሄድ
ይህ ክፍል አዎንታዊና አሉታዊ የአካባቢ ተፅእኖዎች የሚለይበት፣ የሚተነበይበትና የሚተነተንበት ወሳኝ ክፍል ነው፡፡ የእያንዳንዱ ተፅእኖ ትንተና የሚከተሉትን ነጥቦች ሊያካትት ይገባል፡-
1) የእያንዳንዱ ተጽእኖ ግልጽ ማብራሪያና ትንታኔ (ምሳሌ የተፅዕኖው መጠን፣ የቦታ ስፋት፣ የሚቆይበት ጊዜ፣ ድግግሞሽ፣ ደረጃ፣ ተጽእኖ የደረሰበት አካባቢ ወደነበረበት መመለስ የሚቻል መሆኑና አለመሆኑ፣ ስጋትና ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ክስተት፣ ተጽዕኖ የሚደርስባቸው ክፍሎች መጠን ወዘተ) መለየት፣
2) በፕሮጀክቱ ውስጥና አካባቢ የሚገኙ ተጽዕኖ የሚደርስባቸው አካላት ትንተና፣
3) ፕርጀክቱን ለመተግበር የተለዩ አማራጮች ንጽጽር (ስፋት/መጠን፣ መገኛ ቦታ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፕላን፣ የሃይል ምንጭ፣ የጥሬ እቃዎች ምንጭ፣ ቴክኒካዊ ተፈጻሚነት፣ የአካባቢዊና ማህበራዊ ችግሮች/እጥረቶች)፣
4) አዲሱ ፕሮጀክት ከነባር ፕሮጀክቶችና ወደፊት ሊሰሩ ከታቀዱ ፕሮጀክቶች ጋር ሲዳመር ሊደርስ የሚችለውን ተዳማሪ የአካባቢና ማህበራዊ ተጽዕኖ፣
5) የተጽዕኖ ትንበያ የእርግጠኛነት ደረጃ፣
6) የተሻሉ አማራጮችን ለመምረጥ የተሰበሰቡ መረጃዎች ምዘና ናቸው፡፡
1.11 የተፅዕኖ ማቅለያ እርምጃዎች
በፕሮጀክት ትግበራ ወቅት ጉዳት የሚያስከትሉ የፕሮጀክቱን ተግባራት ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ቀዳሚ አማራጭ ተደርጎ መወሰድ ሲኖርበት ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን የተፅእኖ ማቃለያ ተግባራት በሚከተለው መልኩ ተዘርዝረው መቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡
1) ለእያንዳንዱ ተፅእኖ በእያንዳንዱ የፕሮጀክት የትግበራ ደረጃ ሊተገበሩ የሚገባቸው የተጽዕኖ ማቅለያ እርምጃዎች በአግባቡ ሊዘረዘሩና የሚያስፈልጋቸውም ወጪ (ገንዘብ) በበቂ ሁኔታ ሊመደብ ይገባል፡፡
2) የተለያዩ የማቃለያ እርምጃዎችን በመለየትና በማደራጀት ከተዘረዘሩት አማራጮች ውስጥ ምክንያታዊ በመሆን የተሻሉ የማቅለያ እርምጃዎችን በመምረጥ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡
3) አዎንታዊ ተፅእኖዎችንም እንዴት የበለጠ ማሳደግ ወይም ማሻሻል እንደሚቻል በዚህ ክፍል መገለጽ አለበት፡፡
1.12 የአካባቢ አያያዝ እቅድ
1) ይህ እቅድ ከተጽዕኖ ማቃለያ እርምጃዎች የሚቀዳ ሲሆን የሚከናወኑ ተግባራትን በአግባቡ የለየ፣ ፈጻሚ ባለቤት ያለው፣ ሊተገበር የሚችል፣ አፈጻጸሙ የሚለካ፣ ግልጽ የሆነ የአሰራር ስርዓት ያለው፣ በቂ በጀት ያለውና በጊዜ የተገደበ ሆኖ በተለያዩ የፕሮጀክት የትግበራ ምዕራፎች ወቅት አካባቢውን ለመጠበቅ የሚያስችል ዝርዝር አቅድ የሚዘጋጅበት የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ሪፖርት ክፍል ነው፡፡
2) በእቅዱ ውስጥ የሚካተቱ ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ሊሆኑ ይገባል፤
1) የተጽእኖዎች ዝርዝር
2) ለእያንዳንዱ ተጽእኖ የታቀዱ የተጽእኖ ማቅለያ ተግባራት ዝርዝር
3) የታቀዱ የተጽእኖ ማቅለያ ተግባራት መለኪያ
4) የታቀዱ የተጽእኖ ማቅለያ ተግባራት መጠን
5) ለእያንዳንዱ ተጽእኖ ማቅለያ ተግባራት የተመደበ ገንዘብ መጠን
6) የታቀዱ የተጽእኖ ማቅለያ ተግባራት የሚተገበሩበት የጊዜ ሰሌዳ
7) የታቀዱ የተጽእኖ ማቅለያ ተግባራትን የሚፈፅሙ አካላት ዝርዝር
) አንድ የአካባቢ አያያዝ እቅድ የቆያታ ጊዜ ጣሪያ 10 ዓመት ሆኖ በጸደቀ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ መተግበር መጀመር አለበት፡፡ በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ካለተጀመረ ጥናቱ ውድቅ ሆኖ እንደገና እንዲጠና ይደረጋል፡፡ አንድ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ሪፖርት ሲዘጋጅ የፕሮጀክቱን ቅድመ ግንባታ፤ ግንባታ፤ ትግበራና መዝጊያ ወቅት ታሳቢ ያደረገ መሆን ይገባዋል፡፡ ከአስር አመት የጊዜ ቆይታ በኋላ የአካባቢ ጥናት ዘገባው መከለስ ወይንም ደግሞ በአዲስ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡
4) የአካባቢ አያያዝ እቅድ ፎርማት በእዝል 15.1 የተያያዘ ሲሆን የሚዘጋጀው የአያያዝ እቅድ ከላይ የተጠቀሱትን ዝርዝር መረጃዎች መያዝ ይኖርበታል፡
5) የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮና ሌሎች የሚመለከታቸው የስራና የግንባታ ፈቃድ ሰጭ አካላት በምድብ አንድና ሁለት ለተካተቱ የልማት ፕሮጀክቶች (በአብክመ የተሻሻለውን የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የአሰራር መመሪያ ዕዝል አንድን ይመልክቱ) የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ሪፖርት ካልተዘጋጀላቸውና የአካባቢ ይሁንታ ፈቃድ ካልተሰጣቸው በስተቀር የግንባታ/ የስራ ፈቃድ መስጠት የለባቸውም፡፡
6) የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮና ሌሎች የሚመለከታቸው ፈቃድ ሰጭ አካላት በምድብ አንድና ሁለት ለተካተቱና የአካባቢ ይሁንታ ፈቃድ ለተሰጣቸው ፕሮጀክቶች የግንባታ/የስራ ፈቃድ በሚሰጡበት ጊዜ በተጽዕኖ ጥናት ዘገባው ውስጥ የተካተቱ የተጽዕኖ ማቃለያ ተግባራት በቀረበው ዲዛይን/የትግበራ ሂደት ውስጥ መካተቱን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው፡፡
ይቀጥላል............