18/11/2025
GSTS በትግራይ ጦርነት ዳግመኛ እንዳይቀሰቀስ ምሳሰቡ!
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የትግራይ አለም አቀፍ ባለሙያዎችና ምሁራን ሶሳይቲ በትግራይ ድጋሚ ጦርነት እንዳይጀመር አሳሰበ፡፡ የትግራይ አለም አቀፍ ባለሙያዎችና ምሁራን ሶሳይቲ(ጂኤስቲኤስ) ባወጣው መግለጫ እንደገለፀው በትግራይ ክልል ውስጥ ድጋሚ ጦርነት እንዳይጀመር የሚመለከታቸው አካላት በአስቸኳይ ተገቢ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቋል፡፡ ‹‹ከጉዳዩ አሳሳቢነት አኳያ በአስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ያለባቸው›› ያላቸው አካላት 2 ሲሆኑ እነሱም የኢትዮጵያ መንግስትና አለም አቀፉ ማህበረሰብ ናቸው፡፡
ጂኤስቲኤስ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አለም አቀፍ ማህበረሰብ በሚል የገለፃቸው በተለይ የአፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካና እንግሊዝ ሲሆኑ እነዚህም በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ላይ ከማመቻቸት ጀምሮ ፊርማው ሲፈፀም በታዛቢነት መገኘታቸውን ጠቅሷል፡፡ በመግለጫው በትግራይ ውስጥ ድጋሚ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት 2ቱም አካላት በአስቸኳይ ማድረግ የሚገባቸውን ጉዳዮችን በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ እነሱም ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል
1ኛ. በፕሪቶያሪው ስምምነትና በናይሮቢው ዲክላሬሽን መሰረት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውጭ የሆኑ ሀይሎች ከምእራብ፣ ከደቡባዊና ሰሜናዊ ትግራይ ክፍሎች በአስቸኳይ እንዲወጡ፣ በእነዚህ አካባቢዎች የተመሰረቱ ሁሉም ህገ ወጥ አስተዳደሮች እንዲፈርሱና የትግራይ ህገ መንግስታዊ ወሰን ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት እንዲመለስ፣
2ኛ . በፕሪቶሪያው ስምምነትና በአለም አቀፍ መልካም ተሞክሮ መሰረት ተፈናቃዮች ደህንነታቸው፣ ክብራቸውን ፈቃደኝነታቸው በተጠበቀ መልኩ ወደቤታቸው፣ መሬታቸውና ንብረታቸው እንዲመለሱና መልሶ የማቋቋም ድጋፍ እንዲያገኙ፣
3ኛ . ማንኛውም ጦርነት ቀስቃሽ ንግግር እንዲቆምና የትግራይ ህዝብ ሰላም፣ መልሶ መቋቋምና ፈውስ እንደሚፈልግ መቀበል፣
4ኛ. በትግራይ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ጦርነት ናፋቂና ሀላፊነት የማይሰማቸው የፖለቲካ ወይንም ወታደራዊ ተዋናዮች የሚያቀርቧቸውን ማናቸውንም መፈክሮች ወይንም መግለጫዎች የትግራይ ህዝብ እውነተኛ ፍላጎት አድርጎ ከመቀበል እንዲቆጠብ፣
5ኛ. ትግራይንና መላው አገሪቱን በሚመለከቱ ጉዳዮችን ህጋዊ፣ ህገ መንግስታዊ፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ መንገዶችን እንዲከተል፣
6ኛ. የፌዴሬሽን ምክር ቤትንና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ በፌዴራል ተቋማት የትግራይ ህዝብ ህጋዊ ድምፆችና መብቶች እንዲከበሩ፣
7ኛ. በትግራይ ውስጥም ሆነ በመላው አገሪቱ እንዲሁም በድንበር አቅራቢያ የሚገኙትን ጨምሮ የህዝቡን ደህንነትና ህልውና እንዲከበር ማድረግ የሚሉ ናቸው፡፡
ጂኤስቲኤስ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚጠበቁ ያላቸው ነጥቦች ደግሞ፡-
1ኛ የፌዴራል መንግስቱና የትግራይ ባለስልጣናት ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትና አፈፃፀሙ ተገዢ እንዲሆኑ ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጫና ማድረግ፣
2ኛ. የኢትዮጵያ መንግስት በህገ መንግስቱ እውቅና ከተሰጠው የትግራይ ግዛት ውስጥ ከመከላከያ ሰራዊት ውጭ የሆኑ ሀይሎችን ያለቅድመ ሁኔታ፣ በፍጥነትና ሙሉ በሙሉ እንዲያስወጣ መጠየቅ፣ ተፈናቃዮችንም እንዲመልስ ማሳሰብ፣
3ኛ. የትግራይ ግዛቶችን በተቆጣጠረው፣ በድንበር አቅራቢያ የሚገኙ ማህበረሰቦችን ህልውና አደጋ ላይ በጣለውና በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ጣልቃ እየገባ በሚገኘው የኤርትራ መንግስት ላይ ተጨባጭ እርምጃ እንዲወሰድ የሚሉ ናቸው፡፡