Tesfaye getahun

Tesfaye getahun Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from Tesfaye getahun, Business service, 0914069588, London.

20/08/2026

🙏🙏🙏


የደብረ ታቦር በዓል በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ ከዐበይት በዓላት የተመደበበትም ምክንያት በደብረ ታቦር የተገለጸው ምሥጢር ድንቅ በመሆኑ ነው። ደብረ ታቦር ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ በኩል 10 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ተራራ ሲሆን፤ ከፍታው ከባሕር ወለል በላይ 572 ሜትር ይሆናል፡፡ በዚህ ተራራ ላይ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን እንደሚገልጽ ምሳሌና ትንቢት ተነግሯል፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በትንቢቱ "ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል" ብሎ የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራቱን በዚህ ተራራ ላይ ገልጧል። መዝ. 88፥12 በዘመነ መሳፍንት ባርቅ ሲሣራን ከነሠራዊቱ ድል ያደረገው በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ነው፡፡ ምሳሌነቱም ባርቅ የጌታችን ሲሣራ ደግሞ የአጋንንት ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን በቂሳርያ "ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?" ብሎ ከጠየቃቸው ከስድስት ቀን በኋላ አዕማድ ተብለው የሚጠሩ ሦስቱን ሐዋርያት ይዞ ወደ ረጅም ታቦር ተራራ ወጣ፡፡ በፊታቸውም ተለወጠ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ፡፡ እነሆም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ መልሶ ጌታችንን "ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፡፡ ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ እንሥራ አንዱን ለአንተ አንዱን ለሙሴ አንዱን ለኤልያስ" አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፡፡ ከደመናውም "በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡ እርሱን ስሙት" የሚል ድምፅ ተሰማ፡፡ ሐዋርያት ይህንን ሰምተው የጌታችንን መለኮታዊ ክብር ዓይተው በፊታቸው ወደቁ እጅግ ፈርተው ነበር፡፡ ጌታችንም ተነሡ አትፍሩም አላቸው፡፡ በዚህ መልኩም አምላክነቱን ገለጠላቸው። ማቴ. 17፥1-10

ሦስቱ ሐዋርያት ለምን ተመረጡ?
አዕማደ ሐዋርያት ተብለው የተጠሩት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ናቸው፡፡ ገላ. 2፥9 ስያሜውን ያገኙበት ዋናው ምክንያት ጌታችን በኢያኢሮስ ቤት ልጁን ሲፈውስ፣ በጌቴ ሴማኒ ሲጸልይና በደብረ ታቦር ምሥጢረ መለኮቱን ሲገልጥ ከእሱ ስላልተለዩና ይዟቸው ስለሔደ ነው። ማር.5፥37-43

ሙሴና ኤልያስ ለምን ተመረጡ?
ሙሴንና ኤልያስን ወደ ደብረ ታቦር እንዲመጡ ያደረገበት ምክንያት የባሕርይ አምላክ መሆኑን እንዲመሰክሩ ነው፡፡ ሙሴን ከመቃብር ተነሥቶ ኤልያስ ደግሞ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ የባሕርይ አምላክነቱን መስክረዋል፡፡

ሙሴና ኤልያስ የተመረጡበት ሌላው ምክንያት ሙሴ "ጀርባዬንም ታያለህ ፊቴ ግን አይታይም" ተብሎ ስለተነገረለት (ዘፀ.33፥23) ኤልያስ "በኋለኛው ዘመን ምስክሬ ትሆናለህ"ስለተባለ ያንን ለመፈጸም ነው፤ ካገቡት ሙሴን ከደናግል ኤልያስ ያመጣቸው መንግሥተ ሰማያት በሕግ የተጋቡ ሕጋውያንና ሥርዐት ጠብቀው የሚኖሩ ደናግላን እንደሚወርሷት ለማስተማር ሁለቱን መርጧቸዋል፡፡

የደብረ ታቦር ምሳሌ
ደብረ ታቦር የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነች። ተራራ መሠረቱ ከመሬት አናቱ ከሰማይ እንደሆነ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንም መሠረቷ በምድር ሲሆን ራሷ በሰማይ ነውና። በሰማይ ካሉት ሙሴና ኤልያስን ከምድር ካሉት ጴጥሮስን ያዕቆብን፣ ዮሐንስን ሰብስባለችና፡፡ አንድም የወንጌል ምሳሌ ነው፡፡ ተራራ ሲወጡት አድካሚ ነው ከወጡት በኋላ ግን ሁሉንም ቁልጭ አድርጎ ሲያሳይ ደስ ያሰኛል፤ ወንጌልም ሲማሯት፤ ሲያስተምሯት ታደክማለች፤ ከተማሯት በኋላ ግን ጽድቅና ኀጢአትን፤ እውነትንና ሐሰትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ ታሰኛለችና።

19/08/2026
19/08/2026

ደብረ ታቦር

እንኳን ለደብረ ታቦር በዓል በሰላም አደረሰን፤ አደረሳችሁ!!!

መ/ር ጌታቸው በቀለ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥርዓት ከምታከብራቸው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኝ ዓበይት በዓላት አንዱ በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን የምናከብረው የደብረ ታቦር በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል ቡሄ በመባልም ይታወቃል፡፡

የደብረ ታቦር በዓል ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል /ማቴ. ፲፯፥፩ ማር.፱፥፩፤ሉቃ.፱፥፳፰/፡፡ በዚህ በዓል መለኮታዊ ክብሩ፣የነቢያትና የሐዋርያት ምስክርነት ይተረጎምበታል፡፡ በዚህ ጽሑፍም ስለ ደብረ ታቦር በዓል እንመለከታለን፡፡

ደብረ ታቦር (የታቦር ተራራ)

“ደብረ ታቦር” የሁለት ቃላት ጥምር ነው፡፡ “ደብር” እና “ታቦር” ፡፡ በዚህም መሠረት “ደብር” ማለት ተራራ፣ “ታቦር” ደግሞ በናዝሬት አካባቢ በሰማርያ አውራጃ በገሊላ ወረዳ የሚገኝ የረጅም ተራራ ስም ነው፡፡ ደብረ ታቦር ማለት የታቦር ተራራ ማለት ነው፤ የታቦር ተራራ የአይሁድ ማኅበረሰብ በዕብራይስጥ ቋንቋ ከፋር ታቦር (kfar-Tovor) ሲሉት፤ የእንግሊዘኛ ተናጋሪዎች (Transfiguration mount) ይሉታል፤ ብርሃነ መለኮቱ የተገለጠበት ተራራ እንደ ማለት ነው፡፡

ይህንን ተራራ ሁለቱ ወንጌላውያን ቅዱስ ማቴዎስና ቅዱስ ማርቆስ “ረጅሙ ተራራ” ሲሉት ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ “ቅዱስ ተራራ” በማለት ጠርቶታል /ማቴ. ፲፯፥፩፤ ማር.፱፥፩፤ ፪ጴጥ ፩፥፲፮-፲፰/፡፡ በዚህ ተራራ ላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን እንደሚገልጽ አስቀድሞ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል” ብሎ ተናግሮ ነበር /መዝ. ፹፰፥፲፪/፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ተራራ ላይ ብርሃነ መለኮቱን በመግለጡ፤ ተራሮችም የፈጣሪያቸውን ተዓምራት በማየታቸው የነቢያት ትንቢት ተፈጽሟል፡፡

የደብረ ታቦር ተራራ በምድረ እስራኤል ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ ደቡብ በኩል 17 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ከናዝሬት ከተማ በስተምሥራቅ፣ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ ቅዱስ ተራራ ነው፡፡ ደብረ ታቦር ከፍታው ከባሕር ጠለል (ወለል) 572 ሜትር ነው፡፡ በመስኩ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ሊቃውንት የታቦርን ተራራ ሥዕላዊ በሆነ መንገድ ሲገልጹ የተገለበጠ የሻይ ስኒ /Down Tea cup/ ይመስላል ይሉታል፡፡ በጥንት ዘመን ደብረ ታቦር ለእስራኤላውያን በጦርነት ጊዜ ሲያሸንፉ የሚደሰቱበት፣ ሲሸነፍም መደበቂያቸው እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል፡፡

በዚህ ተራራ ነቢዩ ሳሙኤል ትንቢት ተናግሮበታል፡፡ ንጉሥ ሳኦልም ከሦስት ሰዎች ጋር ተገኝቶበታል /፩ኛ ሳሙ.፲፥፫/፡፡ ርእሰ አበው አብርሃምና ኖኅ በዚህ ተራራ ላይ ቀስተ ደመና ተተክሎ አይተዋል፡፡ አባታችን ኖኅም ይህንን ተራራ “መካነ ብርሃን፤ የብርሃን ቦታ” ብሎ ጠርቶታል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ተራራ ላይ ክብሩን እንደገለጠና የዚህም ተራራ ስም ታቦር መሆኑን ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ገልጠዋል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ይህንን ረጅም ተራራ ደብረ ታቦር እያለ በድጓው ጽፏል፡፡ በዓለ ደብረ ታቦር ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፤ ብርሃን የታየበትና ድምፀ መለኮቱ የተሰማበት ዕለት ስለሆነ “የብርሃን በዓል” (Transfiguration) ይባላል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊሊጶስ ቂሳርያ ደቀመዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ!” ብሎ መሰከረ /ማቴ ፲፮፥፲፮/፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ የሃይማኖት መሠረት የሆነውን የጌታችንን ነገረ ተዋሕዶ ከመሰከረ ከስድስት ቀን በኋላ አዕማድ ሐዋርያት ተብለው የተጠሩትን ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስን ይዞ ወደ ተራራ አወጣቸው፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠው ከተስእሎተ ቂሣርያ በስድስተኛው ቀን (ነሐሴ ፲፫ ቀን) ነው፡፡

ደብረ ታቦር ተራራን ለምን መረጠ?

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ለመግለጽ የታቦር ተራራን የመረጠው፤ሌሎች ተራራሮችን ያልመረጠው ስለምንድን ነው? ቢባል ትንቢትና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡ ትንቢቱ፡- “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌስሑ ወይሴብሑ ለስምከ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል” /መዝ. ፹፰፥፲፪/ በማለት ነቢዩ ዳዊት ትንቢት ተናግሮ ነበርና ጌታም ብርሃነ መለኮቱን በታቦር ተራራ በመግለጹ ይህ ትንቢት ተፈጽሟል፡፡ ምሳሌው፡- ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ ነው፤ ይኸውም መስፍኑ ባርቅ ሲሣራን በታቦር ተራራ ድል ነስቶታል /መሳ. ፬፥፬—፳፬/፡፡

ተራራ የወንጌል ምሳሌ ናት፡፡ ተራራ ሲወጡት ያስቸግራል፤ ከወጡት በኋላ ግን ከታች ያለውን ሁሉ ሲያሳይ ደስ ይላል፡፡ ወንጌልም ሲማሯት ታስቸግራለች፡፡ ከተማሯት በኋላ ግን ጽድቅንና ኃጢአትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ ታሰኛለች፡፡ አንድም ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡ ተራራን በብዙ ጻዕር እንዲወጡት መንግሥተ ሰማያትንም በብዙ መከራ ያገኟታልና /ሐዋ.፲፬፥፳፪/፡፡ አንድም ተራራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በደብረ ታቦር ምስጢረ ሥላሴ እንደተገለጠ በቤተ ክርስቲያንም የቅድስት ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ይነገርባታልና፡፡ ተራራ መሠረቱ ከመሬት አናቱ ከሰማይ እንደሆነ ሁሉ፤ ቤተ ክርስቲያንም መሠረቷ በምድር ሲሆን ራሷ (ክርስቶስ) በሰማይ ነውና፡፡ የቤተክርስቲያን አገልጋዮቿ የተጠሩት ከምድር (ከዓለም) ሲሆን ክብራቸው ግን በሰማይ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “እኛስ ሀገራችን በሰማይ ነውና” እንዲል /ፊልጵ.፫፥፳/፡፡ በዚህም መነሻነት ጌታችን በልዩ ልዩ ኅብረ አምሳል ለደቀመዛሙርቱ ነገረ ተዋሕዶውን አስረዳቸው፡፡

ከነቢያት ሁለቱን ከሐዋርያት ሦስቱን ስለምን አመጣ?

ሁለቱን ከነቢያት ሦስቱን ከሐዋርያት ስለምን አመጣ ቢሉ ደብረ ታቦር የቤተክርስቲያን ምሳሌ መሆኑን ሲያስረዳ ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ነቢያት ያስተማሩት ብሉይ ኪዳንና ሐዋርያት የሰበኩት ሐዲስ ኪዳን ይነገራሉና፡፡ በደብረ ታቦር ነቢያት፣ሐዋርያት እንደ ተገኙ ሁሉ፤ዛሬ በቤተክርስቲያን ብሉይና ሐዲስ ኪዳን ይሰበካል፡፡ ሥርዐተ ቅዳሴ የሚፈጽሙ ልዑካን አምስት መሆናቸውም በደብረ ታቦር የተገኙትን ሙሴን፣ኤልያስን፣ጴጥሮስን፣ያዕቆብንና ዮሐንስን ያስታውሱናል፡፡ ዘወትር በቤተ መቅደሱ የሚፈተተው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ደግሞ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን የገለጠው የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡ አንድም ደብረ ታቦር የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡ በሕግ በሥርዐት ያገቡ ሰዎችም፣በንጽሕና በድንግልና በምንኩስና የአምላካቸውን ፈቃድ የሚፈጽሙ መናንያን፣ባሕታውያን፣መነኮሳት አንድ ሆነው መንግሥተ ሰማያትን እንደሚወርሷት ለማጠየቅ ከሕጋውያን ሙሴን ከደናግል ደግሞ ኤልያስን አመጣ፡፡ ሙሴን ከመቃብር አስነሥቶ ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ በደብረ ታቦር ተራራ አብረውት እንዲገኙ ያደረገው ደቀ መዛሙርቱ ሙሴ ነው ወይም ኤልያስ ነው በማለት ሲጠራጠሩ እንዳይኖሩ መለኮታዊ ትምህርት ለመስጠትም ነው፡፡

ቡሄ(ሔ)

የደብረ ታቦር በዓል በምእመናን ዘንድ ቡሄ(ሔ) በመባል ይታወቃል፡፡ ቡሄ በሀሌታው “ሀ” እና በሐመሩ “ሐ” ይጻፋል፡፡

በሀሌታው “ሀ” ሲጻፍ “ቡሄ” ማለት “የበራ የደመቀ የጐላ ብርሃን የብርሃን በዓል እንደ ማለት ነው ይህም በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈው ጌታችን በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን በገለጠ ጊዜ ፊቱ እንደ ፀሐይ በማብራቱ፥ ልብሱም አጣቢ በምድር ላይ ሊያነጣው እስከማይችል ድረስ በጣም ነጭ አንጸባራቂ ሆነ እንዲል፡፡ /ማቴ. ፲፯፥፩፤ ማር.፱፥፪፤ ሉቃ፱፥፳፱/፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል የሚዘከርበት እና ለበዓሉም ችቦ ስለሚበራ “የብርሃን በዓል” በማለት “የቡሄ በዓል” እንላለን፡፡ ወቅቱ የክረምት ፤ጨለማ አልፎ የብርሃን የሚወጣበት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት የመሸጋገሪያ ወቅት ነው፡፡ “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እንዲሉ፡፡

በሐመሩ “ሐ” ሲጻፍ “ቡሔ” ማለት ደግሞ “ደስታ ፍሥሐ” ማለት ይሆናል፡፡ ይኸውም በትንቢት እንደተጻፈው “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌስሑ ወይሴብሑ ለስምከ፤ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል” እንዲል /መዝ. ፹፰፥፲፪/፡፡ በዚህ ትንቢታዊ ቃል መሠረት በወቅቱ የጌታ ብርሃን በዙሪያቸው አብርቷል ከታቦርም እስከ አርምንዔም ተራራ ድረስ ታይቷል፡፡ ይህም መለኮታዊ ብርሃን በወረደበት ጊዜ ከብቶቻቸውን ይጠብቁ የነበሩ በታቦርና በአርሞንኤም አካባቢ ያሉ መዓልቱ የሌሊቱን ቦታ ስለ ወሰደው በሁኔታው ሐሴትን አድርገዋል፡፡

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል፡፡ ‹ቡሄ› ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና በበዓሉ ችቦ የሚበራውም ከዚህ ታሪክ በመነሣት ነው፡፡ ለክርስትና ልጅ፣ ለአማች፣ ለምራት፣ ለዘመድ አዝማድ ዅሉ የቡሄ ዳቦ ይሰጣል፡፡ ልጆችም ዳቧቸውን እየገመጡ ጅራፍ ሲገርፉ ይውላሉ፡፡

ጅራፍ

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ ነጎድጓዳማ ድምፅ መሰማቱን የብርሃን ጎርፍም መውረዱን በማሰብ በሀገራችን በኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶች ለነጎድጓዱ ምሳሌ አድርገው ጅራፍ በማጮኽ፣ የብርሃን ጎርፍ ምሳሌ አድርገው ችቦ በማብራት ያከብሩታል፡፡በደብረ ታቦር በዓል በትውፊታዊ መልኩ ጅራፍ መገመድ(መጥለፍ) እና ጅራፍ ማጮኽ ሁለት ዓይነት ምስጢር የያዘ ትውፊታዊ ተግባር ነው፡፡ የመጀመሪያው ግርፋቱንና ሞቱን እናስብበታለን፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ፤ድምፁን ስንሰማ የባሕርይ አባቱን የአብን ምስክርነት ቃል፤ እንደ ነጎድጓድ ድምፅ ያስታውሰናል፡፡የጅራፍ ትውፊታዊነት /ውርስ/፣ መጽሐፋዊ ትምህርትና ምስጢር ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ጨዋታውን በተራራማ አካባቢ፣ ከመኖሪያ ቤት ርቆና፣ በሜዳ ማድረጉ ጠቃሚ ነው፡፡

ችቦ

ችቦ የጌታችንን ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም ችቦ ለኩሰን በዓሉን እናከብራለን፡፡ የዚህ ትውፊታዊ አመጣጥ በብርሃኑ ድምቀት የቀኑን መምሸት ያልተረዱ እረኞች በሜዳ ቀርተዋልና ወላጆች ከመንደር ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ ሔደዋልና ታሪኩን እያዘከርን በዓሉት እናከብራለን፡፡ የችቦው መንደድም ሌላ ትርጉም አለው፡፡ አንድ ምእመን ለሌላው ምእመን መካሪ አስተማሪ መሆኑን፣ መከራ እየተቀበለም አርአያ፣ ምሳሌ፣ ብርሃን መሆኑን ያሳያል፡፡ በሃይማኖትም አርአያ ምሳሌ ይሆንላቸዋል፡፡

ሙሉሙል

“ሙልሙል/ኀብስቱ” በታቦር ተራራ ዙሪያ ለነበሩት እረኛች ወላጆቻቸው ምግባቸውን ይዘው መሄዳቸውን ያጠይቃል፡፡ አንድም የኀብስቱ ምሳሌነት ለክርስቶስ ነው “አነ ውእቱ ኅብስተ ሕይወት ዘወረደ እምሰማያት” እንዲል /ዮሐ፮፥፴፪/፡፡

በችቦ ብርሃን ልጆቻቸውን ፍለጋ የወጡ ወላጆች ዳቦ ጋግረው ይዘውላቸው ወጥተዋል፡፡ ስጦታው ቤተሰባዊነትን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን መግለጫ ነው፡፡ ወደ ቤታችን “ ቡሄ ” እያሉ ለሚመጡ አዳጊዎችም፤ ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጥ “ሙልሙል” ዳቦ አለ፡፡ ሕፃናቱም ሊዘምሩ ሲመጡይሰጣል፡፡ ሕፃናቱ የደቀመዛሙርት ምሳሌ ናቸው፡፡ መዝሙራቸው ደግሞ ሐዋርያት “የምሥራች” ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ ነው፡፡ ሐዋርያት በገቡበት አገር አስተምረው አጥምቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው በረከት አድለው እንደሚሔዱም፣ ልጆችም ዘምረው፣ አመስግነው፣ መርቀው “ውለዱ ክበዱ፣ ሀብት አግኙ፣ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ያድርጋችሁ ….” ይላሉ፡፡

እንደ መውጫ

የደብረ ታቦር በዓል በቤተክርስቲያናችን ከዋዜማው ጀምሮ እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ ማሕሌት ይቆማል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ስለ በዓሉ የደረሰው “በታማኞችህ ነቢያት በሙሴና በኤልያስ ፊት የባሕርይ ልጅነትህን መሰከርኩልህ” የሚለው መዝሙር በመዘመር ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ተሰጥቶት ይውላል፡፡ የአብነት ተማሪዎች እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ትምህርት ሃይማኖትን የሚማሩ ናቸውና ለሐዋርያት ነገረ መለኮቱን የገለጠ አምላክ እንዲገልጥላቸው በዓለ ደብረ ታቦርን በተለየ ድምቀት ያከብሩታል፡፡ አባቶቻችን ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊ በዓላትን በትምህርት ከማስተላለፍ ባሻገር ምሳሌነታቸውን በባሕላችን ውስጥ እንድንይዘው በማድረግ ሃይማኖታዊ አስተምህሮው ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲገለጽ ያደርጋሉ፡፡

በአጠቃላይ ኦርቶዶክሳውያን የደብረ ታቦርን በዓል ስናከብር ቅዱስ ጴጥሮስ “ለእኛ በዚህ መኖር መልካም ነው” እንዳለው በደብረ ታቦር በምትመሰለው በቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነን የቤተ ክርስቲያናችን ሕግና ሥርዐት አክብረን፣ በቤቱ ጸንተን እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ መኖር ይኖርብናል፡፡ በዓሉን ስናከብር በምስጋና በመዘመር እንጂ ሌሎች ሃይማኖታዊ መሠረት የሌላቸውን ባሕላዊ ነገሮች በማተኮር መሆን የለበትም፡፡

በአጠቃላይ በዓለ ደብረ ታቦር ከእነዚህ ምስክር ካላቸው ትምህርቶቹ፣ ምሥጢር ከሚራቀቅባቸው ትርጓሜያቱና ከትውልድ ትውልድ በቅብብል በተላለፈው ቅዱስ ትውፊት ጋር ሃይማኖታዊ ባሕል ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን አዳጊዎች ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ይዘው እንዲያድጉ ጥቆማ በመስጠት፣ ግጥም በመግጠምና ምሥጢሩን በማብራራት የመጀመሪያዎቹ ባለድርሻዎች ወላጆች ናቸው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዋቤ መጻሕፍት
✍️ መጽሐፍ ቅዱስ
✍️ መጽሐፈ ስንክሳር
✍️ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ
✍️ በዓላት
✍️ ኢንሳይክሎፒዲያ(መድብል)

19/08/2026

እንኳን ለደብረ ታቦር በዓል በሰላም አደረሳችሁ::

Address

0914069588
London

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Tesfaye getahun posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Shortcuts

Share