25/12/2025
በማህበራዊ ሚዲያ የሚደረጉ የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻዎች ታገዱ
አዲስ አበባ — የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በሰብዓዊ ድጋፍ ስም በማህበራዊ ሚዲያ የሚደረጉ ያልተፈቀዱ የገንዘብ ማሰባሰብ እንቅስቃሴዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ አሳሰበ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም በሰጡት መግለጫ፤ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የዲጂታል አማራጮች (Facebook, TikTok እና ሌሎችም) በቡድንም ሆነ በተናጠል የሚደረጉ የድጋፍ ማሰባሰብ ዘመቻዎች የአሰራር ስርዓትን የጣሱና ህገ-ወጥ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ኮሚሽኑ ይፋዊ የድጋፍ ጥሪ ባላቀረበበት ሁኔታ ህዝብን በማሳሳት ለግል ወይም ላልተገባ ዓላማ ገንዘብ የሚሰበስቡ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ በጥብቅ አሳስበዋል።
በተያያዘም በትግራይ ክልል ለተፈናቃዮች የሚቀርበውን ሰብዓዊ ድጋፍ አስመልክቶ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ህወሓት በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ዜጎች የሚላከውን እርዳታ በመንጠቅ "ድራማዊ ፕሮፓጋንዳ" እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ድርጊት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ የሚደረግ የፖለቲካ ቁማር ነው ብለዋል።
ቡድኑ እርዳታ ለችግረኞች እንዳይደርስ በማስተጓጎልና ድጋፉን ለራሱ ጥቅም በማዋል የህዝብ ጠላትነቱን ዳግም እያረጋገጠ መሆኑን ኮሚሽነር ሽፈራው ገልጸው፤ መንግስት ድጋፉ ለሚገባቸው ወገኖች እንዲደርስ ጥረቱን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
Via የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን
እናንተስ ምን ትላላችሁ በዚህ ጉዳይ ? ሀሳባችሁን አካፍሉን ?👇
🌴🌴🌴